ልጆች ሆይ ታዘዙ ለወላጆቻችሁ፤
ከልዑል እግዚአብሔር እንደ ታዘዛችሁ።
ለወላጅ መታዘዝ በታማኝ ልጅነት፤
ደግ ነው መልካም ነው ጠቃሚ ነው በውነት።
ሀብትና በረከት እንዲገባልህ፤
ዕድሜም በምድር ላይ እንዲበዛልህ፤
አባት እናትህን አክብር የሚለው፤
በኦሪቱ ትእዛዝ የታወቀ ነው።
አባቶች ልጆችን አታባልጓቸው፤
ሠርታችሁ ቀጥታችሁ አሳድጓቸው።
ለሰው ይምሰል ሳይሆን በውነቱ ጎዳና፤
መሪና ተመሪ የግዜር ናቸውና፤
ቤተ ሰቦች ሁሉ እግዜርን ፈርታችሁ፤
ታዘዙ ተገዙ ለሚአሳድሩአችሁ።
ጌቶችም አድምጡ ቃሌን ልንገራችሁ፤
በናንተ ላይ ጌታ መኖሩን ዐውቃችሁ፤
አድልዎ ንፍገትን ቁጣን ሳትጨምሩ፤
ለቤተ ሰባችሁ በትክክል ሥሩ።
ጌታም ሆነ ሎሌ በጎ አድራጊ ሰው፤
ከልዑል እግዚአብሔር ታላቅ ዋጋ አለው።