መግቢያየሕይወት ታሪክመጻሕፍትየድምፅ ማኅደርቃለ ውግዘትግምጃ ቤት
 


የክቡር አባታችን የአለቃ አያሌው ታምሩ ዕረፍት ፩ኛ ዓመት መታሰቢያ በደማቅ ሥነ ሥርዐት ተከበረ።
ነሐሴ ፳፬ ቀን ፳፻ ዓ∙ ም∙

ነሐሴ ፲፬ ቀን ፲፱፻፺፱ ዓመተ ምሕረት ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት የክቡር አባታችን የአለቃ አያሌው ታምሩ ዕረፍት ፩ኛ ዓመት መታሰቢያ ቅዳሜ ነሐሴ ፳፬ ቀን ፳፻ ዓመተ ምሕረት በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የሩሲያ የሳይንስና የባህል ማእከል ፑሽኪን አዳራሽ ከ፫፻፶ የማያንሱ ጥሪ የተደረገላቸው ዕንግዶች በተገኙበት በደማቅ ሥነ ሥርዐት ተከበረ።

ይህን መታሰቢያ ምክንያት በማድረግ «የኑሮ መሠረት ለሕፃናት» የተባለችው ክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ በ፲፱፻፶፫ ዓመተ ምሕረት የጻፏት መጽሐፍ ለሁለተኛ ጊዜ ታትማ ለሕዝብ የቀረበች ሲሆን ይህችን መጽሐፍ የሚመለከት የዳሰሳ ጽሑፍ በአዳራሹ ለተገኙ ዕንግዶች ቀርቧል። ጽሑፉን ያቀረቡት ሊቀ ኅሩያን በላይ መኰንን ሲሆኑ ከመጽሐፉ ዳሰሳ በተጨማሪ የግእዝን ቋንቋ አስመልክቶ ክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ፤ «ግእዝ የአዳም ቋንቋ ነው፤» ይሉት ስለ ነበረው አስተምህሮ በጥናት የደረሱበትንና ምሁራንን ለተጨማሪ ምርምር የሚጋብዝ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል።

ጥናታዊ ጽሑፉን አስመልክቶ በተደረገው ውይይት መድረኩን የመሩት ስመ ጥሩ የሥነ ጽሑፍ ሰው ጸሐፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ በሰጡት ማጠቃለያ የግእዝ ቋንቋ የኢትዮጵያውያን አገር በቀል ሥልጣኔና ማንነት መሠረት መሆኑንና ጥበቃና እንክብካቤ ሊደረግለት የሚገባ ቋንቋ መሆኑን የገለጡ ሲሆን ትውልዱ ከዚህ ቋንቋ እየተራራቀ በመምጣቱ ምክንያት የኩረጃ ዕውቀትና የባዕዳን ባህል ተጽዕኖ የወደቀ ራእይ የለሽ ትውልድ እንዲሆን አድርጎታል በማለት ተናግረዋል።

ለውይይት ክፍት በተደረገው መድረክ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ተሳታፊዎችም የግእዝን ቋንቋ ጥቅምና ስለ ህልውናውም መቀጠልና መዳበር ያላቸውን ሐሳብ የሰጡ ሲሆን በቋንቋው መዳከም ምክንያት አሁን ባለው ትውልድ ላይ ተከስተዋል ያሏቸውን ጉዳቶችም በአጽንዖት ጠቁመዋል።

በሊቀ ኅሩያን በላይ መኰንን ከቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ አስቀድሞ በነበረው ሥነ ሥርዐት በዓሉ በጸሎት ከተከፈተ በኋላ የመግቢያ ንግግር የተደረገ ሲሆን የክቡር አለቃ አያሌው ታምሩን ቤተ ሰብ በመወከል ንግግር ያደረጉት ወይዘሮ ሥምረት አያሌው ነበሩ። ወይዘሮ ሥምረት አያሌው ባደረጉት ንግግር የዕለቱ በዓል የጻድቅ ሰውና የደገኛ መምህር መታሰቢያ መሆኑን የገለጡ ሲሆን ለዕለቱ በዓል የተመረጠው መነሻ ኃይለ ቃልም ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን የላከውና በምዕራፍ ፲፫ ቍጥር ፯ የሚገኘው፤ «ተዘከሩ መኳንንቲክሙ ዘነገሩክሙ ቃለ እግዚአብሔር ወእንዘ ትሬእዩ ሠናየ ግዕዞሙ ወሞፃእቶሙ ተመሰሉ በሃይማኖቶሙ።» «የእግዚአብሔርን ቃል የነገሯችሁን መምህሮቻችሁን ዐስቡ፤ መልካም ጠባያቸውንና ፍጻሜአቸውን አይታችሁም በሃይማኖት ምሰሏቸው፤» የሚለው መሆኑን አመልክተዋል። በዚሁ ንግግር ላይ እንደ ተገለጠው ለአገርና ለወገን የሚጠቅምና አርኣያነት ያለው ተግባር ሠርተው ያለፉ ሰዎችን ማሰብና ክብር መስጠት ጥቅሙ ለራስና ለመጪው ትውልድ መሆኑ የተገለጠ ሲሆን እነዚያን ሰዎች እና ባናስባቸው ትርፉ ለታሪክ ተወቃሽነት ራስን አሳልፎ መስጠት መሆኑም ተጠቁሟል። ሙሉውን ንግግር እዚህ ማየት ይችላሉ።

በዕለቱ ከቀረቡት ዝግጅቶች መካከል፤

  • ክቡር አባታችን አለቃ አያሌው ታምሩ የጻፏቸው ፲፩ መጻሕፍት ዝርዝርና እያንዳንዱ መጽሐፍ ያተኰረባቸውን ፍሬ ነገሮች፤
  • በተለያዩ ጊዜያት ከተነሧቸው ፎቶዎች በጥቂቱ፤
  • በዕረፍታቸው ወቅት ኢትዮጵያውያን ወገኖች የተሰማቸውን ኀዘንና ስለ እሳቸው ያላቸውን አክብሮት የገለጡባቸው የተለያዩ አስተያየቶች በዐውደ ርእይ መልክ የቀረቡ ሲሆን በቦታው የተገኙ ተጋባዥ ዕንግዶች እነዚህን ዝግጅቶች በአንክሮና በልዩ ትኩረት ጎብኝተዋቸዋል።

«የኑሮ መሠረት ለሕፃናት»፥ «ምልጃ፥ ዕርቅና ሰላም»፥ «መልእክተ መንፈስ ቅዱስ» የተባሉት መጻሕፍትም ለሽያጭ ቀርበዋል።

በሊቀ ኅሩያን በላይ መኰንን፥ በአቶ ንጉሤ አክሊሉ፥ በመሪጌታ አእምሮና በአባ ገብረ አምላክ አበበ የቀረቡ ዝማሬዎችና የቅኔ በረከቶች በዓሉ ከፍተኛ የሆነ መንፈሳዊ ስሜት እንዲሰፍንበት ያደረጉ ሲሆን፤ የአለቃ አያሌው ታምሩ የልጅ ልጆች የሆኑት ሦስት ወንድማማቾች ታምራት፥ መልካምና ኀይለ ልዑል «የኑሮ መሠረት ለሕፃናት» ከተባለው መጽሐፍ ውስጥ በቃላቸው አጥንተው ያቀረቡት የግጥም ንባብ ዝግጅትም ታዳሚውን ደስ አሰኝቷል። ግጥሙን ከዚህ ማንበብ ይችላሉ።

በዓሉ በጸሎት እንደ ተከፈተ ሁሉ በጸሎት ተዘግቶ የዕለቱ ሥነ ሥርዐት ከቀኑ ፲፩ ሰዓት ላይ ተፈጽሟል።

 

ተጨማሪ ገጾች።
 ዜናዎች
 አስተያየቶትን ይጻፉልን
 የ aleqayalewtamiru.org አባል ይሁኑ
ይህንን ገጽ ለወዳጆችዎ ያሳውቁ።
የኒውስሌተራችን ተጠቃሚ ይሁኑ
በየጊዜው የሚደረጉ ለውጦችን ለማወቅ ይመዝገቡ።
ሙሉ ስም
የኢሜይል አድራሻ
መውረድ የሚችሉ ፋይሎች
የክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ የመንፈቅ መታሰቢያ። (.zip, 28.3 MB)
የክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ የመንፈቅ መታሰቢያ። (light weight) (.zip, 2.4 MB)
Unable to read the text?
Download Font (nyala.ttf, 427KB)
For PC users: download and save the font file in "C:\Windows\Fonts" folder and restart your browser
(Nyala.ttf, © 2006 Microsoft Corporation. All Rights Reserved. Nyala is either a registered trademark or a trademark of Microsoft Corporation in the United States and/or other countries.)
መግቢያየሕይወት ታሪክመጻሕፍትየድምፅ ማኅደርቃለ ውግዘትግምጃ ቤት
Copyright  , aleqayalewtamiru.org