መግቢያየሕይወት ታሪክመጻሕፍትየድምፅ ማኅደርቃለ ውግዘትግምጃ ቤት
 


መጻሕፍት

፩፤ የኑሮ መሠረት ለሕፃናት። (፲፱፻፶፫ ዓ∙ ም∙)
፪፤ የኢትዮጵያ እምነት በሦስቱ ሕግጋት። (፲፱፻፶፫ ዓ∙ ም∙)
፫፤ መች ተለመደና ከተኲላ ዝምድና። (፲፱፻፶፫ ዓ∙ ም∙)
፬፤ ወላዲተ አምላክ በኢትዮጵያ። (፲፱፻፸፱ ዓ∙ ም∙)
፭፤ የጽድቅ በር። (፲፱፻፸፱ ዓ∙ ም∙)
፮፤ ምልጃ፥ ዕርቅና ሰላም። (፲፱፻፺፪ ዓ∙ ም∙)
፯፤ ተአምርና መጽሐፍ ቅዱስ። (፲፱፻፺፫ ዓ∙ ም∙)
፰፤ መልእክተ መንፈስ ቅዱስ። (፲፱፻፺፭ ዓ∙ ም∙)
፱፤ ዜና ሕይወት ዘቅድስተ ቅዱሳን እመ አምላክ። (፲፱፻፺፱ ዓ∙ ም∙)
 
፩፤ የኑሮ መሠረት ለሕፃናት። (፲፱፻፶፫ ዓ∙ ም∙)
  • ለግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ፸ኛ ዓመት በዓለ ልደት መታሰቢያነት የተዘጋጀ ነው።
  • በተለይ ለሕፃናት መማሪያነት ታስቦ የተዘጋጀ ስለ ሆነ መሠረታዊ (የመጀመሪያ ደረጃ) የሃይማኖት ትምህርት ይገኝበታል።
  • የተዘጋጀው ለሕፃናት እንዲስማማ በማሰብ በሦስት ዐይነት መልክ ማለት በስድ ንባብ፥ በግጥምና በጥያቄ ነው።
  • የግእዝና የአማርኛ ፊደል፥ ቁጥርና ፊደለ ሐዋርያ ይገኝበታል።
  • የሥነ ፍጥረትና የሔዋን ተፈጥሮ ታሪክ ይገኝበታል።
  • ዐሥሩ የኦሪት ትእዛዛትና ስድስቱ የወንጌል ትእዛዛት ተዘርዝረውበታል።
  • ስለ ባልና ሚስት ሥልጣን፥ ስለ ባልና ሚስት መፈቃቀርና መከባበር ትምህርት ይሰጣል።
  • ስለ ወላጆችና ስለ ልጆች፥ ስለ ገዢና ተገዢ መብት የተሰጠው የእግዚአብሔር ቃል ይገኝበታል።
  • እግዚአብሔርን መፍራት፥ ንጉሥን ማክበር እንደሚገባ ያስተምራል።
  • የዘወትር ጸሎትና ምስጋና ይገኝበታል።
፪፤ የኢትዮጵያ እምነት በሦስቱ ሕግጋት። (፲፱፻፶፫ ዓ∙ ም∙)
  • እምነት በኢትዮጵያ ያለውን አጠቃላይ ታሪክ ያቀርባል።
  • ሦስቱ ሕግጋት የተባሉት ሕገ ልቡና፥ ሕገ ኦሪትና ሕገ ወንጌል መሆናቸውንና በእነዚህ ሕግጋት እምነት በኢትዮጵያ እንዴት እያደገ እንደ መጣ በስፋት ያብራራል።
  • ኢትዮጵያ በሦስቱም ሕግጋት ጊዜ እግዚአብሔርን ከመከተል ያላቋረጠች አገር መሆኗን ያስረዳል።
  • በሦስቱ ሕግጋት ጊዜ ኢትዮጵያ ከእግዚአብሔር ያገኘቻቸውን ሀብታት በዝርዝር ይገልጻል።
  • ኢትዮጵያውያን እንዴት በሕገ ልቡናና በሕገ ኦሪት እየተመሩ በሕገ ወንጌል ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመቀበል እንደ በቁ ያብራራል።
  • ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ በአንዳንድ የውጭ አገር ጸሐፊዎች የተጻፈውን በማስተባበል ከኢትዮጵያውያን አባቶች የተገኘውን እውነተኛ ታሪክ ያቀርባል።
  • የግእዝን ቋንቋ መሠረትና እድገት ያትታል።
  • ክህነት በኢትዮጵያ መቼ እንደ ተጀመረ ያመለክታል።
  • የታላቁን ካህን የመልከ ጼዴቅን ኢትዮጵያዊነት ያስረዳል።
  • የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት መሠረቱና እድገቱ እንዴት እንደ ሆነ ያስተምራል።
  • ንግሥተ ሳባ ወይም ንግሥተ አዜብ ኢትዮጵያዊት መሆኗንና ከንጉሥ ሰሎሞን ቀዳማዊ ምኒልክን እንደ ፀነሰች ያስረዳል።
  • ቀዳማዊ ምኒልክ ከእስራኤል ታቦተ ጽዮንንና መጻሕፍተ ብሉያትን ይዞ ከሌዋውያን ካህናት ጋራ ወደ አኵስም እንደ ተመለሰ ያስረዳል።
  • ዐምስቱን አዕማደ ምስጢር በስፋትና በጥልቀት ያስተምራል።
  • ፍቅረ እግዚአብሔርና ፍቅረ ቢጽ ምን እንደ ሆኑ ያስተምራል።
  • ፍቅር፥ ጸሎት፥ ጾም፥ ምጽዋት፥ ስግደት፥ ትሕትና፥ ንጽሕና፥ ትዕግሥት፥ ንስሐ፥ ተዘክሮተ እግዚአብሔርና ምስጋና ምን እንደ ሆኑ፥ መሠረታቸው ምን እንደ ሆነና ጥቅማቸው ምን እንደ ሆነ ያብራራል።
  • በኢትዮጵያ የሚከበሩ በዓላት የትኞቹ እንደ ሆኑና መሠረታቸው ምን እንደ ሆነ ያስተምራል።
Kindle Edition on Amazon USA - 9.99 USD
፫፤ መች ተለመደና ከተኲላ ዝምድና። (፲፱፻፶፫ ዓ∙ ም∙)
  • ከአባ አየለ ተክለ ሃይማኖት ዘዐቢይ አዲ በ፲፱፻፶፩ ዓ∙ ም∙ ለተጻፈው «የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ስለ ክርስቶስ ባሕርያት አካላዊ ተዋሕዶ የምታምነው ትምህርት» የተባለ መጽሐፍ ሙሉ መልስ ሆኖ የተዘጋጀ ነው።
  • አባ አየለ፤ «የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንና የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ስለ ክርስቶስ የሚያምኑት እምነትና ትምህርት ልዩነቱ የቃል አገላለጽ እንጂ የምስጢር አይደለም፤» በማለት የገለጹትን ሐሳብ በመቃወም በመካከላቸው ሰፊ ልዩነት መኖሩን፥ ልዩነቱም ምን እንደ ሆነ በስፋትና በጥልቀት ያብራራል።
  • በተዋሕዶ እምነትና በጸጋና በቅባት መካከል ያለውን ልዩነት በስፋት ያብራራል።
  • በኢትዮጵያ ቤተ ክርያቲያንና በግብጽ መንበረ ማርቆስ መካከል ያለውን የእምነት አንድነት ያስረዳል።
  • የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የራሷን ተወላጆች ጵጵስና መሾም እስከ ጀመረችበት ጊዜ ድረስ ጳጳሳት ለምን ከግብጽ መንበረ ማርቆስ እየተሾሙ ይመጡላት እንደ ነበረ ያስረዳል።
  • «ባሕርየ መለኮት ከባሕርየ ትስብእት፤ አካለ መለኮት ከአካለ ትስብእት ስለ ተዋሐደ፤ ይህም ተዋሕዶ ከመዋሐድ በፊት በመለኮትና በትስብእት መካከል ያለውን ልዩነት አጥፍቶ አንድነትን አጸናው፤ ቃል ሥጋ ሆኖ ክርስቶስ ተባለ፤» በማለት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የምታምነውን እምነትና ትምህርት በስፋትና በጥልቀት ያብራራል።
Kindle Edition on Amazon USA - 9.99 USD
፬፤ ወላዲተ አምላክ በኢትዮጵያ። (፲፱፻፸፱ ዓ∙ ም∙)
  • በኢትዮጵያ በተለይ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያለውን አስተሳሰብ፥ ትምህርትና ባህል የሚገልጽ ነው።
  • ልዑል እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ኢትዮጵያን ለእናቱ ለእመቤታችን ርስት፥ ሕዝቧንም ዐሥራት አድርጎ መስጠቱን ያስረዳል።
  • ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ «እነሆ ልጅሽ»፥ «እነኋት እናትህ» በማለት በእመቤታችንና በክርስቲያኖች መካከል የዐደራ እናትነትንና የዐደራ ልጅነትን እንደ መሠረተ ያስተምራል።
  • ስለ እመቤታችን ዕረፍትና ትንሣኤ ይተርካል።
  • ለእመቤታችን የሚገባውን አጠራር፥ ምልጃና ምስጋና ያስተምራል።
  • እመቤታችን ስግደት፥ አምኃና በረከት እንደሚገባት ያስተምራል።
  • በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በእመቤታችን ስም የሚከበሩት በዓላት የትኞቹ እንደሆኑና እንዴት እንደሚከበሩ ይገልጻል።
  • በአጠቃላይ፤ ኢትዮጵያ ስለ እመቤታችን የምታደርገውን ሁሉ አምላክ ናት ብላ ሳይሆን አምላክን የወለደች፥ የአምላክ እናት ናት ብላ መሆኑን፤ ይህም የክርስትና እምነት፥ ትምህርትና ሥርዓት ተስተካክሎ ወደ አገራችን ከገባበት ጊዜ ጀምሮ የኖረ እንጂ ኋላ የመጣ አለመሆኑን ያስረዳል።
፭፤ የጽድቅ በር። (፲፱፻፸፱ ዓ∙ ም∙)
  • በተለይ ጾምን በተመለከተ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያለውን እምነት የሚገልጥና የሚያብራራ ነው።
  • የጾምን ትርጕም ያስረዳል።
  • የጾምን አጀማመርና ሥርዓት ይገልጻል።
  • በብሉይ ኪዳን የነበረውን የጾም ሥርዓት ያብራራል።
  • ጾም በሐዲስ ኪዳን ያለውን ቦታና የአፈጻጸም ሥርዓቱን ይዘረዝራል።
  • በሐዲስ ኪዳን ስላሉት አጽዋማት (ዐቢይ ጾም፥ ሰሙነ ሕማማት፥ ጾመ ድኅነት፥ ጾመ ስብከት፥ ጾመ ሐዋርያት፥ ጾመ ፍልሰታ፥ ጾመ ገሃድና ጾመ ነነዌ) ገለጻ ይሰጣል።
  • የጾም ኃይሎቿ ምን ምን እንደ ሆኑ ይዘረዝራል።
  • አርምሞ ምን እንደ ሆነና ለምን እንደሚጠቅም ያስረዳል።
  • የኅብረት ጾም ምን እንደ ሆነና በምን መልክ እንደሚፈጸም፥ ጥቅሙም ምን እንደ ሆነ ይገልጻል።
፮፤ ምልጃ፥ ዕርቅና ሰላም። (፲፱፻፺፪ ዓ∙ ም∙)
  • የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በተለይ ምልጃንና ዕርቅን በተመለከተ ያላትን እምነት በጥልቀትና በስፋት ለማስተማር የተዘጋጀ ነው።
  • ምልጃ ወይም ዕርቅ ምን ማለት እንደሆነ፥ ቃሉ ስንት ዐይነት መልኮችና አገባቦች እንዳሉት ያስረዳል።
  • የምልጃ መልኮች ምንና ምን እንደሆኑ ያስረዳል።
  • ምልጃ ወይም ዕርቅ በብሉይ ኪዳን በምን መልክ ይፈጸም እንደ ነበር ይገልጻል።
  • ሰውን ከእግዚአብሔር ለማስታረቅ ከአዳም ጀምረው የነበሩ ካህናትና ነቢያት የፈጸሙትን ምልጃ ይዘረዝራል።
  • ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውን ለመቤዠት የፈጸመውን የአስታራቂነት ሥራ በስፋት ያትታል።
  • ጌታችን የአስታራቂነቱን ሥራ በመስቀል ላይ ሞቶ ከፈጸመ በኋላ የአስታራቂነትን ሥልጣን ለቅዱሳኑ እንደ ሰጠ ያስተምራል።
  • የቅድስና ምንጭ እግዚአብሔር ቅድስናን ለአገልጋዮቹ እንዴት እንደሚያድል ያስረዳል።
  • የመላእክት፥ የእመቤታችን፥ የመስቀል፥ የቤተ ክርስቲያንና የጻድቃንና የሰማዕታት ቅድስና እንዴት እንደ ሆነ፥ ልዩነቱም ምን እንደ ሆነ ያስረዳል።
  • ሃይማኖት፥ ድኅነትና ሰላም ምን እንደ ሆኑ ያስረዳል።
  • ጸጋና መሠረቱ ተገልጾበታል።
፯፤ ተአምርና መጽሐፍ ቅዱስ። (፲፱፻፺፫ ዓ∙ ም∙)
  • ከጥላሁን መኮንን «መጻሕፍተ ኑፋቄ በመጽሐፍ ቅዱስ ዐይን ሲታዩ» በሚል ርእስ ለተጻፈ መጽሐፍ መልስ ሆኖ የተዘጋጀ ነው።
  • የተዘጋጀው ለእመቤታችን ለምክሐ ደናግል ማርያም ክብር ሲሆን መታሰቢያነቱ ለክቡር አቶ ሙሉጌታ ገብረ ወልድ ነው።
  • ተአምር፥ ገድልና ድርሳን ምን እንደ ሆኑ ይገልጻል።
  • በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ተአምር፥ ገድልና ድርሳን እየተባሉ የሚጠሩት መጻሕፍት የመጻሕፍት ቅዱሳትን ፍሬ ነገር የሚያብራሩ፥ የሚያስተምሩ እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን የማይቃወሙ መሆናቸውን ያስተምራል።
  • በተለይ ተአምር ምን ማለት እንደ ሆነና በብሉይ ኪዳንና በሐዲስ ኪዳን የነበረውንና ያለውን መልክ ያሳያል።
  • ተአምርና መጽሐፍ ቅዱስ የማይለያዩ፥ የማይነጣጠሉ ጥንትና ፍጻሜ መሆናቸውን ከብሉያትና ከሐዲሳት ማስረጃ እያጣቀሰ የሚያስተምር ነው።
  • አምላካችን በእመቤታችን አማካይነት ያደረገውን ተአምራት (ተአምረ ማርያም) ያስረዳል።
  • ስለ እመቤታችን ቅድስና፥ ንጽሕና፥ ድንግልናና አማላጅነት በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሚታመነውን ትምህርት ይገልጻል።
  • ስለ እመቤታችን በብሉይ ኪዳን የነበሩትን አምሳላትና ቃላተ ትንቢት የትኞቹ እንደ ነበሩ፥ ፍጻሜያቸውም ምን እንደ ሆነ ያስረዳል።
፰፤ መልእክተ መንፈስ ቅዱስ። (፲፱፻፺፭ ዓ∙ ም∙)
  • የኢትዮጵያን ተስፋ የሚያበሥርና በልዩ ልዩ የታሪክ መጻሕፍት የተገለጠውን ዜና የሚያመለክት ሥዕል በመጽሐፉ የጀርባ ሽፋን ላይ ይገኛል።
  • የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በተለይ ስለ መንፈስ ቅዱስ የምታምነውን እምነትና የምታስተምረውን ትምህርት ለመግለጽ የተዘጋጀ ነው።
  • ስለ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ፥ ስለ ልዩ ልዩ ሥራውም በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረትነት ለማስተማር የተዘጋጀ ነው።
  • መንፈስ የሚለው ቃል ያለውን ትርጕምና መልኮቹን ይገልጻል።
  • መንፈስ ቅዱስ ማን ነው? ወይም ምንድነው? ለሚለው ጥያቄ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረትነት ሰፊና ጥልቅ መልስ ይሰጣል።
  • ጌታችን የሰውን ልጅ ለመቤዠት ያደረገውን የአስታራቂነት ሥራ በዝርዝር ያቀርባል።
  • ጌታ ወደ መስቀልና ወደ ዕርገት ያደረገውን ጉዞ በስፋት ያስረዳል።
  • ክርስትና ምን ማለት እንደ ሆነ ያስረዳል።
  • ማዕተብ ምን እንደ ሆነ ያስረዳል።
  • ስለ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋና ክቡር ደም እንዲሁም በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ስላለው የቍርባን ሥርዓት ሰፊና ጥልቅ ገለጻ ያቀርባል።
  • እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ እንዴት ለክርስቲያኖች ልዩ ልዩ ሀብቶችን እንደሚያድል ይገልጻል።
  • መንፈስ ቅዱስ ክርስቲያኖችን እንዴት እንደሚጠራና ለመሥዋዕትነት እንደሚያዘጋጃቸው፥ ስምሪታቸውና ሰልፋቸውም እን ዴት እንደ ሆነ ያስረዳል።
  • የክርስቶሳውያን መሣሪያዎች ምን ምን እንደሆኑና ጥቅማቸው ምን እንደ ሆነ ይዘረዝራል።
  • የክርስትናን ሃይማኖት ጥልቀትና ርቀት፥ በውስጡም ያሉት ሀብቶች ምን ምን እንደ ሆኑ ይገልጻል።
  • ስለ ፍቅርና ስለ አንድነት ሰፊ ትምህርት ይሰጣል።
  • በማጠቃለያው በዮሐንስ ራእይ ምዕራፍ ፪ና ፫ ያሉትን መምሪያዎች በመተርጐም መንፈስ ቅዱስ ለቤተ ክርስቲያን ኃላፊዎች የሰጠውን መምሪያ ቃል ያብራራል።
፱፤ ዜና ሕይወት ዘቅድስተ ቅዱሳን እመ አምላክ። (፲፱፻፺፱ ዓ∙ ም∙)
  • የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በተለይ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የምታምነውን እምነት በመግለጽ በተለይ በአሜሪካ ባሉ በአንዳንድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናት እመቤታችንን አስመልክተው ለተጻፉ አንዳንድ ጽሑፎች መልስ ሆኖ የተዘጋጀ ነው።
  • በሙሴ ድንኳንና በሰሎሞን ቤተ መቀደስ የነበረችው ቅድስተ ቅዱሳን የእመቤታችን ምሳሌ እንደ ነበረች ያስረዳል።
  • በእመቤታችን ጸሎት ውስጥ ያሉትን ቃላት በስፋት በማብራራት ስለ እመቤታችን ቅድስናና ክብር ያስተምራል።
  • በመጽሐፈ ቀሌምንጦስና በመጽሐፈ ኩፋሌ ያሉትን ስለ እመቤታችን የተነገሩ ትንቢቶች ያብራራል።
  • በውዳሴ ማርያም፥ በቅዳሴ ማርያም፥ በቅዱስ ያሬድ ድርሰቶችና በሌሎችም መጻሕፍተ ሊቃውንት እመቤታችንን አስመልክቶ የተሰጠውን ትምህርት ያብራራል።
  • እመቤታችን ከጥንተ አብሶ ነጻመሆኗንና በሥነ ፍጥረት በአምላክ ቸርነት ታስባ፥ ተመርጣ ከአዳም ጀምሮ እስከ ወላጆቿ ድረስ በንጹሕ ዘርነት በአባቶቿ ወገብ ተቋጥራ ከትውልድ ወደ ትውልድ በ፷፮ቱ ትውልደ አበው እየተላለፈች መኖሯን ያስተምራል።
  • እመቤታችን የተፈጠረችው ለሰው ዘር ሁሉ ሕይወት መሠረት ሆና መሆኑን ያስረዳል።
  • እመቤታችን በ፷፬ ዓመት ዕድሜዋ ጥር ፳፩ ቀን ለሰው ልጆች በተሠራው ሥርዐት ሞትን መቀበሏን፥ ልጇ ነፍሷን ከሥጋዋ ለይቶ መቀበሉን፥ ሐዋርያት ሥጋዋን እንደ ሥርዐቱ በጌቴሴማን መቃብር ማሳረፋቸውን፥ ግን መላእክት ሥጋዋን ከዚህ አንሥተው በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር ማሳረፋቸውን፤ በመጨረሻም ባረፈች በ፪፻፭ ቀን ነሐሴ ፲፮ ቀን ጌታ በዕፀ ሕይወት ሥር ከነበረው መቃብር አስነስቶ ወደ መንግሥተ ሰማያት እንዳሳረጋት ያስረዳል።
  • እመቤታችን አምላክን በድንግልና ፀንሳ በድንግልና መውለዷን፤ ከዚያም በኋላም የተመረጠችበትን ክብር አግኝታ፥ የአምላክ እናት ሆና ከፍጥረት ሁሉ በላይ በሆነ የክብር፥ የቅድስና፥ የልዕልና መዓረግ እስከ ዕለተ ምጽአት የምትመሰገን መሆኗን፥ በመንግሥተ ሰማያትም ምስጋና የማይቋረጥባት መሆኗን በቅዱሳት መጻሕፍት መሠረትነት ያስተምራል።
ተጨማሪ ገጾች
 ዜናዎች
 አስተያየቶትን ይጻፉልን
 የ aleqayalewtamiru.org አባል ይሁኑ
ይህንን ገጽ ለወዳጆችዎ ያሳውቁ።
የኒውስሌተራችን ተጠቃሚ ይሁኑ
በየጊዜው የሚደረጉ ለውጦችን ለማወቅ ይመዝገቡ።
ሙሉ ሥም
የኢሜይል አድራሻ
መውረድ የሚችሉ ፋይሎች
የክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ የመንፈቅ መታሰቢያ። (.zip, 28.3 MB)
የክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ የመንፈቅ መታሰቢያ። (light weight) (.zip, 2.4 MB)
Unable to read the text?
Download Font (nyala.ttf, 427KB)
For PC users: download and save the font file in "C:\Windows\Fonts" folder and restart your browser
(Nyala.ttf, © 2006 Microsoft Corporation. All Rights Reserved. Nyala is either a registered trademark or a trademark of Microsoft Corporation in the United States and/or other countries.)
መግቢያየሕይወት ታሪክመጻሕፍትየድምፅ ማኅደርቃለ ውግዘትግምጃ ቤት
Copyright  , aleqayalewtamiru.org