የተከበራችሁ ወገኖቻችን!
ጥሪአችንን አክብራችሁ በዚህ ዕለትና ቦታ በመገኘታችሁ በቅድሚያ በመላ ቤተሰቡ ስም እግዚአብሔር ያክብርልን እላለሁ።
ዛሬ ለመሰብሰባችን ምክንያት የሆነን ጻድቅ ሰው የምናከብርበት፥ ደገኛ መምህር የምናስብበት በዓል ነው።
ቤተሰባችን ይህን የዛሬውን መታሰቢያ ሲያዘጋጅ መነሻ ምክንያቱ ሥጋዊ ተዘምዶው ብቻ አይደለም። ዋነኛና መሠረታዊ ምክንያቱ ችላ ሊባል የማይቻል የእውነትና የእምነት ዕዳ ነው።
ከክቡር አባታችን ከአለቃ አያሌው ታምሩ የወረስነው ሥጋዊ አባትነታቸውን ብቻ አይደለም። መንፈሳዊ አባትነታቸውን ጭምር ነው። በቅርበት ያየነውን መንፈሳዊ ሕይወታቸውንና ብቃታቸውን ለመመስከር፥ ለመዘከርና ለማክበር፥ በእጃችን ላይ የሚገኙ መንፈሳዊ ቅርሶችንም ለቀሪው ወገናችን ለማካፈል የሚያስገድድ ኃላፊነት ይሰማናል።
ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስ በ፫ኛዪቱ መልእክቱ በቍጥር ፲፩ እና ፲፪ ላይ ስለ ተወደደ አገልጋይ ድሜጥሮስ ሲጽፍ «∙∙∙ ለድሜጥሮስ ሁሉ ይመሰክሩለታል፤ እውነት ራስዋ ትመሰክርለታለች፤ እኛም ደግሞ እንመሰክርለታለን፤ ምስክርነታችንም እውነት እንደ ሆነ ታውቃላችሁ፤» አለ።
የዓለም ታሪክ እንደሚያስተምረን ለእውነት፥ ስለ እውነት የተንገላቱ፥ የታሰሩ፥ የተሰደዱ፥ የተጋደሉና የተሰዉ ሰዎች ታሪካቸውን ራሳቸው በራሳቸው ጽፈው ያለፉ በመሆኑ ማንም ሰው ዐዲስ ታሪክ ሊጽፍላቸው አይችልም፤ እነሱ የጻፉትን ከማንበብ በቀር። በእርግጥ ከማንበብ ባሻገር ከተተኪ ትውልድ የሚጠበቅ ነገር አለ። ይኸውም በትምህርታቸው በመጠቀም፥ በምሳሌነታቸው በመመራት፥ የሚገባቸውን ክብርም ባለ መንፈግ ራስን፥ ወገንንና አገርን ከፈጣሪ ቁጣ ለመጠበቅ መጣርና ከኅሊናና ከታሪክ ተወቃሽነት፥ ከጡርም ለመዳን መሞመከር ነው። ከዚህ እምነት በመነሣት እኛም፤ «ተዘከሩ መኳንንቲክሙ ዘነገሩክሙ ቃለ እግዚአብሔር ወእንዘ ትሬእዩ ሠናየ ግዕዞሙ ወሞፃእቶሙ ተመሰሉ በሃይማኖቶሙ።» «የእግዚአብሔርን ቃል የነገሯችሁን መምህሮቻችሁን ዐስቡ፤ መልካም ጠባያቸውንና ፍጻሜአቸውን አይታችሁም በሃይማኖት ምሰሏቸው፤» በማለት ቅዱስ ሰዎች ለዕብራውያን ሰዎች በጻፈው መልእክት በምዕራፍ ፲፫ ቍጥር ፯ ያለውን ቃል የዚህ በዓል መሪ ኃይለ ቃል እንዲሆን መርጠናል። ይህ የሐዋርያው ቃል ለክርስቲያኖች ሁሉ የተሰጠ ምክር፥ ትእዛዝና መልእክት እንደ መሆኑ መጠን የእግዚአብሔርን ቃል ሲያስተምሩን የኖሩትን የክቡር አባታችንን ሃይማኖት፥ መልካም ጠባይና ፍጻሜ ለማዘከር መሰብሰባችን አግባብነት ያለው ነው ብለን እናምናለን።
ያለፉትን ፶ና ፷ ዓመታት ባካተተው የዘመን ሂደት ውስጥ ያለፍን ኢትዮጵያውያን ድንቅ የሆነ ተሰጥዖ ካላቸው ወይም ከነበራቸው ታላላቅ ኢትዮጵያውያን ጎራ የሚመደብ አንድ ሰው ለማሰብ፥ ለማዘከር ያህል ዕዝነ ኅሊናችንን ጥቂት ወደ ኋላ እንመልሰው ዘንድ እጠይቃለሁ።
- የክርስትናን ሃይማኖት ለይስሙላ ሳይሆን ለእውነት፥ ስለ እውነት እንድንኖርበት ያስተማረ፥ ሃይማኖትን ከምግባር አጣምረን እንድንተጋ የቀሰቀሰ፥ አገራችን ሀገረ እግዚአብሔር እኛም ሕዝበ እግዚአብሔር መሆናችንን ዐውቀን ሃይማኖታችንንና አገራችንን ከባዕዳን ወረራ እንድንጠብቅ ደጋግሞ ያስጠነቀቀ፥ ምክር ባንሰማ ግን ሊደርስብን ስላለው ሥጋዊና መንፈሳዊ ውድቀት ሳይሰለች፥ ሳይታክት የተናገረ፥ የገሠጸ፥ የጸለየ፥ የማለደ፥ እንቢ ባዮችንም አውግዞ የለየ አንድ ቆራጥ የሃይማኖት አባት ነበረ።
- ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት፥ ስለ እርስ በርስ ተዘምዷችን፥ ስለ ሰንደቅ ዓላማችን፥ ስለ ነጻነታችን፥ ስለ ግእዝ ቋንቋችን፥ ስለ ባህላችን ለመቅናት፥ ለመመስከር፥ ለመሟገት የማይፈራ፥ የማያፍር አንድ የታሪክ መምህር ነበረ።
- ስለ እምነቱ፥ ስለ አገሩ፥ ስለ ወገኑ የሚነገሩና የሚጻፉ ሐሰተኛ ታሪኮችን ከመቃወም፥ ከማጋለጥ ወደ ኋላ የማይሸሽ፥ የአምባገነኖችን አስፈሪ ግርማና ጉልበት የተጋፈጠ፥ ተጋፍጦም መስዋዕትነትን የከፈለ አንድ ሰማዕት ነበረ።
- ዋሽቶ በማስዋሸት፥ ክዶ በማስካድ የሠለጠኑ ሰዎች የእግዚአብሔርን ክብር በሰው ክብር ለውጠው ሹመትን፥ ሽልማትንና ገንዘብን ለማትረፍ በነገሥታትና በካህናት ዐደባባይ ጎንበስ ቀና እያሉ ሲሽሞነሞኑ፤ ቀድሞውኑ የነበረውን ክብርና ማዕረግ ሳይቀር በመናቅ እግዚአብሔር በማይከብርበት ዐደባባይ የሚገኝ ማዕረግና ክብር ይቅርብኝ ያለ አንድ መናኝ ሰው ነበረ።
- «የመንግሥት ሥልጣን የሚመነጭ ከሕዝብ ነው፤ የሕዝብ አንድነት፥ ሕይወትና ሥልጣኔም ከቤተ ክርስቲያን ጋራ ሥረ ወጥ ግንኙነት አለው። ስለዚህ ምን ጊዜም ቢሆን ብሔራዊት ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ አስፈላጊ ናት። በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንና በሌሎች እምነቶች ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያንም መሠረታዊና ብሔራዊ ልደታቸው ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ነው። ጥንታውያን አባቶቻቸውና እናቶቻቸው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መሆናቸውን ሳይዘነጉ ሁሉም በጥንተ እምነት እናታቸው የሆነችውን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን የእናትነት መብትና ክብር ማወቅና ማክበር በታሪክና በብሔራዊ ዓላማ ፊት እውነተኞች እንደሚያደርጋቸው ማወቅ ይገባቸዋል፤» እያለ ያስተማረ አንድ እውነት መካሪ ያገር ሽማግሌ ነበረ።
ከላይ የጠቀስናቸውና ሌሎች ተጨማሪ ብርቅና ድንቅ ስጦታዎች የታደለው ያ ሰው ከዛሬ ፹፭ ዓመታት በፊት በዲማ ቅዱስ ጊዮርጊስ ተወለደ። የ፫ ዓመት ተኩል ሕፃን ሳለ የዐይኑን ብርሃን አጣ። ዛሬ እኛ የምንደነቅባቸውን ተሰጥዖዎቹን ሁሉ አስቀድመው እንዳዩ ሁሉ አያቱ ተዋበች ዋሴ «አያሌው ታምሩ» ብለው ስም አወጡለት። «ትንቢት ይቀድሞ ለነገር» ይባል የለ! ያለ ወላጅ ጥበቃ፥ ያለ ቅርብ ሰው ክትትል በእግዚአብሔር ቸርነት ብቻ ተደግፎ ያ ሰው ከተወለደበት ቀዬ እስከ ነገሥታትና ካህናት ዐደባባይ ከፍ ከፍ አለ።
ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በሚያምኑና በሚያከብሩ ሁሉ ፊት ታፈረ፤ ተወደደ፤ ተከበረ። በሌሎች ፊት ደግሞ ተፈርቶ፥ ተጠልቶ፥ ተገፍቶ ፹፬ ዓመታት በዚህች በጊዜአዊት ቤት በዓለማችን ቆየ። በዕድሜው የመጨረሻ ዘመናትም፤ «ምነው ዕንባዬ እንደ ሐምሌና ነሐሴ ዝናም በፈሰሰ፤ ፈሶም የኢትዮጵያንና የቤተ ክርስቲያንን ውርደት ባጠበልኝ፤» እስከ ማለት የልቡን ኀዘን አሰምቶ ተናገረ። ተናግሮም አልቀረ ከተሠወሩ ዐይኖቹ የሚወጣ መሪር ዕንባን ስለ እኛ አየጸለየ አፈሰሰ።
«ፈቀደ እግዚእ ያግእዞ ለአዳም ኅዙነ ወትኩዘ ልብ፤» «እግዚአብሔር ያዘነ የተከዘ አዳምን ነጻ ሊያወጣው ወደደ፤» እያለ ለብዙ ዘመናት በጸለየባት በዕለተ ሰኑይ፥ የእናታችን የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም መታሰቢያ ሱባዔ በሚፈጸምባት በነሐሴ ፲፬ ቀን በሺ ፱፻፺፱ ዓመተ ምሕረት ሩጫውን ፈጸመ። ዐረፈ።
አዎ! እሱስ ዐረፈ። እኛ ግን አዘንን፤ ተሰቀቅን። ያኔ የዛሬ ዓመት በሞት ሲለየን ክብራችን፥ ሞገሳችን፥ አንደበታችን፥ ኅሊናችን የነበረውን ሰው አጥተናልና ባዶነት ተሰማን፤ መራራ ለቅሶም አለቀስን።
በወቅቱ የነበረውን ሁኔታና የሕዝቡን ኀዘን፤ «ከቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ሞት በኋላ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ኀዘን የፈጠረ ሞት፤» በማለት ነበር አንጋፋው ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ የገለጠው።
«እንደ አለቃ አያሌው ያለ ትልቅ ሰው የሌለበት አገር እንደ ባዶ ነው የሚቆጠረው፤» በማለት ባዶነታችንን የነገሩን ደግሞ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኀይሌ ነበሩ።
ሌላው ኢትዮጵያዊ ቴዎድሮስ አበበ ደግሞ፤
«የአባት ያለህ እንላለን ታላቁን ሊቅ ስንሸኛቸው፤
በእጅ ያለ ወርቅ እንደ ሆኑ ለተለዩን ላጣናቸው፤
ጠጥተን ሳንረካ ከውቅያኖሱ ዕውቀታቸው፤
ተምረን ሳንጠነክር ከዐለቱ ጽናታቸው፤»
በማለት የሁላችንንም ቁጭት ገለጡ።
ዛሬ እዚህ መድረክ ላይ ዐብሮን ያለ ወንድማችን ሊቀ ኅሩያን በላይ መኰንን ደግሞ፤
«እስቲ ንገሪኝ ኢትዮጵያ
እስቲ ንገሪኝ እማማ?
እስቲ ንገሪኝ ጎጃም
እኮ ንገሪኝ ዲማ?
ምሰሶው ከወደቀ የታሪካችን ማማ
በሞት እድፍ ከነተበ የኛነታችን ሸማ
አንደበተ ርቱዑን አያሌውን ካጣንማ
ጥያቄ ለማን እናቅርብ ታሪክሽን ከማን እንስማ?
የዘመን መለወጫ ዕንቊጣጣሽ ሲመጣ
«እዮሃ አበባዬ» ብለን ለደመራሽ ስንወጣ
«ወረደ ወልድ» እያልንም ወደ ከተራ ስንመጣ
ማን ይንገረን የነበረ ማን ያስተምረን ኬት መጣ?
አለቃ አያሌው ታምሩ ካልተገኘ በጉባኤ
የውጪው ማስሚዲያ ዶቼቬሌ ቪኦኤ
ማንን ጠይቆ ይዘግብ የገና የትንሣኤ?
እስቲ ንገሪኝ እማዬ?»
እያለ ፍርሃታችንን፥ ስጋታችንን፥ እጦታችንን ነገረን።
መጋቤ ምስጢር አሳየ በየነ የተባሉ የቅኔ ሊቅ ደግሞ፤ «ኢትዮጵያ ኢርእየት ወኢነጸረት ሕዋሳ፤ እስመ ዘመዓልት ጽልመት ለኢትዮጵያ ወረሳ፤» በማለት የሊቁ ሞት ለአገራችንን የዐይንን ብርሃን እንደ ማጣት፥ በቀን ጨለማም እንደ መዋጥ የከበደ መሆኑን ገለጡ።
እንደ ደገኛ ስሙ እንደ አያሌው ታምሩ፤
እንደ ተወጣው ግዳጁ እንደ ሥራና ተግባሩ፤
ጋዜጦች መጽሔቶች መሰከሩ ብዙ ጻፉ፤
ራዲዮና ድረ ገጾች የሕዝብን እሪታ ለፈፉ።
፫፻፷፭ ቀናት ዓመት መሆናቸው እስኪረሳ፤
ከትዝታው ማዕበል ጋራ ስንወድቅና ስንነሣ፤
ዛሬም ተሰብስበናል መልካም ግብሩን ልናወሳ።
የተከበራችሁ ወገኖች!
ዛሬ በምናከናውነው የመታሰቢያ በዓል ላይ ለኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን አንዲት መጽሐፍ ይዘን ቀርበናል። መጽሐፏ «የኑሮ መሠረት ለሕፃናት» ትባላለች። መጽሐፏ በመጠን ትነስ እንጂ በውስጧ ከፍተኛ የሆነ ቁም ነገርን ይዛለች። እንደ ስሟም ለኑሮ መሠረትነት የሚጠቅሙ ምክሮችን አካታለች። ክቡር አባታችን አለቃ አያሌው ታምሩ ይህችን መጽሐፍ የጻፏት ከዛሬ ፵፯ ኦመት በፊት ቢሆንም ከ፵፯ ዓመታት በኋላ ዛሬ ያለነውን ሰዎች ገና በርቀት ሳለን አይተውን የጻፏት ይመስላል።
የማንቸስተርንና የአርሴናልን ኳስ ተጫዋቾች፥ የሆሊዉድን የፊልም ተዋንያንና የሬጌና የራጋ አዚመኞችን የሕይወቱ እስትንፋስ ያደረገውን፥ ባለ ትልቅ ዋጋ ማንነቱን በኃጢአትና በዋልጌነት ድር በተሠሩ የመረጃ መረቦች ውስጥ ጥሎ የተጠመደውን፥ ዓላማ ቢስ ራእይ የለሽ ትውልድ ይሆን ዘንድ የተጠመደለትን የጫትና የተለያዩ ሱስ አምጪ ዕፀዋት ወጥመድ ተራምዶ ማለፍ ያቃተውን፥ ካላጣው ቁም ነገር በራሱ ላይ የሣቅ ንጉሥ ያነገሠውን ይህን የዛሬውን የእኛን ትውልድ አለቃ አያሌው ታምሩ ከ፵፯ ዓመታት በፊት በመንፈሰ እግዚአብሔር አዩት። አይተውም አዘኑለት። በራሱና በልጆቹ ህልውና ላይ ካንዣበበው የጥፋት አደጋ ይጠበቅ ዘንድ ለኑሮ መሠረት ያሉትን ትምህርት ጻፉለት።
ይህ ትምህርት በብዛት ለሕዝብ እንዲዳረስና ከአባታችን የወረስነውን ቅርስ ከወገናችን ጋር ለመካፈል ይኸው «ሀ» ብለን ጉዞ ጀምረናል። በቀረበው ትምህርት መጠቀም ደግሞ የሁሉም ሰው ተግባር ሊሆን ይገባል። የመጽሐፉ ዋጋ ከአንድ የልጆች ፊልም ወይም ሲዲ መግዢያ ዋጋ በጣም ያነሰ፥ ፈጽሞም የማይመጣጠን ነው። ጥቅሙ ግን ከገንዘብ ተመን በላይ ነው። ለመጪው የዘመን መለወጫ በዓል የመልካም ምኞች መግለጫ የምትለዋወጡ ወገኖች ይህን መጽሐፍ ለወላጆችና ለልጆች በስጦታነት ብትሰጡ ሥጋዊና መንፈሳዊ ግዳጅ እንደ ተወጣችሁ ሊቆጠር ይችላል።
ስለ መጽሐፉ አጠቃላይ ይዞታ እዚሁ መድረክ ላይ የዳሰሳ ጽሑፍ ስለሚቀርብ ይህንኑ በጥሞና እንድትከታተሉ እጋብዛለሁ።
በዚህ በዛሬው በዓል ላይ «የኑሮ መሠረት ለሕፃናት» ከተባለችው መጽሐፍ ሌላ ክቡር አባታችን የጻፏቸውን ሌሎች መጻሕፍትም ምናልባት በገበያ ላይ ላታገኟቸው ትችላላችሁ ብለን በማሰብ አቅርበናል። ገዝታችሁ ተጠቀሙባቸው።
ከመጻሕፍቱ ዜና በተጨማሪ ለክቡራን ወገኖቻችን የምናቀርበው ሌላ ዜና አለን። ይኸውም ከ፮ ወራት በፊት በሐሳብ ደረጃ አቅደነው የነበረ የክቡር አባታችን ስም የሚታሰብበት ማኅበር ምሥረታ ጉዳይ ነው።
ሐሳቡ በሐሳብ ደረጃ በቀረበበት ዕለት ከእናንተ ከወገኖቻችን በተቀበልናቸው ገንቢ አስተያየቶች መሠረትነት ከተለያዩ ባለሙያዎች ጋር መክረን ሕጉም የሚፈቅድልንን መንገድ አጥንተን በኢትዮጵያ ፍትኀ ብሔር ሕግ ቍጥር 404/52 መሠረት «አያሌው ታምሩ የግእዝ ቋንቋ ጥናትና ምርምር ማኅበር» ተብሎ የሚጠራ ድርጅት አቋቁመናል። የማኅበሩ ዋነኛ ዓላማ ክቡር አባታችን ለታሪካዊ ቅርስነቱ፥ ለህልውናው ሲሟገቱለት የነበረውን የግእዝን ቋንቋ ከጥፋት ለመታደግና ትውልዱም ጥቅሙን ተረድቶ በስፋትና በጥራት እንዲማረው፤ አባቶቹ በብዙ መሥዋዕትነት እንዳስረከቡት በማወቅም እሱ ደግሞ ለልጆቹ የሚያወርስበትን ሥራ መሥራት ነው።
የማኅበሩን ሕጋዊ አቅዋም የማስፈጸም ሂደት እንዳለቀ ጠቅላላ ጉባኤ የሚጠራ በመሆኑ የማኅበሩ አባል ለመሆን ፈቃደኛ የሆናችሁ ሁሉ የጠቅላላ ጉባኤ ጥሪ በምናደርግበት ጊዜ ከጎናችን እንደምትቆሙ በማመን ባለፈው ጊዜ ያልተመዘገባችሁ ወገኖችም ዛሬ ስምና አድራሻችሁን እንድታስመዘግቡ እንጠይቃለን።
ምንም እንኳ የአባታችን ከእኛ መለየት የሁሉም ወገን ኀዘን ቢሆንም በተለይ ቤተሰቡን በማረጋጋት፥ በማጽናናት፥ በመጠየቅ፥ ባዘጋጀናቸው የመታሰቢያ የጸሎት ጊዜዎች ላይ በመገኘት፤ ይልቁንም ደግሞ የመታሰቢያ ማኅበሩን የምሥረታ ሂደት በማፋጠን የተለያየ ትብብርና ድጋፍ ላደረጋችሁ ወገኖቻችን ሁሉ በዚህ ጉባኤ ፊት አክብሮቴን እየገለጽኩ እግዚአብሔር ይስጥልን እላለሁ።
መጪው ዐዲስ ዓመት የሰላም፥ የፍቅር፥ የበረከት፥ የሃይማኖት እንዲሆንልን እግዚአብሔር ይርዳን።
እግዚአብሔር ይስጥልኝ።