ታላቂቱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፤ በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በእመቤታችን አማላጅነት፣ በምእመናን ጽኑዕ እምነት፣ በነገሥታት የበላይ ጠባቂነት፣ በካህናትና በሊቃውንት ቀናዒነት ተጠብቃ በየጊዜው የተደቀኑባትን መከራዎች ሁሉ በማለፍ ብዙ ዘመናትን ለመሻገር ብትችልም፤ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን በታሪኳ ታይተው የማያውቁ ብዙ ፈተናዎችን ለማስተናገድ ተገዳለች፡፡ እነዚህም የእምነት፣ የሥርዓት የታሪክ መፋለስ ተብለው በጥቅል ሊቀመጡ ቢችሉም በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ያደረሱት አደጋ ግን መጠኑ ከፍተኛ ሲሆን ውጤቱም የምእመናንን ኀዘንና የእግዚአብሔርን ቁጣ ያስከተለ ነው፡፡
ችግሩ አሁንም መፍትሔ አላገኘም፡፡ አሁን በሥራ ላይ ያለው የቤተ ክርስቲያኒቱ ‹‹ሲኖዶስ›› አባላት እንዲሁም ካህናትና አገልጋዮች፤ ከችግሩ ጠንሳሽ ከውጉዙ የቀድሞ ፓትርያርክ አባ ጳውሎስ ጋር በመተባበር በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ያደረሱት በደል ከፍተኛ እንደ መሆኑ መጠን፤ የቀድሞው የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ አለቃ አያሌው ታምሩ ባላቸው ግዴታና ኃላፊነት፣ እንዲሁም ከእግዚአብሔር በደረሳቸው መልእክት መነሻነት ውግዘት ለማስተላለፍ ተገደዋል፡፡ ይሁን እንጂ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቃነ ጳጳሳት፣ ጳጳሳት፣ ኤጲስ ቆጶሳት፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናት፣ ለቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪ ነን ባዮች ማኅበራትና ቡድኖች እንዲሁም ምእመናን ሳይቀሩ ለችግሩ መፍትሔ በመፈለግ ፈንታ ለበደሉ ፈጻሚዎች ድጋፍ በመስጠታቸው ምክንያት ችግሩ እስካሁን ድረስ ቤተ ክርስቲያናችንን እየጎዳት ይገኛል፡፡
በአሁኑ ወቅትም የቤተ ክርስቲያኒቱ ሲኖዶስ ፮ኛ ፓትርያርክ ለማስመረጥና ለመሾም ሽር ጉድ እያለ እንደሚገኝ የሚገልጽ ዜና ከዜና ዐውታሮች በመስማታችን ኀዘናችን ከፍ ያለ ሆኗል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን አሁን የተጋረጠባት ከፍተኛ ችግር የፓትርያርኩ መንበር ክፍት መሆን ሳይሆን የእምነትና የሥርዓት መጥፋትና መፋለስ ነው፡፡ በዚህ መነሻነት በተላለፈው ውግዘት ምክንያትም የቀድሞው ፓትርያትክም ሆኑ አሁን ያሉት የሲኖዶስ አባላት፣ እንዲሁም የበደሉ ተባባሪ የሆኑ ካህናት፤ የማጥመቅም ሆነ የመባረክ፣ የማቁረብ፣ የመሾም፣ የመሻር በአጠቃላይ የክህነት መብታቸው የተነሣ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ስለ ሆነም አዲስ ፓትርያርክ ለመምረጥም ሆነ ለመሾም የሚያስችል እምነትም ሆነ ሥልጣን እንዲሁም ጸጋ የላቸውም፡፡ አሁን የቤተ ክርስቲያኒቱ እምነት፣ ሥርዓትና ሕግ በተፋለሰበትና በቦታው በሌለበት ሁኔታ፤ ፮ኛ ፓትርያርክ ለማስመረጥና ለመሾም በሚል ፈሊጥ የሚደረገው ሥራ ሁሉ፤ የጥቂት ማኅበራትንና ቡድኖችን ፍላጎትና ጥቅም ከማርካት ያለፈ ጥቅም የሌለው፤ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳት የሚያባብስና ቁስሏን የሚያሰፋ፤ በቤተ ክርስቲያንና በምእመናን እንዲሁም በእግዚአብሔር ላይ የሚፈጸምና የተፈጸመ ተግዳሮትና ስላቅ ነውና፤ ውጤቱ ጥፋት እንደሚሆን የተረጋገጠ ነው፡፡
ስለ ሆነም የሲኖዶስ አባላትና ካህናት ከዚህ ክፉ ሥራ ተቆጥበው፤ ከዚህ ቀደም በሠሩት በደል ተጸጽተውና ንስሐ ገብተው፤ ከዚህ ቀደም የተፋለሱትን የቤተ ክርስቲያቱን እምነትና ሥርዓት እንዲያስተካክሉ፤ የተበረዙትን የቤተ ክርስቲያን መጻሕፍትና ሕጎች ወደ ነበሩበት እንዲመልሱ፤ በአጠቃላይ ለቤተ ክርስቲያኒቱና ለምእመናን የሚበጀውን ሥራ እንዲያስቀድሙ ጥሪያችንን አናስተላልፋለን፡፡ ምእመናንም በዚህ ፮ኛ ፓትርያርክ ማስመረጥ በሚል ዜና ሳይደናገሩ በእምነታቸው ጸንተው፤ ‹‹ይደልዎ›› ከማለትና ከሆሆታ ተቆጥበው በጸሎት ልመናቸውን ወደ እግዚአብሔር እንዲያቀርቡ እናሳስባለን፡፡
ይህንን መልእክት ያግዝ ዘንድ ከዚህ ቀደም ‹‹ወደ ግብጽ መመለስ›› በሚል ርእስ የቀረበውን ጽሑፍ ለማንበብ ከዚህ ይጫኑ፡፡