«ኢትዮጵያ እርስዎ ለሚመልኩት አምላክ ጸሎት ልታሳርግ አትችልም። ሌላው ዓለም እንደዚሁ ወደ እርስዎ አምላክ ሊጸልይ አይችልም። እርስዎ ከእግዚአብሔር ይልቅ ለሰውየው ለሙሶሊኒ የሚገዙ ሆነዋልና።»
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን። ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠቅላላ ምእመናንና አባሎች እንደገና፥ ደግሞ እንደገና፥ አሁንም እንደገና አቤት እላለሁ። ጩኸቴ በውሃ ውስጥ እንደሚናገር ሰው ሰሚ ማጣቱ፥ ሁሉም ዝም ማለቱ አቤቱታዬን አይገታውም። ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውድቀት፥ ክብሯ ስለ መገሠሡ፥ ትምህርተ ሃይማኖቷ ስለ መፋለሱ፥ ነባር ሕንጻ ታሪኳ ስለ መፍረሱ፥ ሕጓ፥ ሥርዓቷ ስለ መጣሱ፥ ሰማንያ አሐዱ መጻሕፍቶቿ ስለ መደምስሳቸው፥ ፓትርያርኳና ጳጳሳቶቿ፥ የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎችና ካህናት ተባብረው በላይዋ ስለ ማመፃቸው፥ ምእመናንና ሊቃውንት መናገር የሚገባቸው ሁሉም እየሰሙ እንዳልሰሙ፥ እያዩ እንዳላዩ ዝም በማለታቸው አሁንም እንደገና አቤቱታዬን አሰማሁ።
«አፉሁ ለጻድቅ ይትሜሃር ጥበበ ወልሳኑ ይነብብ ጽድቀ።» «የጻድቅ ሰው አንደበቱ ጥበብን ይማራል፤ መላሱም እውነትን ይናገራል።» ስለ እግዚአብሔር ክብር እውነቱን፥ እውነተኛውን መናገር በሚያስፈልግበት ጊዜ ዝም ማለት እግዚአብሔርን ያሳዝናል። ጌታችን አምላካችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ሆሣዕና ወደ ቤተ መቅደስ በገባ ጊዜ ሕፃናት ሲያመሰግኑት የካህናት አለቆች ተቆጡ። ጌታም፤ «እነዚህ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮሃሉ፤» የሚል መልስ ሰጥቷቸዋል። (ሉቃ. ፲፱፥ ፵።) አዎ። ስለ እግዚአብሔር ክብር ሊናገሩ፥ ሊመሰክሩ የሚገባቸው በጊዜው እምቢ ካሉ ድንጋዮች ወይም ሌሎች ፍጥረታት ይናገራሉ። የሞዐብን ሰው በለአምን የተቀመጠባት አህያ ገሥፃዋለች። ስለ እግዚአብሔር ክብር መናገር፥ መመስከር የማይገባው፥ ከዚህ ጸጋ የሚከለከል በአንደበቱ እውነት የማይገኝበት የሐሰት አባት ሰይጣን ብቻ ነው። ጌታችን ወንጌልን ሲያስተምር በነበረበት ወቅት በሰንበት ቀን ወደ ምኩራብ ገብቶ ሳለ በስፍራው ጋኔን የያዘው ሰው ስለ ነበር በሰውየው ላይ ያደረው ጋኔን ስለ ጌታ ሊመሰክር ሊጀምር ጌታ፤ «ዝም በልና ውጣ፤» ብሎ እንደ ገሠፀው በወንጌል ተጽፏል። እንግዲህ ሊናገሩ የሚገባቸው ዝም ቢሉ ወይም ሊናገሩ የሚገባቸውን የሚከለክሉ ቢኖሩ ሁለቱም የሚገባቸውን አላደረጉም ማለት ነው። ግን የእግዚአብሔርን ክብር እንዳይናገሩ የሚከለከሉ ሰይጣናት መሆናቸውን ልናውቅ ይገባል። (ማር. ፩፥ ፳፫ - ፳፯። ያለውን መመልከት ይጠቅማል።) ሰው ግን የእግዚአብሔርን ክብሩን ሊወርስ፥ ስሙን ሊቀድስ የተፈጠረ ስለ ሆነ በእግዚአብሔር ላይ ራሱን ሊወዘውዝ፥ ምላሱን ሊያስረዝም፥ ትከሻውን ሊያሳይ፥ ስለ እግዚአብሔር ስም ሊናገር፥ ሊመሰክር ሲገባው፥ ሲቻለውም ሊያፍርበትና ዝም ሊል አይገባም።
የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ለመግዛት የሚመኙ ቢኖሩም ዕድሉ የገጠማት ግብጽና ዕድሉ እየራቃት በትግል ላይ የምትኖረው የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ተፈትነዋል ማለት ይቻላል። ሆኖም ከቀንበር ወደ ቀንበር እየተዛወረች የምትኖረው የግብጽ ቤተ ክርስቲያንም ብትሆን በኢትዮጵያ ላይ ለረጅም ጊዜ ሥልጣን ይዛ የመኖሯን ያህል ለኢትዮጵያ ምእመናን ያሳየችውና የምታሳየው ፍቅር እጅግ በጣም አነስተኛ ነው። እንዲያውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኢየሩሳሌም ባላት ይዞታ ላይ የግብጽ ቤተ ክርስቲያን በባለ አደራነት ገብታ ራሷ ቀማኛ ሆና ከመገኘቷም በላይ ለሌሎች ከመስጠት ዐልፋ በቀሪው አነስተኛ ይዞታ ላይ የፈጠረችው ተንኮል እስከ አሁንም መዘዙ ያላለቀ በመሆኑ የሁለቱ እኅትማማች አብያተ ክርስቲያናት ግንኙነት ባሳዛኝ ሁኔታ ላይ ይገኛል። ነገሩ ከውሥጥም ከውጭም ብዙ ግፊት ያለው ቢሆንም በ፲፱፻፴፯ ዓ.ም. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተሰይሞ የነበረው መንፈሳዊ ጉባኤም ከግብጽ ጋር የነበረው ግንኙነት ፍጻሜ አግኝቶ፤ «የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በራሷ ልጆች እንድትመራ ያስፈልጋል፤» ወደሚለው ፍጻሜ ለመድረስ ያስገደደው ይህ ከዚህ በላይ የጠቀስነው ሁኔታ ነበር አንጂ በግብጽ ላይ በሌሎች ምክንያት ያጣችውን የገዢነት ሥልጣን በኢትዮጵያ ላይ እንድታስፋፋ በሰባኪዎቿ፥ በመልእክተኞቿ፥ ከዚያም ዐልፎ በጦረኞቿ ስትታገል ለኖረችው ለሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አመቻችቶ ለመስጠት አልነበረም። የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ኢትዮጵያን እጅ ለማድረግ ባደረገችው የረጅም ጊዜ ትግል ይልቁንም ከ፲፱፻፳፰ ዓ. ም. - ፲፱፻፴፫ ዓ. ም. ከሙሶሊኒ ጋር ተባብራ በጥቁር ሸሚዝ ለባሽ ፋሺስት ጦረኛዋ የፈጸመችው ግፍ፥ በተከለከለ የመርዝ ጋዝና የአውሮፕላን ድብደባ የኢትዮጵያን ሕዝብ በመጨረስ ያሳየችው ጎምዛዛና መራር አድራጎት እንኳን ለኢትዮጵያውያን ለባዕዳን ሕሊና የሚሰቀጥጥ እንደ ነበር ታሪክ መዝግቦታል።
በጊዜው ያልነበረ ሊያውቀው ሊረዳው አይችል ይሆናል። እኔ ግን በጊዜው በልጅነት ዕድሜዬ የነበርኩባት አገሬ ዲማ ጊዮርጊስ በአውሮፕላን ከዐርባ ቀን በላይ ስትደበደብ ከላይ የአውሮፕላን ከታች የመድፍ፥ የመትረየስ ድምፅ ምድሪቱን ሲያንቀጠቅጣት በነበረ ጊዜ ከዚያው ስለ ነበርኩ አሁንም ትዝታው ያስጨንቀኛል። ይልቁንም በ፲፱፻፴፩ ዓ. ም. ነሐሴ ፲፪ ቀን እኔና የልጅነት ዕድሜ ጓደኞቼ ከቤተ ክርስቲያን ውሥጥ በቅሎ ባደገው ሣር እየተሳሰርን ስንጫወት አቶ አየለ ኀይሉ የተባሉ ምእመን ቤተ ክርስቲያን ለመሳለም መጥተው እኛ ከምንጫወትበት ዘንድ ሰፊ ድንጋይ ስለ ነበር የሣሩን ጤዛና የመሬቱን ጭቃ ሸሽተው ዘንጋቸውን ተመርኩዘው ከድንጋዩ ላይ ቆመው ዳዊት ይደግሙ ነበር። እኛ በጨዋታችን ላይ በጤዛው እየተነከርን፥ በጭቃው እየተለወስን ስንጫወትና ስናስቸግራቸው አንዳንድ ጊዜ ጸሎታቸውን እያቋረጡ ይገሥፁን ነበር። እኛ ግን ጨዋታችንን ስለ ቀጠልን ሁለቱ ጓደኞቼ ሰውየው ከቆሙበት ድንጋይ ሥር ጥለው እንደ ብራና ወጥረው ከግራና ከቀኝ ሣሩን እያስተላለፉ አሰሩኝ። እጆቼን ግራና ቀኝ ዘርግተው በጀርባዬ አንጋለው እግሮቼን ገጥመው በቁመት አምስት ላይ ሁለቱን እጆቼን ጨምሮ በጠቅላላው ከሰባት ላይ አስረው ጥለውኝ ሄዱ። እኔም ያንን ሁሉ ለመፍታትም ሆነ ለመቁረጥ ዐቅም አልነበረኝም። ሰውየው ወደ ጸሎታቸው እንጂ ወደ እኔ አልተመለሱም። ጊዜው ከቀኑ ፫ ሰዓት ይሆናል። የክረምት ፀሐይ ብልጭ ብላለች። እኔንም ለጨዋታና ለድንጋጤ የጋበዘችኝ እሷው ነበረች። የፍልሰታ ቤተ ክርስቲያን ሳሚ ሕዝብ እንዲሁም በዕለቱ አንድ ሰው ሞቶ ነበርና ከሩቅም ከቅርብም የመጣው ሕዝብ በቤተ ክርስቲያኑ ግቢ ሙሉ ነበር። አቶ አየለ ኀይሉም ነጭ ልብሳቸውን ለብሰው ዘንጋቸውን ተመርኩዘው ከድንጋያቸው ላይ ቆመው ዳዊታቸውን ይደግሙ ነበር። ከአፍ የወደቀች ጥሬ የምታህለው ሕፃን አያሌው ታምሩም በበቀለው እንግጫ፥ ሙርጅና አክርማ ከመሬት ጋር ተጣብቃ ታስራ እንደ ቅሪላ ትለፋ ነበር። በድንገት የሚያስገመግም ድምፅ ተሰማ። የጣሊያን ቦምብ ጣይ አውሮፕላን ነበር። ሕዝቡም አልጠረጠረውም ነበር። እንደ ደረሰም ነጭ ልብስ ለብሰው በቆሙት ዳዊት ደጋሚ ላይና ከእግራቸው ሥር በበቀለው ሣር ታስራና ተጠፍራ፥ እንደ ብራና ተወጥራ ከመሬት ላይ ተለጥፋና ተዘርግታ በነበረችው ሕፃን አያሌው ታምሩ ላይ ቦምቡን አዘነበው። ኀይሉም አየለ ኀይሉን ከቆሙበት አንሥቶ ከቤተ ክርስቲያኑ ዕቃ ቤት ግቢ ውሥጥ ሲጥላቸው ድንጋዩም ተፈንቅሎ ተከተሏቸው ሄዶ ከዕቃ ቤቱ ግቢ በር ላይ ወደቀ። የአካባቢውም መሬት ተገለባበጠ። ተስፋ የለሽ አያሌውም በሊቀ መላእክት በቅዱስ ሚካኤል በሰማዕቱ በቅዱስ ጊዮርጊስ ይልቁንም አምላክን በወለደች በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ቸር እግዚአብሔር ባደረገላት ተአምራት ከሞት ተርፋ በመሬቱ መገለባበጥ ከእስራቷ ተፈታ በቀኝ እጇ የታሰረችበትን ሣር ግን ከነጉሊቱ ተሸክማ ከወደቀችበት ተነሥታ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብታ ተጠለለች። አየለ ኀይሉ ሞቱ። አያሌው በአስደናቂ ተአምራት ከሞት ዳነች።
ያቺ ሕፃን ናት ከታሪክ ጋር ቆማ ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፥ ስለ ምእመናኖቿ የሮማን ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የምትሟገት፤ አባ ጳውሎስንም ከሮም ጋር በመተባበር በፈጸሙት ደባ የምትከስ፥ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት፥ ሊቃውንት ለቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎችና ካህናት፥ ለሰበካ ጉባኤ አባላትና ለምእመናን በጠቅላላውም ለኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎችና ካህናት፥ ለሰበካ ጉባኤ አባላትና ለምእመናን፥ በጠቅላላውም ለኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባሎች ልጆችና አባቶች አቤቱታዋን ባለ ማቋረጥ የምታቀርበው ያን ጊዜ በተአምራት ከሞት የተረፈችው ሕፃን ናት። ዛሬም የእግዚአብሔር የተአምራት ምርኮኛው አለቃ አያሌው ታምሩ ነኝ። የእኔን ከነገርኳችሁ በሌላ በኩል የተመዘገበውን ታሪክ ደግሞ ላሳያችሁ በሚከተለው ተመልከቱ።
«ከዚህ ላይ ለቤተ ክርስቲያን ታሪክ አስከፊና አሳፋሪ ሁኖ የሚታየው የኢትዮጵያን ሕዝብ ለመደምሰስ ቫቲካን ከሙሶሊኒ ጋር መተባበሩ ነው። እንዲያውም ከሙሶሊኒ ጎን ተሰልፈው ምክር ይሰጡ የነበሩና ብዙ ካህናትንም ያስፈጁ የወታደር ልብስ ለብሰው የመጡ የሮማ ካቶሊክ ቄሶች ናቸው ይባላል። ፓፓውም የተቀደሰ ዘመቻ ነው ብለው መድፉንና ታንኩን ባርከዋል። በዚህ ሁሉ ድርጊታቸውም በዓለም ክርስቲያኖች ዘንድ ተነቅፈውበታል።
ከብዙዎቹም መካከል ኤሊክ ሲንድሩም የሚባሉት የስዊድን ጋዜጠኛ ፓፓውን እንዴት እንደ ወቀሷቸው (ሲሞን ረስቲን የተረጎመውን) ከዚህ ቀጥለን እናቀርባለን።
«ቅዱስ ሆይ፤ እኔ በሰሜን አገር የተወለድሁ አንድ ፕሮቴስታንት ነኝ። ባገራችንም በስዊድን በግንባራችን የምንደፋው በእልፍኛችን ሁነን ከእግዚአብሔር ከአምላካችን ጋር ስንናገር ነው እንጂ ከሰው ጋር ብንናገር ቁመን እንነጋገራለንና በእግርዎ ላይ ወድቄ ጫማዎን ስለማልስምዎ አይቆጡብኝ። ቅዱስ ሆይ፤ እኔ አንድ ምስኪን ኃጢአተኛ፤ እርስዎ ግን የመድኀኒታችን ምትክ የማይሳሳቱም ኖት፤ ይሁን እንጂ እኔ እነቅፍዎታለሁ። እርስዎ የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ዋና ነዎት፤ ካቶሊካዊት ማለትም የሁሉም ማለት ነው። ዛሬ እንግዲህ የርስዎ ቤተ ክርስቲያን በእውነት የሁሉ ቤተ ክርስቲያን ናት? እርስዎ ከሙሶሊኒ ጋር ሆነው ከሌላው ዓለም ጋር በጠብ አሉ። እርስዎና ከርስዎ በታች ያሉት ሌሎችም ጳጳሳት ኢትዮጵያ ለኢጣሊያ ቅኝ አገር እንድትሆን የሚገባ ነው ብለው ተናገሩ። እርስዎ መቼም የሐዋርያው የጴጥሮስ ተከታይ ነዎትና አይሳሳቱም። እንግዲህ ሌላው ዓለም ሁሉ ቃልዎን ሳይሰማ በኢጣልያ ላይ «ሳንክሲዮ» ቢያደርግ መሳሳቱ ነው? ቅዱስ ሆይ፤ ኢጣሊያ የፍርድ ሥራ ትሠራለች ብለው ሰብከዋል። የመሲና የቢረንዲቤም ጳጳሳት ወርቃቸውን ሁሉ ለጦርነቱ ኪሳራ እንደ ሰጡ ሰማን። እናንተ ጳጳሳት ይህንን ስታደርጉ እግዚአብሔር ከኢጣሊያ ጋር ነው የማለት ያህል ይመስለኛል። እንግዲህ ሌላው ዓለም ሁሉ የኢጣሊያን ሥራ ቢቃወም የእግዚአብሔርን ፍርድ ይቃወም ይሆን? ኢትዮጵያስ አገራቸውን ሲጠብቁ በእግዚአብሔር ላይ ተነሥተው ይህንን እርስዎ እንዳሉ ኢጣሊያ የጽድቅ ውጊያ የምትዋጋ ከሆነ ሌላውም ዓለም ይህንን የጽድቅ ጦርነት ቢቃወም መቼም ከእናንተ በቀር ሌላው ዓለም ሁሉ እግዚአብሔርን የካደ ይመስላል። እንግዲህ እርስዎ እንደሚሉት እግዚአብሔር አምላካችን የኢጣሊያ መንግሥት ቃሉን ሊያፈርስ፥ መሐላውንም ሊሰብር ፈቅዷል። እርስዎ እንደሚሉት የኢትዮጵያ ሰዎች አገራቸውን ለመጠበቅ ቢሰበሰቡ የኢጣሊያ አውሮፕላን ጥርግ አድርጎ ቢያጠፋቸው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ ነው። ሴቶችንና ሕፃናትን በቦምብ ሲያጠፉ እግዚአብሔርን ያገለግላሉ። ይህንን ሁሉ ካሁን በፊት በመጽሐፍ ቅዱስ አላገኘንም ነበርና እርስዎ አሁን ስላስተማሩን ትልቅ ነገር ነው። ይህንን ሁሉ የምታስተምረን ቅድስቲቱ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ናት። በዱሮ ዘመን ግን ቤተ ክርስቲያን ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር መታዘዝ ይገባል ብላ ታስተምር ነበር። ቅዱስ ሆይ፤ የእርስዎ ቤተ ክርስቲያን ቅድስት አይደለችም፤ የሁሉም አይደለችም። እግዚአብሔር መሐላን ማፍረስ ይወዳል ብለው ቢያስተምሩን ውሸትዎን ነው ብለን እንመልስልዎታለን። እርስዎም የዓለም ሁሉ አባት ነኝ ሲሉ የሙሶሊኒ ባርያ ሁነዋል። በኢጣሊያ ላይ ሥጋዊ «ሳንክሲዮ» ማድረግ የግድ ነው። እርስዎ የሚያመልኩት አምላክ ጣዖት ነው እንጂ አምላክ አይደለም። ኢትዮጵያ እርስዎ ለሚያመልኩት አምላክ ጸሎት ልታሳርግ አትችልም። ሌላው ዓለም እንደዚሁ ወደ እርስዎ አምላክ ሊጸልይ አይችልም። እርስዎ ከእግዚአብሔር ይልቅ ለሰውየው ለሙሶሊኒ የሚታዘዙ ሆነዋልና። እርስዎ መናገር በተገባዎ ጊዜ ዝም አሉ፤ ዝም ማለት በተገባዎ ጊዜ ተናገሩ። አሁንም ከሌሎች ጳጳሳት ጋር የሙሶሊኒን ጫማ ስመዋል። የዓለምን ሰላም የሚያውከውን ወንበዴውን ቢያወግዙት ኖሮ ለቤተ ክርስቲያንዎ እንዴት ያለ ጥቅም በሆነ ነበር። ምናልባት እርስዎም በታሰሩ ነበር። ምናልባትም እንደ ድሮ ዘመን ክርስቲያኖች ወደ ሰማዕትነት ሞት በደረሱ ነበር። ዓለም ሁሉ ከርስዎ ጋር በሆነ ነበር። ክርስቲያን ቢሆን አረመኔም ቢሆን ሰው ሁሉ እርስዎ የእግዚአብሔር አገልጋ እንደ ሆኑ በተረዳ ነበር። አሁንም በቅርብ የገና በዓል ነው። ለግፍ ጦርነት ወርቃቸውን የሰጡ ጳጳሳትም እንግዲህ ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን በምድር ላይ ሰላም ይሁን ለሰውም በጎ ፈቃድ ይሁን ብለው ሊዘምሩ ናቸው። ይህንንም ሲዘምሩ በደረታቸው የወርቅ መስቀል ሳያደርጉ አይቀርም። ነገር ግን በጀርባቸው ላይ የእንጨት መስቀል ቢሸከሙ ይሻል ነበር። ቅዱስ ሆይ፤ በዓሉን ያሳምርልዎ ብዬ ምኞቴን እገልጻለሁ።» ይህ የጭካኔ ድርጊት በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል እንደ ትልቅ ገደል ሆኖ ይኖራል።»
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፥ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት፥ ክቡራን ሊቃውንት፥ የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎችና የሰበካ ጉባኤ አባላት፥ ቀሳውስት፥ ዲያቆናት መምህራንና ደቀ መዛሙርት፥ የተወደዳችሁ ምእመናን! መላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባሎች አባቶችና ልጆች! ከዚህ በላይ የተጻፈውን ታሪክ ተመልክታችሁ ታሪክ እየተናገረ ስለ ሆነ ሁላችሁም በየራሳችሁ መልስ እንድትሰጡት ትጠየቃላችሁ። ፋሺስቶች በኢትየጵያ ላይ ምን ምን እንደ ፈጸሙ በኢትዮጵያ ያለ ሰው ብቻ ሳይሆን እንስሳው፥ አውሬው፥ ወፉ፥ አሞራው፥ እንጨቱ፥ ድንጋዩ፥ ሣሩ፥ ቅጠሉ፥ ቆላ፥ ደጋው፥ ተራራው፥ ኮረብታው፥ ሜዳው ጎድጓዳው የሚመሰክረው ነው። የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አፍአውያንና ውሣጣውያን ጦረኞቿን አስታጥቃና አሰልፋ በኢትዮጵያ ላይ ሥውርና ግልጥ ጦርነት ማድረግ ከጀመረችበት ጊዜ ጀምሮ የፈጸመችውንና ታሪክ የመዘገበውን ሁሉ በዚህ ጠባብ ዐምድና ጊዜ መግለጥ ባይቻልም በፋሺስቶች ጊዜ የተፈጸመውን ስዊድናዊው ጸሐፊ ከተመለከቱት፥ ከገመገሙት፥ ከመዘኑት ሁኔታ የተነሣ፤ «እርስዎ ለሚያመልኩት አምላክ ኢትዮጵያ ጸሎት አታሳርግም፤ መላው ዓለምም ጸሎት አያሳርግም። እርስዎ የሚያመልኩት አምላክ ጣዖት ነው፤» ከማለታቸውም በላይ፤ «ይህ የጭካኔ ድርጊት በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል እንደ ትልቅ ገደል ሁኖ ይኖራል፤» ብለዋል። አስደናቂ ነው። ቁንጥጫው ያልደረሰባቸው፥ በኢትዮጵያ ላይ የተፈጸመው ግፍ እጅግ ያስጨነቃቸው ሰዎች ይህን ያህል የሚናገሩ ከሆነ ኢትዮጵያውያን ለሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ቤተሰብ መሆናቸው፥ ቤተሰብ ለመሆን መጣራቸው፥ ለስሟ ለክብሯ ሽንጣቸውን ገትረው መቆማቸው፥ መሟገታቸው፥ እናታቸውን ኢትዮጵያንም በሷ ፍቅር መለወጣቸው፥ በኢትዮጵያና በሷ መሐከል የኖረውን ታላቅ ገደል ማን በምን ቆፍሮና ደልድሎ አስተካክሎት ነው? ያንንስ በመካከላቸው በኢትዮጵያውያን ዐጽምና ደም የታነጸውን ሰማይ ጠቀስ ግንብ ማን ንዶ ከመንገድ አስለቅቆት ነው? ያ ግንብ እኮ የባቢሎን ግንብ አይደለም። ዛሬም ነገም የሚኖር፥ ምን ጊዜም የማይናድ ግንብ ነው። ተሰዓቱ ቅዱሳን አበው የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ጥርስ ሸሽተው በእግዚአብሔር ስምና ሥልጣን በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ወደምትታደጋቸውና ወደምትጠብቃቸው ወደ ኢትዮጵያ ገቡ። ሁሉም ገድላቸውን ጨርሰው በሰላም ወደሚፈልጉት አዲስ ሕይወት ገቡ። በሥዋሬ ያሉም አሉ፤ ወደ ሌላ ዓለም ያለፉም አሉ።
ዛሬ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ አክሊለ ክብራቸውን ተሸክመው ለሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ያለ ጦርነት ተማርከው እጃቸውን ሲሰጡ፥ በተራ ምእመን ደረጃ ከካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን እግረ መንበር ሥር ተቀምጠው የልዮንን ተወካይ ቡራኬ ሲቀበሉ እነ አቡነ ገሪማ፥ እነ አቡነ አረጋዊ ተሰዓቱ ቅዱሳን አበው በጠቅላላው፥ የገዳማተ ትግሬ ቅዱሳን፥ የመላዋም ኢትዮጵያ አበው አይታዘቧቸው ይሆን? መቼም በምድር ላይ የክርስቶስ እንደራሴ ለተባለው የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ፓፓ ራሳቸውን አሳፈው ሰጥተዋልና፥ በእምነቱም መሠረት ግዴታ መወጣት የተለመደ ነውና ምናልባት ቫቲካን አቡነ ጳውሎስን በመንግሥቴ ላይ ዐምፀው ወደ ኢትዮጵያ የገቡትን ያሉትን በሕይወታቸው፥ የሞቱትንም ከመቃብራቸው ማምጣት አለብዎ ብላ ብትጠይቃቸው መልሳቸው ምን ይሆን? የዕውቀት ፍጻሜ ነው ብለው የያዙት ፊሊጥ ነውና ምናልባትም ለእኔ ጥያቄ ዝም እንዳሉ ያንንም በዝምታ ያልፉት ይሆን? አይመስለኝም። ይህማ እንዳይሆን ከዚያ ወዲህ የክሕደት፥ የኑፋቄ መጽሐፍ በመሳተምና በመበተን፥ ኦርቶዶክሳዊውን የሊቃውንት ጉባኤ በማፍረስ፥ በቤተ ክርስቲያን ሕግ የቆመውን፥ በቃል ኪዳን በወልደ እግዚአብሔር ደም ምለው ተጠሪ የሆኑለትን ኦርቶዶክሳዊውን የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በማፍረስ በሮም ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት አመራር ሰጪ የሆኑለትን፥ ለራሳቸው ተጠሪ ያደረጉትን ሚያዝያ ፴ ቀን ፲፱፻፹፰ ዓ. ም. በተፈረመ ሕገ ጣዖት ሰው ሠራሽ ሲኖዶስ በማቋቋም ታላቅ ማረጋገጫ የሰጡ ስለ ሆነ የቫቲካንን ጥያቄ በቸልታ የሚያልፉት አይመስልም። በሕይወት ያሉት የነ አቡነ ገሪማ፥ የነ አቡነ አረጋዊ፥ የነ አቡነ ዮሐኒ ሕይወት የማያሰጋ ቢሆንም በልዩ ልዩ ገዳማተ ትግሬ ያረፈው የልዩ ልዩ ቅዱሳን አበው ዐጽም እየተቆፈረ ለሮማ ቤተ ክርስቲያን ገጸ በረከት እንዳይሰጥ ታላቁና ሃይማኖታዊው የትግሬ ክርስቲያን ሕዝብ ማስተዋል የተሞላበት ጥንቃቄ እንዲደርግ ያሻል። በኢያሱ ዘመን እርም የሆነውን ደብቆ የተገኘ አካን ወልደ ከርሚ በሕዝቡ ላይ ብርቱ ጥፋት አስከትሎ እንደ ነበር መጽሐፍ ይናገራል። አቡነ ጳውሎም እርም የሆነውን፥ ከሮማ ጋር የተከለከለውን ግኙነት ከተሾሙባቸው ክርስቲያኖች ደብቀው በፈጸሙት ሥራ ሁሉ ሕዝባቸውን ለጥፋት እያጋለጡ ነው።
አበው ጳጳሳት! ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ አራት ታላላቅ ሌላም ጥቃቅን ሃይማኖቶች አርግዛ እያማጠችና እየተጨነቀች ነው። እንኳን ይህን ያህል ሽል ሁለት መፅነስ ክብደቱ ምን ያህል እንደ ሆነ በርብቃና በትዕማር ታሪክ የታወቀ ነው። ይህ ብዙ ሃይማኖትን በአንድ ጊዜ ማርገዝ በኢትዮጵያ ብቻ ለሙከራ የቀረበ ሲሆን ሽሎቹ በመታገል ላይ መሆናቸውና ይልቁንም አንዱ እንደ ፋሬስ ጥሶ ለመውጣትና ብኵርናውን ለመውሰድ እየታገለና ወላዲቱንም እያስጨነቃት መሆኑ እየታየ ነው።
አበው ጳጳሳት፥ መነኮሳት፥ ሊቃውንት፥ ቀሳውስት፥ እናቶች፥ አባቶች! ሌላው ቢቀር ተሰብስባችሁ ማርያም ማርያም ብትሉ አይሻልምን? ኧረ ዝምታው አያዋጣም። አሁን እኔ አይደለሁም የምናገር። ታሪክ ነው የሚናገር። ስዊድናዊው ታላቅ ጸሐፊ የመዘገቡላችሁን ካነበባችሁ በኋላ፤ «እርስዎ ለሚያመልኩት አምላክ ኢትዮጵያ ጸሎት ልታሳርግ አትችልም፤» ያሉትን አስታውሳችሁ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለሰበከችው፥ አቡነ ጳውሎስ ለተቀበሉት፥ ሰው ሠራሽ ሲኖዶስ ላቆሙለት ሰው ሠራሽ ሃይማኖት እንዳትንበረከኩ መላው የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ጎሣ ቋንቋ ሳይለያችሁ ለሃይማኖታችሁ አንድ ሆናችሁ እንድትቆሙ፤ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃማኖታችሁን ያፋለሱትን፥ የቤተ ክርስቲያናችሁን ክብር የገሠሡትን አቡነ ጳውሎስን በአንድ ቃል እንድትቃወሙ ወርቀ ደሙን ዋጋ፥ መስቀሉን የድል ገበያ አድርጎ በደሙ በዋጃችሁ በኢትዮጵያ አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እጠይቃችኋለሁ።
እንዲሁም የመስቀሉ ጠላቶች ሲሆኑ በአንገታቸው መስቀል አድርገው፥ በእጃቸው መስቀል ጨብጠው ከሚታዩት ከአቡነ ጳውሎስና ከአቡነ ገሪማ፥ ከደጋፊዎቻቸውም ጋር የመስቀልን የደመራ በዓል እንዳታከብሩ ለአባቶች ለሐዋርያት ለእኔም በተሰጠው በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ሥልጣን ገዝቼአለሁ። በዚህ ፈንታ በየደጃችሁ ቤተሰብ ከቤተሰብ፥ ጎረቤት ከጎረቤት ተባብራችሁ በዓላችሁ በጸጥታ አክብሩ። በበዓሉ ላይም ፲፪ ጊዜ እግዚኦታ፥ ፲፪ ጊዜ በእንተ ማርያም፥ ፲፪ ኪራላይሶን አድርሱ። በዓላችሁ በጸሎት፥ በኀዘን የተጠበቀ ይሁን።
ያለነው እጅግ በሚያዝን ሁኔታ ውሥጥ ነው። ሃይማኖት በሌለበት ዓለምም ሰላምም አሉ ማለት አይቻልም። ሰላም ደግሞ ከዓለም የሚገኝ ስጦታ አይደለም። ሰላም ከእግዚአብሔር የሚገኝ ስጦታ ነው። እግዚአብሔር የሌለው ሰላም የለውም። ይህ ደግሞ የሚያከራክር አይደለም። ኢትዮጵያ ከእግዚአብሔር ጋር በሃይማኖት ጸንታ የኖረችበትን ረጅም ዘመንና ከሱ ተለይታ ወደ ፖለቲካ ገበያ ገብታ የሃይማኖት ሸቀጥ እያማረጠች ያለችበትን ከለውጥ ወዲህ ያለውን ዘመን በሚዛን ላይ አድርጎ መመልከት ይቻላል። ስለዚህ ሰው ምንም ሊያደርግ የማይችልበት የመከራ ሌሊት ነግቶ የሃይማኖት ብርሃን ወደሚታይበት ጊዜ ለመድረስ እጅግ በጣም አጥብቆ መጸለይ ያስፈልጋል። ትጉ ጸልዩ። ሃይማኖታችሁን ጠብቁ።
የእግዚአብሔር አብ ጸጋ፥ የእግዚአብሔር ወልድ ቸርነት፥ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ፍቅር ከእናንተ ጋር ይሁን።
አለቃ አያሌው ታምሩ ዘዲማ ጊዮርጊስ፤
የኦርቶዶክሳዊው የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ።
(ማዕበል ጋዜጣ፤ መስከረም ፲፩ ቀን ፲፱፻፹፱ ዓ. ም. )