በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን።
አባታችን አለቃ አያሌው ካረፉ እነሆ ሦስት ዓመታት ተቆጠሩ። በእነዚህ ሦስት ዓመታት በቤተ ክርስቲያናችን በኩል ያለው ችግር ከቀን ወደ ቀን እየባሰ ከመሄድ በስተቀር የተሻለ ነገር አልታየም። ይልቁንም በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ጣዖት እስከ መቆም ደርሷል። በክቡር አባታችን የቀረቡት ማስጠንቀቂያዎችም እየተፈጸሙ ይገኛሉ። የቤተ ክርስቲያናችን ትምህርተ ሃይማኖትና ሥርዓት ተበላሽቷል፤ ሲኖዶሱ ተጠሪነቱ ለመንፈስ ቅዱስ መሆኑ ቀርቶ ለፓትርያርኩ ሆኗል፤ በዚህም ምክንያት ቤተ ክርስቲያኒቱ የፓትርያርኩ የግል ርስት ሆናለች። ሊቃነ ጳጳሳት፥ ካህናትና ምእመናን ቤተ ክርስቲያንን ችላ ብለዋል። በቤተ ክርስቲያን ብልሹ አሠራር ነግሧል፤ ሰላም ጠፍቷል። በቤተ ክርስቲያን "አባቶች" ዘንድ የእግዚአብሔር ተግሣፅ እየታየ ነው። ነገር ግን ፓትርያርኩም ሆኑ ሊቃነ ጳጳሳት ምንም የመደንገጥ ምልክት አይታይባቸውም፤ እግዚአብሔርን መፍራት ርቋቸዋልና። በነዚህ ጉዳዮች ምክንያት በነዚህ ሦስት ዓመታት ኀዘናችን ከመበርታት በስተቀር የመቀነስ ምልክት አላሳየም፤ መካሪና አስተማሪ አባታችን ከጎናችን ተለይተዋልና። ነገር ግን እግዚአብሔር አምላካችን እንዲያስተላልፉ የሰጣቸው ቃላት እየተፈጸሙ መሆናቸውን ስናይ ደግሞ እንጽናናለን።
የተወደዳችሁ ምእመናን! ለክቡር አባታችን ዕረፍት ሦስተኛ ዓመት መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ያዘጋጀነውን ብሮሹር ከዚህ ማውረድ ትችላላችሁ። በተጨማሪም ይህንን ዕለት ምክንያት በማድረግ ለምእመናን ማንቂያ ይሆን ዘንድ የተሰናዳውንና አባታችን በተለያዩ ጊዜአት ለሊቃነ ጳጳሳት፥ ለካህናትና ለምእመናን ያስተላለፉትን መልእክት አጠናክሮ የያዘውን ጽሑፍ ከዚህ ማንበብ ይቻላል።
እግዚአብሔር አምላካችን በእመቤታችን አማላጅነት ለአገልጋዩ ለአባታችን ዕረፍተ መንግሥተ ሰማያትን ያድልልን። ለቤተ ክርስቲያናችን የሚበጀውን እሱ በፈቃዱ ያሰናዳልን። አሜን።
አባታችን ካረፉበት ጊዜ አንሥቶ ከቤተ ሰባቸው ጎን ሳትለዩ ላጽናናችሁ ሁሉ እግዚአብሔር ዋጋችሁን አይንፈጋችሁ፤ አሜን።