መግቢያየሕይወት ታሪክመጻሕፍትየድምፅ ማኅደርቃለ ውግዘትግምጃ ቤት
 


የታላቁ ሊቅ የክቡር አባታችን የአለቃ አያሌው ታምሩ ዐጭር የሕይወት ታሪክ።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ።
«ክቡር ሞቱ ለጻድቅ በቅድመ እግዚአብሔር።»
«የቅዱሳኑ ሞት በእግዚአብሔር ፊት የከበረ ነው።» (መዝ፤ ፻፲፭፣ ፯።)

፩፤ ልደታቸውና ትምህርታቸው።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀዋሚ ምስክር የሆኑት አለቃ አያሌው ታምሩ፤ ከአባታቸው ከአቶ ታምሩ የተመኝና ከእናታቸው ከወይዘሮ አሞኘሽ አምባዬ፤ በጎጃም ክፍለ ሀገር በብቸና አውራጃ በእነማይ ወረዳ በታላቁ ደብር ወገዳም በደብረ ድማኅ ቅዱስ ጊዮርጊስ ልዩ ስሙ ቤተ ንጉሥ በተባለ ቦታ መጋቢት ፳፫ ቀን ሺሕ ፱፻፲፭ ዓመተ ምሕረት በዕለተ ሆሣዕና ተወለዱ።

ያለፈውንም የወደፊቱንም የሚያውቅ ልዑል እግዚአብሔር ለበለጠ ክብርና አገልግሎት ያዘጋጃቸው ቢሆንም ዕድሜአቸው ለትምህርት ሳይደርስ ገና የሦስት ዓመት ተኩል ሕፃን ሳሉ በፈንጣጣ ሕመም ምክንያት የዐይናቸውን ብርሃን አጥተዋል። የስምንት ዓመት ዕድሜ ልጅ ሳሉ በዓለ ተክለ አልፋን ለማክበር ከአባታቸው ጋር ወደ ዲማ እንደ ሄዱ በዚያው ትምህርታቸውን ለመቀጠል ስላሰቡ ወደ ቤታቸው አልተመለሱም። ከዚህ ጊዜ ጀምሮም በቅርብ ቤተ ዘመድ እየተረዱ ለአንድ ዓመት ያህል ሲማሩ ከቈዩ በኋላ አባታቸው ስላረፉ ኑሮአቸው በትምህርት ቤት ብቻ ስለ ተወሰነ ከቤተ ሰብእ ጋር የነበራቸው ግንኙነት እየቀነሰ መጣ። ይህም ሁኔታ የሚፈልጉትን ትምህርት በአንድ ልብ ለመቀጠል ግድ ብሎአቸዋል።

ክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ ምንም እንኳ ሥጋዊ የዐይን ብርሃናቸውን ቢያጡም ልበ ብርሃን በመሆናቸውና ትምህርትን ለመቀበል ፈጣን አእምሮን የታደሉ በመሆናቸው ካሰቡበት ለመድረስ አላገዳቸውም። በዚሁ መሠረት በ፲፭ ዓመት ዕድሜአቸው የቅኔ መምህር ለመሆን በቅተዋል። ስለ ዐይናቸው ብርሃንና ስለ ትምህርታቸው፤ «ምልጃ ዕርቅና ሰላም፤» በተባለው መጽሐፋቸው ገጽ ፬ ላይ እንዲህ ሲሉ ገለጸዋል። «ይህ ሁሉ የተገኘው ገና በልጅነት ዕድሜዬ፤ በቅዱስ ሐዋርያ ያዕቆብ እንደ ተነገረው የምመራበት፣ የምኖረበት በወሰድከው በዐይኔ ፈንታ ዕውቀት ስጠኝ ብዬ የለመንኩት አምላኬ፤ «ለምኑ ይሰጣችኋል፤ ሹ ታገኛላችሁ፤ በር ምቱ ይከፈትላችኋል፤ ለሚወደኝ እኔ ራሴን እገልጥለታለሁ፤» ሲል በሰጠው ተስፋና በለገሰኝ የአእምሮ ምጽዋት መሆኑን ስለምረዳ ነው፤» ብለዋል።

ታላቁ ሊቅ አለቃ አያሌው ታምሩ በተወለዱበት አካባቢ ባሳለፉአቸው ዓመታት የቀሰሙአቸው ዋና ዋና የቤተ ክርስቲያን ትምህርቶችና ያስተማሩአቸው መምህራን እንደሚከተለው ተዘርዝረዋል።

ሀ፤ መሪጌታ ከበበው፣ መሪጌታ እውነቴ፣ መሪጌታ ክንፉና መሪጌታ አልማው ከተባሉት መምህራን ጸዋትወ ዜማን ከጣዕመ ዝማሬው ጋር፤

ለ፤ አለቃ ማርቆስ፣ መሪጌታ ወልደ ኪዳን፣ መሪጌታ ያሬድ ከተባሉት መምህራን የግእዝን ቋንቋ ከጠቅላላ ሙያው ጋር፤

ሐ፤ አባ አካሉ፣ መምህር እጅጉ (ዘወልደ ማርያም) ከተባሉት መምህራን የሐዲሳትን ጣዕመ ትርጓሜ፤ ከብሉያት አራቱን ብሔረ ነገሥት፤ ትርጓሜ ዳዊት ከነቢያትና ከሰሎሞን ጋራ፤ የውዳሴ ማርያምና የቅዳሴ ማርያም ትርጓሜ።

ከላይ የተጠቀሱት ዋና ዋናዎቹ ሲሆኑ፤ ከዚህ ያልተጠቀሱትንም ሌሎች ትምህርቶች ሰንቀው ሰፊ አገልግሎት ወደሚሰጡበት ወደ አዲስ አበባ ከተማ በ፲፱፻፴፱ ዓመተ ምሕረት አጎታቸውን ታላቁን ሊቅ ክቡር መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬን ተከትለው መጡ።

ክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ ከዕውቀት ወደ ዕውቀት እያደጉ ከመሄዳቸውም በላይ ያወቅሁት ይበቃኛል ሳይሉ፤ ወደ አዲስ አበባም ከመጡ በኋላ፤

ሀ፤ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ መልካም ፈቃድ በጊዜው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት ተብሎ በሚጠራው ትምህርት ቤት ከስመ ጥሩው መምህር ፊላታዎስ መጽሐፈ ኢሳይያስን፣ መጽሐፈ ዐሠርቱ ወክልኤቱ ደቂቀ ነቢያትን፣ መጽሐፈ አስቴርን፣ መጽሐፈ ዮዲትንና መጽሐፈ ጦቢትን ከነ ሙሉ ትርጓሜአቸው፤

ለ፤ በዳግማዊ ምኒልክ መታሰቢያ ትምህርት ቤት ከመጋቤ ምስጢር ጌራ ስምንቱን ብሔረ ኦሪትና መጽሐፈ ዳንኤልን ከነ ትርጓሜአቸው፤

ሐ፤ ከመምህር ጽጌ (ኋላ ብፁዕ አቡነ ማርቆስ ዘጎጃም) የአርባዕቱን ወንጌል ትርጓሜ፤

መ፤ ከመምህር ገብረ ማርያም መጽሐፈ ኪዳንንና ትምህርተ ኅቡዓትን ተምረዋል።

አባታችን አለቃ አያሌው ታምሩ የቅድስት ተዋሕዶ ሃይማኖታቸውን ዕውቀት ካደላደሉ በኋላ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንና በሌሎች አብያተ ክርስቲያን መካከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ፤ እንዲሁም ባለ ማወቅ የተሳሳቱትን ለመመለስ፤ የእምነታቸውን መሠረትና የእንግሊዝኛ ቋንቋ፣ እንዲሁም ለዐይነ ሥዉራን የተዘጋጀውን የብሬል ጽሑፍ ለመማር ወደ እንጦጦ ወንጌላዊት ሚስዮን ትምህርት ቤት ገቡ። በዚያም የፈለጉትን ያህል መቀጠል ባይችሉም የብሬል ጽሑፍና መጠነኛ የሆነ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተምረው ወጥተዋል።

ክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ ስለ ትምህርታቸው በአጠቃላይ፤ «የኢትዮጵያ እምነት በሦስቱ ሕግጋት፤» በተባለው መጽሐፋቸው ገጽ ፲፭ ላይ የገለጹትን እንጠቅሳለን። «ትምህርቴ እንደ መምህሮቼና እንደ ትምህርት ቤቶቹም ብዛት ሙሉ አይደለም። ዕውቀቴም አነስተኛ ነው። ይህንኑ ከመምህራኑ ከሞላ ጎደል የሰማሁትን የትምህርት ጣዕም በጥቂቱ እንዳውቀውና እንዳስተውለኝ ያደረገኝ፤ ምሬቱንም ያጠነከረብኝ ዐዲሱ ዘመን ብዙ የትምህርት ዐይነቶችን ስላስገኘና በወንጌላዊት ሚሲዮን ትምህርት ቤት በነበርኩበት ጊዜ በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንና በሌሎቹ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን ልዩነት በደንብ ለማጥናት ስላገዘኝ፤ ከዚያ ወዲህ ራሴን መቆጣጠር ስጀምር ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት በሎንዶን ያሳተሙትን መጽሐፍ ቅዱስ በቤተ መጻሕፍት ወመዘክር አዘውትሬ መመልከቴ፣ ከመልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬና ከመምህር ይኄይስ ወርቄ ጋር በጥብቅ መነጋገሬ ነው። ሆኖም ዕውቀቴ በዚህ ሁሉ ፍጹም ሊሆን አልቻለም። ግን ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ፤ ስለ ቀናችው ሃይማኖቷና ስለ ተቀደሰው ምግባሯ፤ በእግዚአብሔርና በሷ መካከልም ስላለው ጥሩ ፍቅር በሕሊናዬ የሚወጣው የሚወርደው ሐሳብ እንደ እሳት ያቃጥለኛል። ቆሜ ተቀምጨ፣ ተኝቼ ተነሥቼ በምሄድበትና በማርፍበት፣ በምበላበትና በምጠጣበት ጊዜ ሁሉ ትሩር አድርጌ የምመለከተው እሱን ብቻ ነው። በዚህ ምክንያት በመኝታዬ ጊዜ እንኳ የጤና ዕንቅልፍ አጥቼ ሕልም ይሆንብኝና፤ «ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር፤» «አሐዱ ነገሩ ለኲሉ ዓለም፤» ያመጽኡ እምሳባ ወርቀ ወስኂነ፤» «ቃል ወልድ እኁየ ናሁ ውእቱ መጽአ፤» «ንግሥተ አዜብ ትትነሣእ አመ ዕለተ ደይን፤» «ናሁ መሰግላን መጽኡ እምብሔረ ጽባሕ፤» «ሁር ትልዎ ለዝንቱ ሠረገላ፤» «ቃል ሥጋ ኮነ፤» «ተሣሃለነ በሞተ ወልዱ፤» ስለሚሉትና እነሱንም ስለ መሳሰሉት ቃላት ሙሴን፣ ዳዊትን፣ ኢሳይያስን፣ ንግሥተ ሳባን፣ ማቴዎስን፣ ዮሐንስን፣ ሉቃስን፣ ፊልጶስንና ጳውሎስን ስጠይቅ አድራለሁ። ይሁን እንጂ፤ «ጥበብን የሚሻ ሰው ቢኖር ሳያወላውል ሳይጠራጠር ከእግዚአብሔር ይለምን፤ እግዚአብሔርም ንፍገት የሌለው አምላክ ነውና ይሰጠዋል፤» (ያዕ፤ ፩፣ ፭።) ብሎ ሐዋርያው ያዕቆብ እንደ ተናገረው፤ እግዚአብሔር አምላኬ የለመንኩትን ስላልነሣኝ፤ በዕውቀቴ ሳይሆን በቸርነቱ እየተረዳሁ ይህን መጽሐፍ ሳዘጋጅ ምስጋናዬን ለሱ አስቀድማለሁ፤» በማለት ገልጸዋል።

፪፤ መንፈሳዊ አገልግሎትና አስተዳደር።

ሀ፤ ወደ አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ዛሬ የክቡር ዐፅማቸው ማረፊያ በሆነው ደብረ አሚን ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን የቅኔ መምህርነት አገልግሎታቸውን በ፲፱፻፴፱ ዓመተ ምሕረት ጀመሩ። በመቀጠልም በዚሁ ደብር፤ መጀመሪያ የሊቀ ጠበብትነት ማዕረግ አግኝተው ያገለገሉ ሲሆን ኋላም የዚሁ ደብር አስተዳዳሪ በመሆን ሰፊ አገልግሎት አበርክተዋል።

ለ፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ቤተ ክህነት የሊቃውንት ጉባኤ ተመርጠው ከሰኔ ወር ፲፱፻፵፰ ዓመተ ምሕረት ጀምሮ የስብከተ ወንጌል ክፍል አባል ሆነው አገልግለዋል።

ሐ፤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሊቃውንት ጉባኤ አባልና ዋና ሰብሳቢ ሆነው ሠርተዋል። በዚህም የሥራ ዘመናቸው፤ የቤተ ክርስቲያን የወንጌል ትምህርት በመሆኑ ይህ አገልግሎት ሳይበረዝና ሳይከለስ እምነቱም፣ ትምህርቱም፣ ሥርዐቱም ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ የሚያስችለውን መንገድ ለመቀየስ በተሰጣቸው ኀላፊነት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ሌት ተቀን ሠርተዋል። ዐልፎ ዐልፎም ከውስጥም ሆነ ከውጪ ለሚነሡት መናፍቃን መልስ በመስጠት፣ በቤተ ክርስቲያኒቱ በየጊዜው የሚታተሙትን መጻሕፍት በማረምና ለኅትመት እንዲበቁ በማድረግ፤ ስለ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ ስለ ቅድስት ሀገራችን ኢትዮጵያ ለሚጠየቁ ጥያቄዎች መልስ በመስጠት፤ በበዓላትም ሆነ በሌሎች አጋጣሚዎች በራዲዮ፥ በቴሌቪዥን፥ በመጽሔቶችና በጋዜጦች ትምህርትና ምክር በማስተላለፍ ሀገራዊና ሃይማኖታዊ ኃላፊነታቸውን ተወጥተዋል። ክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ በነበራቸው ዕውቀትና ኀላፊነት፤ ሐዲስ ኪዳንን በግእዝና በአማርኛ ፥ መጽሐፈ ግጻዌ፥ ሃይማኖተ አበው የተባሉትን መጻሕፍት ከሌሎች የጉባኤው አባላት ጋር ተርጉመው እንዲታተሙ አድርገዋል። ከነዚህም በተጨማሪ በግላቸው ገድለ አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስን፥ ገድለ ቅዱስ ጊዮርጊስን፥ ገድለ ቅዱስ ቴዎድሮስ በናድልዮስን ከግእዝ ወደ አማርኛ ተርጉመዋል።

መ፤ ከሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢነት ሥራቸው ላይ ደርበው በተጨማሪ የኢተዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ መሥሪያ ቤት የታሪክና የሥነ ጽሑፍ ማደራጃ ዋና መምሪያ ሥራ አስኪያጅ በመሆን አገልግለዋል።

ሠ፤ በኢተዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ መንበርነት በሚመራው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት የአስተዳደር ጉባኤ ውስጥ አባል ሆነው ሠርተዋል።

ረ፤ በትንሣኤ ዘጉባኤ ማሳተሚያ ድርጅት ውስጥ የመጻሕፍት አዘጋጅ ኮሚቴ አባል ሆነው አገልግለዋል።

ሰ፤ በቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ መንፈሳዊ ኰሌጅ ከ፲፱፻፶፬ እስከ ፲፱፻፷፬ ዓመተ ምሕረት፤ እንዲሁም በተግባረ እድ ትምህርት ቤትና በቅዱስ ጳውሎስ ከፍተኛ መንፈሳዊ ትምህርት ቤት መንፈሳዊ ትምህርት አስተምረዋል።

ቀ፤ ከኢትዮጵያ ዓይነ ሥውራን ማኅበር መሥራቾች አንዱ ሲሆኑ፤ መጀመሪያ የማኅበሩ ምክትል ፕሬዚዳንት ኋላም የቦርድ ሊቀ መንበር በመሆን አገልግለዋል።

፫፤ በግላቸው ያዘጋጁአቸው መጻሕፍት።

ክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ በሕይወት ዘመናቸው ያበረከቷቸው አገልግሎቶች ዝርው ሆነው አልቀሩም። በመጽሐፍ ጥራዝ አዘጋጅተውና አሳትመው ለትውልድ ያስተላለፏቸው መጻሕፍት ዘጠኝ ሲሆኑ በይዘታቸው በሁለት የተከፈሉ ናቸው። በአንደኛው ክፍል ያሉት የቤተ ክርስቲያንንና የኢተዮጵያን ማንነት ለኢትዮጵያውያን ለማስተማር የተዘጋጁ ሲሆኑ፤ በሁለተኛው ክፍል ያሉት ደግሞ ከቤተ ክርስቲያን ውስጥም ሆነ ከቤተ ክርስቲያን ውጪ ለተነሡና ለሚነሡ መናፍቃን መልስ በመስጠት የምእመናንን ልቦና ለማጽናት የሚያስችል መልእክት የሚያስተላልፉ ናቸው። ከነዚህ መጻሕፍት ውስጥ ዐምስቱ በቤተ ክህነት አገልገሎት ላይ የተዘጋጁ ሲሆኑ፤ አራቱ ደግሞ ከቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በግፍ ከታገዱበት ከ፲፱፻፹፰ ዓመተ ምሕረት በኋላ የተዘጋጁ ናቸው።

በቤተ ክህነት አገልገሎት ላይ በነበሩበት ጊዜ ያዘጋጇቸው፤ «መች ተለመደና ከተኲላ ዝምድና»፥ «የኢትዮጵያ እምነት በሦስቱ ሕግጋት»፥ «የኑሮ መሠረት ለሕፃናት»፥ «ወላዲተ አምላክ በኢትዮጵያ»፥ «የጽድቅ በር» የተባሉት መጻሕፍት ናቸው። ከሥራ ገበታ ከታገዱ በኋላ በመኖሪያ ቤታቸው ሆነው ያዘጋጇቸው፤ «ምልጃ፥ ዕርቅና ሰላም»፥ «ተአምርና መጽሐፍ ቅዱስ»፥ «መልእክተ መንፈስ ቅዱስ»፥ «ዜና ሕይወት ዘቅድስተ ቅዱሳን እመ አምላክ» የተባሉት ናቸው።

፬፤ የቤተ ሰብእ ሁኔታ።

ክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ በቤተ ክርስቲያን ሥርዐት መሠረት በሥርዐተ ተክሊል ከወይዘሮ ርብቃ ልሳነ ወርቅ ጋር ሚያዝያ ፲፪ ቀን ፲፱፻፶ ዓመተ ምሕረት ጋብቻ ፈጽመው ፲፬ ልጆችና ፲፪ የልጅ ልጆች ለማፍራት ታድለዋል።

፭፤ ስለ ቅን አገልግሎታቸው የተሸለሟቸው ሽልማቶች።

ክቡር አባታችን አለቃ አያሌው ታምሩ እጅግ ይወዷቸውና ያከብሯቸው በነበሩት በግርማዊ ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ መልካም ፈቃድ፤

፩ኛ፤ በ፲፱፻፵፩ ዓመተ ምሕረት የመምህራን ሽልማት ሜዳይ፤

፪ኛ፤ በ፲፱፻፷፪ ዓመተ ምሕረት የኢትዮጵያ የክብር ኰከብ የፈረሰኛ ደረጃ ኒሻን ተሸልመዋል።

፮፤ ከቤተ ክህነት አገልግሎት ስለ መሰደዳቸው።

ክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት፥ ትምህርት፥ ሥርዐትና አስተዳደር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተለወጠና እየተበላሸ መሄዱ በእጅጉ ያሳዝናቸው ስለ ነበር፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ የሊቃውንት ጉባኤ ዋና ሰብሳቢ እንደ መሆናቸው መጠን፤ ጥፋቱ እንዲታረም ብዙ አቤቱታና ተማጽኖ ጉዳዩ ወደሚመለከተው ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ ቅዱስ ሲኖዶስ፤ ሲኖዶሱን በመሠረተና በሚመራው በመንፈስ ቅዱስ ስም ተማጽነው ቢያቀርቡም ሲኖዶሱ ጉዳዩን ለማፈን ከመሞከር በስተቀር ምንም እርምጃ ሳይወስድ ቀርቷል። እሳቸውም ያቀረቡት ጥያቄ መፍትሔ ባለማግኘቱ ጉዳዩን ለሚመለከተው ለኢተዮጵያ ሕዝበ ክርስቲያን ለማሳወቅና፤ በቤተ ክርስቲያን ላይ ዐመፅ የሚፈጽሙትን ፓትርያርኩንና የእሳቸው ተባባሪ የሆኑ ጳጳሳትን ባላቸው ከፍተኛ ኀላፊነተና ሥልጣነ ክህነት በሥልጣነ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ፥ በሥልጣነ ጴጥሮስ ወጳውሎስ ለማውገዝ ተገደዋል። ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናት በጸሎተ ቅዳሴ ጊዜ የዐመፀኛውን ፓትርያርክ ስም እንዳይጠሩ ውግዘት አስተላልፈዋል። ምእመናንም ከዐመፀኞች ካህናት ምንም ዐይነት አገልገሎት ማገኘት የማይችሉ መሆናቸውን ተገንዝበው ሕይወታቸውን በጥንቃቄ እንዲመሩ አሳስበዋል።

በዚህም ምክንያት ከ፶ ዓመት በላይ ካገለገሉበት የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት በሐሰት ክስና የእምነት ክሕደት ቃላቸውን ባልሰጡበት ሁኔታ ያለ ምንም ጡረታ ከሥራ ገበታቸው ላይ በግፍ እንዲነሡ በመደረጉ ከሚያዝያ ወር ፲፱፻፹፰ ዓመተ ምሕረት ጀምሮ እስከ ዕለተ ዕረፍታቸው በመኖሪያ ቤታቸው ተወስነው ኖረዋል። በነዚህ ዓመታትም በየዕለቱ ለጸሎት ባዘጋጇት አነስተኛ ክፍል በመገኘት ወደ ልዑል እግዚአብሔር በመጸለይና በማልቀስ ይተጉ ነበር። ምእመናንም በተኲላ እንዳይነጠቁ በተለያዩ ጋዜጦች ትምህርትና ማበረታቻ ሲሰጡ ኖረዋል። ከቤተ ክህነት በግፍ ተሰድጄአለሁ በማለትም ሥራቸውን አልዘነጉም፤ ከላይ ከጠቀስናቸው መጻሕፍት ውስጥ አራቱን ያዘጋጁት በዚሁ ጊዜ ውስጥ ነበር። እንዲሁም መኖሪያ ቤታቸው ድረስ እየመጡ ለሚጠይቋቸው ሰዎች መልስና ምክር በመስጠት አገልግሎታቸውን ሳያቋርጡ ቤተ ክርስቲያን የጣለችባቸውን ኀላፊነት ሲወጡ ኖረዋል።

፯፤ ዕረፍታቸውና የቀብራቸው ሥነ ሥርዐት።

ክቡር አባታችን ምንም አገራቸውንና ቤተ ክርስቲያናቸውን ለማገልገል በቁርጥ ዐሳብ ሲሠሩ ቢኖሩም፤ ከአዳም ጀምሮ ለሰው ልጆች ሁሉ የተሰጠውን የሥጋ ሞት ለመቅመስ የእሳቸውም ተራ በመድረሱ፤ ለጥቂት ቀናት በሕመም ከሰነበቱ በኋላ ነሐሴ ፲፬ ቀን ፲፱፻፺፱ ዓመተ ምሕረት፤ እጅግ ይወዷት የነበረችው የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም መታሰቢያ የሆነው ጾመ ፍልሰታ ሱባዔ ሲጠናቀቅ በልጇ ፈቃድ የሰላም ዕንቅልፍ እንዳንቀላፉ ያለ ምንም ጻዕር ከዚህ ዓለም ወደ ዘለዓለም ሕይወት ተሸጋግረዋል። ከማረፋቸው ሦስት ቀናት በፊትም በተለየ የተመስጦ ራእይ ውስጥ ሆነው ብዙ ምስጢር ያላቸው ቃላት የተናገሩ ሲሆን፤ ከነዚህ ውስጥም፤ «የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በመወከል ወደ ግብጽ ቤተ ክርስቲያን ሄደህ እንድታስተምር ተብዬ ተጠርቼአለሁና ልብሴን ስጡኝ፤ ከመንበረ ማርቆስ የወርቅ ሰዓትና የወርቅ ሣህን ተሸለምኩ፤ የተሸለምኩትን የወርቅ ሰዓት ስጡኝ፤» የሚሉ ይገኙባቸዋል።

የክቡር አባታችን የቀብር ሥነ ሥርዐት ነሐሴ ፲፯ ቀን ፲፱፻፱፺፱ ዓመተ ምሕረት ብዙ ዘመን ባገለገሉበት የአዲስ አበባው ደብረ አሚን ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን በዙ ሕዝብ በተገኘበት ተፈጽሟል። የዕረፍታቸው ፵ኛ ቀን መታሰቢያም መስከረም ፲፯ ቀን ፳፻ ዓመተ ምሕረት በጸሎት ታስቦ ውሏል።

ስለ ክቡር አባታችን አለቃ አያሌው ታምሩ ከብዙ በጥቂቱ፥ ከረጅሙ ባጭሩ ለመጥቀስ ሞከርን እንጂ የእሳቸው ትምህርት በብዙ ኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ የተጻፈ መሆኑ እሙን ነው። ትጉሁ የወንጌል ገበሬ አባታችን አባታቸው ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ እንደ ተናገረው ለእግዚአብሔር ኖረው ለእግዚአብሔር የሞቱ፤ ደም አልባ ሰማዕትነትን የተቀበሉ አባት ናቸው። ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለ፤ «እኔ በሕይወት ብኖር ክርስቶስን ለማገልገል ነው፤ ብሞትም ዋጋ አለኝ።» (ፊልጵ፤ ፩፥ ፳፩።)

አምላካችን እግዚአብሔር ለአባታችን አለቃ አያሌው ታምሩ (አቡነ ወልደ ጊዮርጊስ) በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ዕረፍተ መንግሥተ ሰማያትን ያድልልን። ለባለ ቤታቸው፥ ለልጆቻቸው፥ ለልጅ ልጆቻቸው፥ በመንፈሳዊ ዕውቀት ኰትኲተው ላሳደጓቸው፤ እንዲሁም ለሚወዳቸውና ለሚያፈቅራቸው የኢትዮጵያ ሕዝበ ክርስቲያን መጽናናቱን ይስጥልን።

ክብር ምስጋና ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ፤ እንዲሁም ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም ይሁን። አሜን።

ለክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ የመንፈቅ መታሰቢያነት የተዘጋጀውን መጽሔት እዚህ ጋር ያውርዱ።

የክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ የመንፈቅ መታሰቢያ። (.zip)(28.3 MB)

 

ተጨማሪ ገጾች
 ዜናዎች
 አስተያየቶትን ይጻፉልን
 የ aleqayalewtamiru.org አባል ይሁኑ
ይህንን ገጽ ለወዳጆችዎ ያሳውቁ።
የኒውስሌተራችን ተጠቃሚ ይሁኑ
በየጊዜው የሚደረጉ ለውጦችን ለማወቅ ይመዝገቡ።
ሙሉ ስም
የኢሜይል አድራሻ
መውረድ የሚችሉ ፋይሎች
የክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ የመንፈቅ መታሰቢያ። (.zip, 28.3 MB)
የክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ የመንፈቅ መታሰቢያ። (light weight) (.zip, 2.4 MB)
Unable to read the text?
Download Font (nyala.ttf, 427KB)
For PC users: download and save the font file in "C:\Windows\Fonts" folder and restart your browser
(Nyala.ttf, © 2006 Microsoft Corporation. All Rights Reserved. Nyala is either a registered trademark or a trademark of Microsoft Corporation in the United States and/or other countries.)
መግቢያየሕይወት ታሪክመጻሕፍትየድምፅ ማኅደርቃለ ውግዘትግምጃ ቤት
Copyright  , aleqayalewtamiru.org