መግቢያየሕይወት ታሪክመጻሕፍትየድምፅ ማኅደርቃለ ውግዘትግምጃ ቤት
 


የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለፓፓ ፒየስ ፲፪ኛ የቅድስና መዓርግ ለመስጠት ማሰቧን በመቃወም የቀረበ መግለጫ።

የተወደዳችሁ ምእመናን! የቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንዳስቀመጠው የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን በሃይማኖት ከኦርቶዶክሳውያን አብያተ ክርስቲያን ከተለየችበት ጊዜ አንሥቶ የሮማን የቄሣር መንግሥት ጉልበት በማድረግ ካቶሊካውያን ያልሆኑ ክርስቲያኖችን በተለያዩ አሠቃቂ መንገዶች ከማጥቃት የቦዘነችበት ጊዜ የለም። ይልቁንም የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን። ይህም ግብሯ በዐፄ ሱስንዮስ ጊዜ በነበረው የሃይማኖት ጦርነት፥ ኋላም በዐድዋ ጦርነትና በ፭ቱ ዓመት የፋሺስት ጦርነት ጊዜ የታየና በታሪክ የተመዘገበ ነው። እነዚህ ጦርነቶች ሁሉ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን አወንታና ቡራኬ ያገኙ ነበሩ። ይልቁንም በ፲፱፻፳፰ ዓ. ም. የኢጣሊያ ጦር በፋሺስቱ መሪ በቤኒቶ ሙሶሊኒ አዛዥነት ኢትዮጵያን ለመውረር በተንቀሳቀሰ ጊዜ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲንያና በጊዜው የነበሩት ፓፓዋ ፒየስ ፲፪ኛ ጦርነቱ የተቀደሰ መሆኑን በመጥቀስ ሠራዊቱን መባረካቸውና የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳትና ካህናትም የተለያየ ልገሣ ለፋሺስት ጦር ማድረጋቸውን ታሪክ መዝግቦታል።

የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ኢትዮጵያን እጅ ለማድረግ ባደረገችው የረጅም ጊዜ ትግል ይልቁንም ከ፲፱፻፳፰ ዓ. ም. - ፲፱፻፴፫ ዓ. ም. ከሙሶሊኒ ጋር ተባብራ በጥቁር ሸሚዝ ለባሽ ፋሺስት ጦረኛዋ የፈጸመችው ግፍ፥ በተከለከለ የመርዝ ጋዝና የአውሮፕላን ድብደባ የኢትዮጵያን ሕዝብ በመጨረስ ያሳየችው ጎምዛዛና መራር አድራጎት እንኳን ለኢትዮጵያውያን ለባዕዳን ሕሊና የሚሰቀጥጥ እንደ ነበር ታሪክ መዝግቦታል።

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ የታሪክ ጸሓፊዎችና ተመራማሪዎች ብዙ የጻፉ ሲሆን አባታችን አለቃ አያሌው ታምሩም በተለያዩ መጻሕፍቶቻቸውና በተለያዩ አጋጣሚዎች ባስተላለፏቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች አማካይነት ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ገለጻ አቅርበዋል። ለምሳሌ ያህል መስከረም ፲፩ ቀን ፲፱፻፹፱ ዓ. ም. በወጣው ማዕበል አማካይነት፤ «ታሪክ ይናገራል፤ መልስም ይጠብቃል፤» በሚል ርእስ ያቀረቡትን ጽሑፍ ከዚህ ማየት ይቻላል።

ይህ በንዲህ እንዳለ በቅርቡ የአሁኑ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፓፓ ቤኔዲክት ፲፮ኛ፤ በ፪ኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ለነበሩት ፓፓ ፒየስ ፲፪ኛ የቅድስና መዓርግ ሊሰጧቸው መሆኑ ተሰምቷል። (Pope John Paul II and Pius XII move closer to sainthood – BBC News, Vatican defends move to beatify wartime pope – MSNBC)

ከላይ እንደ ተጠቀሰው ፓፓ ፒየስ ፲፪ኛ በ፲፱፻፳፰ ዓ. ም. የፋሺስት ጦር ኢትዮጵያን ለመውረር በተንቀሳቀሰበት ጊዜ ጦርነቱ የተቀደሰ ነው በማለት በሰጡት ቡራኬ መሠረት፤ በ፭ቱ ዓመት ተጋድሎ የኢጣሊያ ጦር ባደረገው ጭፍጨፋ የካቲት ፲፪ ቀን ፲፱፻፳፱ ዓ. ም. በአዲስ አበባ ከተማ በተደረገው ጭፍጨፋ ብቻ ከሦስት መቶ ሺሕ በላይ ኢትዮጵያውያን ማለቅ፤ በተጨማሪም በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በሕዝብ ላይ የደረሰው ጭፍጨፋ፥ በተለያዩ የኢትዮጵያ ገዳማት በደብረ ሊባኖስ፥ በዲማ፥ በዋልድባ፥ እንዲሁም በተለያዩ የኢትዮጵያ ገዳማት በሚገኙ መነኮሳት ላይ የደረሰው ጭፍጨፋ፥ የታላላቆቹ አባቶች የአቡነ ጴጥሮስና የአቡነ ሚካኤል መሥዋዕትነት፥ እነ ራስ ደስታ ዳምጠውን የመሳሰሉ የነጻነት ዐርበኞች መሥዋዕትነት ፤ የአብያተ ክርስቲያን መቃጠል፥ የንዋየ ቅድሳት ምዝበራና ዘረፋ በታሪክ መዛግብት ተመዝግቦ የፋሺትን ጨካኝነት፥ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንንና የፓፓዋን ለተቀደሰው የሰው ልጆች ሕይወት ያላቸውን ደንታ ቢስነት እየመሰከረ እያለ እንደገና አሁን፤ ግፈኛውን የፋሺስት ጦር፤ «የምታካሂደው የተቀደሰ ጦርነት ነውና ግፋ ቀጥል፤» በማለት ቡራኬ የሰጡትን ፓፓ ፒየስ ፲፪ኛ «ቅዱስ» ብሎ መጥራት የሰውን ልጅ ክብር ማዋረድ ከመሆኑም በላይ የክርስትናን ሃይማኖት የሚጻረር በመሆኑ፤ ይህን ዐሳብ የኢትዮጵያንና የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ክብርና ነጻነት ለመጠበቅ በተደረጉ ተጋድሎዎች አጥንታቸውን በከሰከሱ፥ ደማቸውን ባፈሰሱ ኢትዮጵያውያን ስምና በኢትዮጵያ አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም በጥብቅ የምንቃወም መሆኑን እንገልጻለን። ስለሆነም ፓፓ ቤኔዲክት ፲፮ኛ ለፓፓ ፒየስ ፲፪ኛ የቅድስና መዓርግ ለመስጠት ያሰቡትን ዐሳብ እንዲሰርዙ እንጠይቃለን። እንዲሁም ይህንን የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ዐሳብ በመቃወም በተለያዩ አቅጣጫዎች በመሰለፍ ድምፃቸውን በማሰማት ላይ ላሉ ወገኞች ያለንን አጋርነት እንገልጻለን።

አምላካችን አገራችንን ኢትዮጵያን ይጠብቅልን፤ አሜን።

 

ተጨማሪ ገጾች
 ዜናዎች
 አስተያየቶትን ይጻፉልን
 የ aleqayalewtamiru.org አባል ይሁኑ
ይህንን ገጽ ለወዳጆችዎ ያሳውቁ።
የኒውስሌተራችን ተጠቃሚ ይሁኑ
በየጊዜው የሚደረጉ ለውጦችን ለማወቅ ይመዝገቡ።
ሙሉ ሥም
የኢሜይል አድራሻ
መውረድ የሚችሉ ፋይሎች
የክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ የመንፈቅ መታሰቢያ። (.zip, 28.3 MB)
የክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ የመንፈቅ መታሰቢያ። (light weight) (.zip, 2.4 MB)
Unable to read the text?
Download Font (nyala.ttf, 427KB)
For PC users: download and save the font file in "C:\Windows\Fonts" folder and restart your browser
(Nyala.ttf, © 2006 Microsoft Corporation. All Rights Reserved. Nyala is either a registered trademark or a trademark of Microsoft Corporation in the United States and/or other countries.)
 
መግቢያየሕይወት ታሪክመጻሕፍትየድምፅ ማኅደርቃለ ውግዘትግምጃ ቤት
Copyright  , aleqayalewtamiru.org