በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን።
ውጉዙና ዐመፀኛው ፓትርያርክ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለማፍረስ ቀን ከሌት ለሚያደርጉት ጥረት ማስታወሻ ወይም ማኅተም ይሆን ዘንድ፤ ወይንም ይህችን ጥንታዊት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ለማፍረሳቸው የእንኳን ደስ አለዎ ገጸ በረከት ይሆን ዘንድ በግብር አበሮቻቸው የተሠራላቸው ሐውልት ወይም ጣዖት በአካል በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ከቆመ እነሆ ቀናት ተቆጠሩ። እሳቸው ግን ቤተ ክርስቲያን የምትመራባቸውን ሕጎች ሁሉ ሽረው ቤተ ክርስቲያንን በሚመራው መንፈስ ቅዱስ ፈንታ ገብተው በጣዖትነት ከተሠየሙ ከ፲፬ ዓመት በላይ ሆኖአል። ነገር ግን ቤተ ክርስቲያናችን አዛኝና ተቆርቋሪ አባቶችና ምእመናን አጥታ በከፍተኛ ኃዘን ላይ ትገኛለች። እግዚአብሔር ግን ይህችን ቤተ ክርስቲያን ፈጥሞ አልጣላትም ነበር፤ ለዚህች ቤተ ክርስቲያን ተቆርቋሪ የሆኑ አንዳንድ ነቢያትን ማስነሣቱ አልቀረም። ሰሚ አላገኘም እንጂ። ከነዚህም እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያን አንደበት አድርጎ ካስነሣቸው አባቶች መካከል በዚህ ወር የዕረፍታቸውን ሦስተኛ ዓመት የምናስበው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ አለቃ አያሌው ታምሩ አንዱ ነበሩ።
አባታችን አለቃ አያሌው ታምሩ ነፍስ ካወቁበትና በቤተ ክርስቲያን ሥራ ላይ ከተሠማሩበት፥ ይልቁንም የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ ከሆኑበት ጊዜ አንሥቶ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ እምነትና ሥርዓት ጥበቃ ጉዳይ የሊቃውንት ጉባኤን በቀጥታ የሚመለከተው እንደ መሆኑ መጠን በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደርሱ በደሎችና አደጋዎች ይቆሙ ዘንድ ገና ከመጀመሪያው ለሚመለከታቸው ክፍሎች አቤቱታ በማቅረብ ይታወቃሉ። አብዛኛዎቹ ጥቆማዎቻቸውና ምክሮቻቸው ግን በቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች ዘንድ ተቀባይ ባለ ማግኘታቸው ቤተ ክርስቲያን ከጊዜ ወደ ጊዜ ውድቀቷ እየጨመረ መጥቶ አሁን ባምስተኛው ፓትርያርክ ዘመን ከፍጻሜ ላይ ደርሷል።
እሳቸው ግን ማንም ምክሬን አልተቀበለውም በሚል ምክንያት ሥራቸውን አላቋረጡም። ይህንንም ሁኔታ በአንድ ወቅት እንዲህ በማለት ገልጠውት ነበር። "የቤተ ክርስቲያን መልእክተኛ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ነውና ባየው፥ በሰማው፥ በተመለከተው ሁሉ ሰው ይሰማኛል አይሰማኝም፥ ይቀበለኛል አይቀበለኝም አይልም። ሰው የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መልእክት ማድረስ ግዴታው ነው። ይህ ስለ ሆነ እኔም ግዴታዬ ነው፤" (ጦማር፤ ሚያዝያ ፳፫ ቀን ፲፱፻፹፰ ዓ. ም.)
በተለይም ዐምስተኛው ፓትርያርክ አባ ጳውሎስ የፓትርያርክነቱን መንበር ከተረከቡበት ጊዜ አንሥቶ በግብር አበሮቻቸው አጋዥነት የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ለማፍረስ የሚያራምዱትን ዓላማ ገና ከጅምሩ በመቃወም ጉዳዩን ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሲኖዶስ፥ ጳጳሳት፥ የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች፥ ካህናትና ምእመናን በየደረጃው ማቅረባቸውና በመጨረሻም ቃለ ውግዘት ማስተላለፋቸው የሚታወስ ነው።
ይህንን ዐሳባችንን የበለጠ ያብራራልን ዘንድ አባታችን የካቲት ፭ ቀን ፲፱፻፹፱ ዓ. ም. ከወጣው ኢትኦጵ ጋዜጣ ጋር «ቤተ ክርስቲያንን ከተውንማ ሌቦች ይገቡበት የለም ወይ ተብሏል። አሁንስ ገብተውበት የለም ወይ።» በሚል ርእስ ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ከዚህ ቀጥለን አቅርበናል።
«የሃይማኖት ሊቅ አለቃ አያሌው ታምሩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውሥጥ ያለውን ውዝግብ በተመለከተ ለእምነቱ ተከታዮች ግዝት አስተላልፈዋል። በተለይም ባሕታዊ ፈቃደ ሥላሴ ጥር ፩ ቀን ፲፱፻፹፰ ዓ. ም. ከተገደሉ በኋላ ምእመናን ፓትርያርኩ ባሉበት እንዳይደርሱና ታቦትንም እንዳጅቡ ገዝተዋል። ይህንን የአለቃ አያሌውን ግዝት በተመለከተ በርካታ የእምነቱ ተከታዮች በነገሩ ግራ መጋባታቸውንና ግዝቱ ግልጽ እንዳልሆነላቸው፥ አንዳንዶቹም ግዝቱ እንዲነሣላቸው በዝግጅት ክፍላችን በኩል ጥያቄዎችን በማቅረብ ላይ ናቸው። በዚህ ጉዳይ ላይ ያልተብራሩና ተብራርተውም ምእመናን ሊረዱ ያልቻሏቸውን ጥያቄዎች በመያዝ ወደ አለቃ አያሌው ታምሩ ዘንድ ጎራ ብለን ነበር። አለቃ አያሌው፤ «ጉዳዩን ግልጽ አድርጌዋለሁ፤ ያው አዲስ ነገር የምጨምረው የለም፤» የሚል አቋም ቢኖራቸውም ምእመናን ጥያቄውን እስካቀረቡ ድረስ ግልጽ አልሆነም የተባለውን ግልጽ አደርገዋለሁ በማለት ለምእመናን ጥያቄ ምላሽ ሰጥተውናል። በቅድሚያ በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መካከል የተፈጠረውን ውዝግብ የሃይማኖቱን ቤተሰቦች ብቻ ሳይሆን የሌሎች ኢትዮጵያውያንንም ሰላማዊ ሕይወት የሚያውክና ሰላምን የሚነሣ በመሆኑ ይህንን ጥቅል ሀገራዊ ችግር የሚፈታ መፍትሔ በማፈላለጉ ረገድ እኛም በሙያችን ለምናደርገው ጥረት አለቃ አያሌው ላሳዩን ትብብር በቅድሚያ ከልብ እያመሰገንን ወደ ቃለ ምልልሱ እንመለሳለን።
ኢትኦጵ፦ ባለፈው በኢትኦጵ ጋዜጣም ሆነ በተለያዩ የጋዜጣ ኅትመቶች ላይ እርስዎ ማንኛውም ምእመን ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዳይሄድ፥ እንዳይገባ ከልክለዋል። ያሉት አባቶች በሙሉ በሃይማኖቱ ላይ ሕፀፅ እየሠሩ ስለ ሆነ እነሱን አምኖ እዚያ መክበብ የለበትም ብለዋል። አንዳንድ ምእመናን ደግሞ ቤተ ክርስቲያን የአቡነ ጳውሎስ የግል ቤት አይደለችም፤ ለምሳሌ እንድ ውሻ ቤተ ክርስቲያን ውሥጥ ቢገባ ረክሷልና እርሱ ተባርኮ ምእመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን መግባት ይችላሉ። ስለዚህ አቡነ ጳውሎስን ማውገዝ ይቻላል፤ ወይም የእርሳቸውን ተከታይ የሆኑ ሰዎችን ማውገዝ ይቻላል፤ እንዴት ምእመናን ከቤተ ክርስቲያን ይራቁ ይላሉ? የሚል አንዳንድ ጥያቄዎች እየተነሡ ነው ያሉትና በዚህ ጉዳይ ላይ የእርስዎ ሐሳብ ምንድነው? ካለፈው በመነሣት።
አለቃ አያሌው፦ በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን። ከሁሉ አስቀድሞ ሥራችን የተባረከ ይሁን። በመሠረቱ ውግዘት እንደ ተራ ነገር አይወረወርም። ተጠንቶ፥ አስፈላጊ በሆነ ጊዜ ነው። ውግዘት ማለት ሰይፍ ነው። ጳውሎስ፤ «የእግዚአብሔር ቃል ጽኑዕ ነው፤ ኀያል ነው፤ ሕያው ነው፤ ሁለት ልሳን ካለው ሰይፍ ይበልጥ ስለት ያለው ነው። ነፍስን ከሥጋ፥ ከጥንትን ከጅማት የሚለይ፥ ሐሳብና ልብን ሳይቀር የሚመረምር ነው፤» ይላል። እንግዲህ ይህ «የእግዚአብሔር ቃል» ሲል ጳውሎስ የጠቀሰው ውግዘት ነው። መናፍስት ርኩሳንን ከቅዱሳን የሚለይ፥ አንተ መንፈስ ርኩስ ውጣ ብሎ የሚገሥፅና ከሰዎች የሚያርቅ፤ በሁለተኛ ደረጃ መናፍቃንን ከመሐይምናን የሚለይ፥ አንመለስም እምቢ ያሉትን፥ የማይፈወሱ ድውያን፥ የማይመለሱ ጊጉያን ከሆኑ፥ ሆነው ከተገኙ ሌላውን እንዳይበክሉ በውግዘት ይለያሉ። በብሉይ ኪዳን ሥርዓት ዝንጉርጉር ለምጽ የነበረበት ሰው በሕዝብ መካከል፥ ብዙ ሕዝብ በሚያርፍበት መካከል አይኖርም፤ ክልክል ነው። ሙሉ ለምጽ ከሆነ ግን አይከለከልም። ምክንያቱ ምንድነው? ሙሉ ለምጽ የሆነ እንደ ሆነ ሁሉ ያውቀዋል፤ አይጠጋውም። ዝንጉርጉር ለምጽ የሆነ እንደ ሆነ ግን የማያውቅ ስለሚጠጋውና ስለሚጋባ በዚህ ምክንያት ዝንጉርጉር ለምጽ ያለው በሕዝብ መካከል እንዳይኖር ተወስኗል። ይህም የመናፍቃን ምሳሌ ነው። የለየለት የማያምን ከሆነ ዐብሮ መኖር ይችላል፤ ችግር የለም መስሎ አያስትም። እስላምና ክርስቲያን ዐብረው መኖር ይችላሉ። ሃይማኖታቸው ቀጥታ የተለያየ ስለ ሆነ። ግን በክርስቲያን መካከል ያለው ልዩነት ይዘው እየተሽሎከሎኩ ቤተ ክርስቲያንን የሚያውኩ፥ የምእመናንን ትምህርት የሚያናውጡ፥ የምእመናንን ጠባይ የሚበርዙ ሆነው ከተገኙ በውግዘት ይለያሉ።
ስለዚህ በመጀመሪያ አንድ፥ ሁለት፥ ሦስት ሆኖ ምክር መስጠት ይቻላል። ይህ ሳይቻል ከቀረ በጉባኤ ለምእመናን ተነግሮ ስሕተቱ፥ በደሉ፥ ክሕደቱ ታውቆ ይለያል። በዚህ መሠረት ቤተ ክርስቲያን ከተቋቋመችበት ጊዜ ጀምሮ ብዙ መናፍቃን ከቤተ ክርስቲያን ወጥተዋል። ብዙውን ትተን በዐጭሩ ለመጥቀስ ወልድ በመለኮቱ ፍጡር ነው ያለ አርዮስ፥ ዛሬ ጂሆቫ የሚሰብከውን ስብከት ይሰብክ የነበረውን ያመነጨው አርዮስ፥ ክርስቶስ አምላክ ያደረበት ሰው ነው እንጂ አምላክ አይደለም ያለ ሳምሳጢ ጳውሎስ፥ መንፈስ ቅዱስ ከአብና ከወልድ ያንሳል ያለ መቅዶንዮስ፥ ለክርስቶስ ሁለት አካል ሁለት ባሕርይ አለው ያለ ንስጥሮስ፥ አንድ አካል ሁለት ባሕርይ ነው ያለ ፍላብያኖስና የእሱን ዐሳብ ደግፎ የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን የመሠረተ ልዮን ተወግዘው ተለይተዋል በጉባኤ። እንግዲህ ይህ የሆነው ኦርቶዶክሳዊት ርትዕት ሃይማኖት በቤተ ክርስቲያን ጸንታ እንድትኖር ነው። ከዚህ በኋላ አንዱ ወደ ሌላው ሊሄድ አይችልም፤ በውግዘት ተገድቧል። ጳውሎስ፤ «የእግዚአብሔር ቃል ጽኑዕ ነው፤ ኀያል ነው፤ ሕያው ነው፤ ሁለት ልሳን ካለው ሰይፍ ይበልጥ ስለት ያለው ነው። ነፍስን ከሥጋ፥ ከጥንትን ከጅማት የሚለይ፥ ሐሳብና ልብን ሳይቀር የሚመረምር ነው፤» ሲል በተናገረለት በእግዚአብሔር ቃል ተለይተዋል። ተከታዮቻቸው በየጊዜው ሲለዩ፥ ሲወገዙ ይኖራሉ። ጌታ፤ መጀመሪያ ራስህ፥ ቀጥሎ ሁለት ሦስት ይዘህ ንገረው፤ ከዚህ በኋላ አልመለስም ካለ ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ለቤተ ክርስቲያን ነግረሃት ቤተ ክርስቲያንን አልሰማም ካለ እንደ አረመኔ ይሁን፤ ሲል ማንም ሰው የቤተ ክርስቲያንን ትምህርት፥ ሥርዓት፥ ሕግ መጠበቅ የማይችል ሆኖ ተመክሮ የማይመለስ ከሆነ መጀመሪያ በግል፥ በምስክር፥ በማኅበር ተወግዞ ይለያል።
በዚህ መሠረት ነው እኔ ያወገዝኩት። መጀመሪያ ብቻዬን ሁለት ዓመት ተኩል በቃልም በደብዳቤም
ጠየቅኋቸው። አባ ጳውሎስም አባ ገሪማም እምቢ ብለው በቤተ ክርስቲያንና በሃይማኖት ላይ ስለ ዐመፁ ለጉባኤ ነግሬአለሁ። በአጠቃላይ
ጉባኤ፤ «ከፓፓው በላይ ካቶሊክ የለም አንደሚባለው ነው፤ አንመለስም፤» ብለው ከነ ተረታቸው ወደ ፓፓው መሄዳቸውን ስላረጋገጡ ከዚህ
በኋላ ለሕዝብ ነግሬአለሁ። ለሕዝብ ከነገርኩ በኋላ ደግሞ እኔን ማባረር ሳይበቃቸው የቤተ ክርስቲያኒቱን የሊቃውንት ጉባኤ ስላፈረሱ፥
የክሕደትና የኑፋቄ መጽሐፍ ስላወጡ፥ መጽሐፍ ቅዱስን የሚለውጥ ጉባኤ ስለ ሰየሙ፤ በሲኖዶስ እንዳልከሳቸው ደግሞ ሲኖዶስን ሽረው ራሳቸው በመንፈስ ቅዱስ ፈንታ ተሰይመው በጣዖትነት ደረጃ በቤተ ክርስቲያን ላይ ስለ ተቀመጡ ለዚህም ሚያዝያ
፴ ቀን ፲፱፻፹፰ ዓ. ም. የማስፈጸሚያ ሕግ ስላወጡ፤ ይህን ሕግ አንዲያነሡ ጠየቅሁ። አልቀበልም ስላሉ አወገዝሁ። ራሳቸው
አባ ጳውሎስና የሲኖዶሱ ዋና ጸሓፊ አባ ገሪማ ከዐጸደ ቤተ ክርስቲያን እንዳይደርሱ፥ ከምእመናን እንዳይቀላቀሉ፥ ሥጋውን ደሙን እንዳይቀበሉ
አወገዝኩ። እምቢ ስላሉ ደግሞ፤ በእነሱ እጅ፥ ከእነሱ ማንኛውም ሰው ቡራኬ እንዳይቀበል፥ ትምህርት እንዳቀበል
አወገዝኩ። እንደገናም ሊቃነ ጳጳሳቱ ሐምሌ ፮ ቀን የሳቸውን በዓል ለማክበር ሲዘጋጁ አስቀድመው ሕጉን እንዲሽሩ፥
ካልሻሩ ግን ይህንን በዓል እንዳያከብሩ፤ በሕጉ ላይ የፈረሙት ጳጳሳት፥ ድጋፍ የሰጡ አለቆችና ተባባሪዎች በጸሎተ ቅዳሴ ስማቸውን
ካህናት እንዳይጠሩ አወገዝኩ። አልቀበልም ስላሉ የእነሱን ሐሳብ የሚከተሉ ምእመናን ሁሉ በዚህ እንዳይመረዙ፥
እነሱንም እንዳይከተሉ፥ እንዳይቀበሉ አውግዤአለሁ።እንግዲህ የእኔ የውግዘት ደረጃ እዚህ ድረስ ነው የመጣው። ሰዎች ከእነሱ መተባበር እንዲለዩ እንጂ ሌላ ቃል አላስተላለፍኩም። በእነሱ እጅ ሥጋውን ደሙን እንዳይቀበሉ፥ በእነሱ እጅ
እንዳይባረኩ፥ በእነሱ እጅ መስቀል እንዳይሳለሙ፤ ምክንያቱም በትንቢተ ሚልክያስ ምዕራፍ ፪፤ «ይህች ትእዛዝ ለእናንተ ለካህናት
ናት፤» በሚለው ክፍል፤ «እናንተ ካህናት ስሜን አርክሳችኋልና እኔም በረከቴን ነሥቼአችሁአለሁ፤» በሚለው ቃል ጠቅሼ ክርስቶስን
የከዱ፥ አምላክነቱን የካዱ፤ የማሉበትን፥ ቃል ኪዳን የገቡበትን ደሙን የረገጡ አባ ጳውሎስና አባ ገሪማ፥ ደጋፊዎች ጳጳሳት፥ የተቀበሏቸው
አለቆችና ካህናት ሁሉ በረከት አልባ ስለ ሆኑ በገዛ እጃቸው ከበረከት የወጡ ስለ ሆኑ አውግዤአለሁ። ምክንያቱም
ከእነሱ የሚገኝ በረከት የለም። ሰዎች የሚሉት ብንቆርብ ምናለበት፥ መስቀል ብንሳለም ምናለበት ነው። ምናለበት የሚባል ነገር የለም።
በሃይጂን ሕግ እንኳ ባልታጠበ ዕቃ አይበላም፥ ባልታጠበ ዕቃ አይጠጣም። ራሱ እምነት ከሌለው በምን ሥልጣኑ ነው የሚባርክ፥ መሥዋዕት
የሚለውጥ፥ ዕጣን፥ ቁርባን የሚያሳርግ በምን ሥልጣኑ ነው? ውጉዝ ነው፤ አይችልም። ሃይማኖት የለውም፤ ውጉዝ ነው፤ ምንም ሥራ መሥራት
አይችልም። ጌታ ሲናገር ምንድነው ያለው? ለሐዋርያት፤ «እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤» ብሏቸዋል። ጨው ምንድነው? ከዓለም
መራራው ነገር ሁሉ የሚጣፍጥበት ነው። «ግን፤» ነው ያለ ጌታ፤ «ጨው አልጫ ቢሆን ድንጋይ ተብሎ ይጣላል እንጂ ለምንም አይጠቅምም፤»
ነው ያለው። «ጨውን አልጫ የሚያደርግ ቢኖር፤» አይደለም ያለው። ከሌላ አይደለም የሚመጣው፤ ከራሳቸው ነው። ጨው አልጫ ቢሆን ድንጋይ
ይሆናል። ድንጋይ ከሆነ ምንም ነገር የለውም። ከእሱ የሚገኝ ነገር የለውም ማለት ነው። ይሁዳም እኮ ጨው ነበር፤ ጨው ናቸው ከተባሉት
ከሐዋርያት ውሥጥ ነበር። ስለ ከዳ ግን ድንጋይ ሆነ። ስለዚህ ከሱ በረከት አይጠበቅም። «አበያ ለበረከት ወትርሐቅ እምኔሁ።» «በረከትን እምቢ ብሏታል፤ ከእሱ ትራቅ፤» ነው ያለው እግዚአብሔር ቃል። «በረከትን እምቢ ብሏታል፤ ከእሱ ትራቅ፤ መርገምንም እንደ
ልብስ ለብሷታል፤» ነው ያለው።
አባ ጳውሎስና አባ ገሪማ ሚያዝያ ፴ ቀን ፲፱፻፹፰ ዓ. ም. የታወጀውን፥ የቤተ ክርስቲያንን ሕጎችና ደንቦች ሽረው ለአባ ጳውሎስ ሲባል የታወጀውን ሕግ ያወጡ፥ የፈረሙ ጳጳሳት ሁሉ በረከትን እምቢ ብለዋል፤ እነሱ በረከት የላቸውም፤ ለሌላውም በረከት መስጠት አይችሉም። ጳጳሳት፥ መነኮሳት፥ ቀሳውስት በሙሉ የዚህን ድጋፍ የሰጡ ሁሉ ምንም ሥልጣነ ክህነት የላቸውም። «ጨው አልጫ ቢሆን ድንጋይ ተብሎ ይጣላል፤» ነው ያለው። ስለዚህ ምእመናን ከእነሱ የሚጠብቁት ነገር የለም፤ ፍትኀት የለም፤ ቁርባን፥ ቡራኬ ከእነሱ አይገኝም።
ከእነሱ ነጻ የሆነ ቄስ ካለ አላወገዝኩም፤ ከእነሱ ነጻ የሆነ መነኩሴ ካለ አላወገዝኩም። በቀረ ግን አንዱ ከቄስ በላይ ነኝ ብሎ ቢያውጅ፥ ሌላው እኔ ጳጳስ ነኝ እሽረዋለሁ ብሎ ቢናገር አይችልም፤ መብቱም አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ክርስቶስ ጳጳስ ነው፥ ነበር የሚል ቃል የለም። ለቤተ ክርስቲያን ካህን ነው የሚለው፤ ታላቁ ካህን ነው የሚለው። «ካህን» በሚለው ስማችን ሁላችንም አንድ ነን። በማጥመቅ፥ በማቁረብ፥ በመናዘዝ፥ በማስተማር፥ በማሰር፥ በመፍታት፥ ኃጢአትን ይቅር በማለት እኩል ነን። የምንለያየው በአስተዳደር ጉዳይ ነው። ስለዚህ እምቢ ብለዋል፤ ቤተ ክርስቲያንን እምቢ ስላሉ አውግዤአቸውአለሁ። ከእነሱ በረከት የሚገኝ ነገር የለም፤ እነሱንም የሚከተል ሁሉ ውጉዝ ነው። ይህ ነው መታወቅ ያለበት። አሁንም እነሱንና ለእነሱ ደጋፊ ሆነው የቆሙትን የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች፥ ቀሳውስት፥ ዲያቆናት፥ ሰበካ ጉባኤ አባላት፥ ዕድሮች ሁሉ እንዳይቀበሉ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ሥልጣን ገዝቼአለሁ።»
በተጨማሪም አባታችን በተለይ ለጳጳሳት የሚከተለውን ምክር አስተላልፈው ነበር። “ዶሮ ጫጩቶቿን
ከክንፎቿ በታች እንደምትሰበስብ ክርስቶስ ኢየሱስ ወደሱ ሊሰበስባችሁ ፈለገ። እየጠራችሁ ልትሰሙት አልፈለጋችሁም። በዚህ ፈንታ ወደ
አባ ጳውሎስ ጉያ ሸሻችሁ፤ በአባ ጳወሎስ ጥላ ሥር ተሰበሰባችሁ። ኢየሱስ ክርስቶስ መረጣችሁ፤ እናንተ ግን አልመረጣችሁትም። በሱ
ፈንታ አባ ጳውሎስን መረጣችሁ፤ አባ ጳውሎስን ወደዳችሁ። መንፈስ ቅዱስ ወደ እውነት ሁሉ ሊመራችሁ ተሰጥቷችሁ ነበር። እናንተ ግን
ከሱ ይልቅ የአባ ጳውሎስን አመራር ሰጪነት መረጣችሁ። ታላቁ ሐዋርያ ቅዱስ ጳውሎስ ፤ “ወኢታምዕዕዎ ለመንፈስ ቅዱስ ዘቦቱ
ዐተቡክሙ አመ ድኅንክሙ።” “የከበራችሁበትን መንፈስ ቅዱስን አታሳዝኑት።” (ኤፌ፤ ፬፥ ፴።) “ይዕዜኒ ዕቀቡ ርእሰክሙ ወኵሎ መራዕየ ዘሎቱ ሤመክሙ መንፈስ ቅዱስ
ጳጳሳተ ከመ ትርአዩ ቤተ ክርስቲያኑ ለእግዚአብሔር እንት አጥረያ በደሙ።” “አሁንም ክርስቶስ በደሙ የዋጃትን ቤተ ክርስቲያን
እነድትጠብቁ መንፈስ ቅዱስ ጳጳሳት አድርጎ ለጥበቃ የሾማችሁ እናነት ለመንጋውና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።” (የሐ፤ ሥራ ፳፥ ፳፫።)
ሲል ታላቅ ምክር ሰጥቶአችሁ ነበር። እናንተ ግን ለራሳችሁም ሆነ ለመንጋው፥ ለቤተ ክርስቲያንና ለምእመናን አልተጠነቀቃችሁም። ቅዱስ
ጳውሎስ በዚህ ብቻ አልቆመም። “ወአነ አአምር ከመ ይመጽኡ እምድኅሬየ ተኵላት መሰጥ እለ ኢይምህክዋ ለመርዔት ወእምውስቴትክሙ
ይትነሥኡ ዕደው እለ ይሜህሩ ጠዋየ ነገረ ከመ ያግብዕዎሙ ለአሕዛብ ኀቤሆሙ።” “ከእኔ በኋላ ለመንጋዪቱ የማይራሩ ነጣቂዎች
ተኩላዎች እንደሚመጡ እኔ ዐውቃለሁ። ከእናንተ መካከል ሰዎችን ወደ እነሱ ይመልሱ ዘንድ ጠማማ ትምህርትን የሚያስተምሩ ሰዎችም ከመካከላችሁ
ይነሣሉ።” (የሐ፤ ሥራ ፳፥ ፳፱ እና ፴።) ብሎ ነበር። እናንተ ግን አልተመለከታችሁትም። “ወሰብእሰ እኩያን ይትሌዓሉ ውስተ
እንተ ተአኪ ወይስሕቱ ወያስሕቱ። ወአንተሰ ሀሉ በዘተመሀርከ ወተአመንከ።” “ክፉዎች ሰዎች ግን በክፋት ላይ ክፋትን እየጨመሩ
ይሄዳሉ፤ ራሳቸው ይስታሉ ሌላውንም ያስታሉ። አንተ ግን በተማርከው ትምህርት በአመንከው እምነት ጸንተህ ኑር፤” ብሎ ነበር። (፪
ጢሞ፤ ፫፥ ፲፫ እና ፲፬።) እናንተ ግን ልብ አላደረጋችሁትም። አባ ጳውሎስ፥ አባ ገሪማ በስርቆሽ በር ገብተው ወደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ
ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ክብር ከደረሱ በኋላ በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም ያገኙት መንፈሳዊና ሥጋዊ ክብር ሁሉ አልበቃቸው ብሎ
የኢትዮጵያንና የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ጥንተ ጠላቶች የሮማን ተኵላዎች ስበው ጎትተው በእናንተ ላይ ከማንገሣቸውና
ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ጥገኛ ከማድረጋቸውም በላይ የቤተ ክርስቲያንን ትምህርተ
ሃይማኖት በማፋለስ፥ ሕጓን ሥርዓቷን በመጣስ በመንፈስ ቅዱስ ፈንታ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አመራር ሰጪ አዲስ አምላክ በመሆን ከክፋት
ወደ ክፋት፥ ከስሕተት ወደ ስሕተት ሲያድጉ እናንተም የጠራችሁን ክርስቶስን፥ የተጠራችሁላትን ቤተ ክርስቲያንን ትታችሁ በእነሱ ስብከት
ተሳስታቸሁ፥ ለግርማቸው ተሸንፋችሁ ራሳችሁ ለአባ ጳውሎስ ተጠሪ በመሆናችሁ፤ በአንጻሩም ክርስቶስ በደሙ የዋጃትን ቤተ ክርስቲያን
ላልተሰቀሉላት፥ ቤዛ ላልሆኑላት ለአባ ጳውሎስ ተጠሪ በማድረጋችሁ እናንተም ቁልቁል አድጋችኋል፤ ቤተ ክርስቲያንንም ተጋፍታቸኋል።
ለራሳችሁም፥ ለመንጋውም አልተጠነቀቃችሁም። በዚህም መንፈስ ቅዱስን አሳዝናችኋል።” (ትኩረት፤ ጥቅምት ፭ ቀን ፲፱፻፹፱ ዓ. ም.)
ለምእመናንም የሚከተለውን ምክር አስተላልፈው ነበር። “አሁን ደግሞ ጭራሽ የሃይማኖት ዱካና
ፍለጋ እንዳይገኝ ነባር መጻሕፍትን ለማጥፋት በእነ አቡነ ጳውሎስ የሚደረገው ትግል ውጤቱ በእግዚአብሔር ፍርድ ውስጥ መውደቅ መሆኑ
አያጠራጥርም። ፓትርያርኩና ሊቃነ ጳጳሳት ወደ ቤተ ክርስቲያን በሚመጡበት ጊዜ ሁሉ እግዚአብሔርን ለመፈለግ ወደ ቤተ ክርስቲያን
የመጡ ምእመናን በእግዚአብሔር ስም የሚያደርጉላቸውን የፍቅር አቀባበል በኃይላቸው፥ በጉልበታቸው ለጌትነታቸው እንደ ተደረገ ግዴታ
አድርገው ስለ ቆጠሩት እግዚአብሔርን ስሙንና ቤተ ክርስቲያኑን እየናቁ ነው። ምክሩንና ተግሣፁን ለመቀበል ፈቃደኛ አይደሉም። ይህ
ፍርድ ደግሞ በእነሱ ብቻ ሊወሰን አይችልም። የዔሊ ልጆች አፍኒንና ፊንሐስ በፈጸሙት ዐመፅ ታቦተ ጽዮን እንድትማረክ፥ እስራኤል
በጠላቶቻቸው እንዲዋረዱ ከእግዚአብሔር ተፈርዷል። በዚህ አንጻር በቤተ መቅደስ ውስጥ የሚፈጸም ዐመፅ በቅርብ አገልጋዮች ብቻ አይወሰንም።
ካልነቁ፥ ንስሐ ካልገቡ ሕዝቡንም ይነካል። በአገልጋዮች ብቻ የሚወሰንበት ጊዜም አለ። በአሮን በቆሬ ልጆች እንደ ተፈጸመው ነው።
በዚህ መሠረት ቅጣቱ በዐመፀኖች ብቻ ከተወሰነ መልካም ነው። ግን በቸልታ በመመልከታቸው ምክንያት ሕዝቡን የሚመለከት ከሆነ
እውነት ፈራጅ እግዚአብሔር ቅጣቱ ከባድ ነውና ሊታሰብበት ይገባል። … መላው ሕዝበ ክርስቲያን በዓላችሁን ከእነሱ ጋር
እንዳታከብሩ ትጠየቃላችሁ። እነሱ ባሉበት በዓል አታክብሩ፤ ቅዳሴ አታስቀድሱ። አምላካችሁን የናቀ እናንተን አያከብርም፤
አምላኩን ከጠላና ከናቀ ሰው በረከት አይገኝም። እግዚአብሔር በነቢዩ በሚልክያስ፤ “እናንተ ካህናት ስሜን አርክሳችኋልና
እኔም በረከቴን እነሣችኋለሁ፤” ብሏል። እግዚአብሔር ቢያሾፉበት የሚወድ አምላክ አይደለም። “እናንት ጎድን ጎድን ብትሄዱ እኔም
ጎድን ጎድን እሄዳለሁ፤” ብሏል። እነ አቡነ ጳውሎስ እምቢ ብለው በራሳቸው የዐመፅ ጎዳና ቢሄዱም እናንተም እነሱን ተከትላችሁ
ወደ ዐመፅ ብትሄዱ ፍርድ ያገኛችኋል። … መላ ኢትዮጵያውያን መንግሥትም የአቡነ ጳውሎስን እርምጃ እንድታስቆሙ በኢትዮጵያ
አምላክ ስም ተማጽኜ አቤቱታዬን አቀርባለሁ።” (ትኩረት፤ ጳጉሜ ፭ ቀን ፲፱፻፹፰ ዓ. ም.)
የቤተ ክርስቲያናችን አብዛኞቹ ካህናትና ምእመናን ግን የአባታችንን ምክር ባለ መቀበል አሁንም ከፓትርያርኩና ከግብር አበሮቻቸው ጋር በመቆማችን ምክንያት ፓትርያርኩና ግብር አበሮቻቸው ምንም የፀፀት ምልክት አላሳዩም። ይልቁንም የዐመፅ ሥራቸውን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ሄዱ እንጂ። አብዛኛዎች ካህናት ለኑሮአቸው ምክንያት በመስጠት፥ ምእመናን ደግሞ ምንም ቤተ ክርስቲያን የነሱ መሆኗ ቢታወቅም እኛን ምን አገባን የሚል ምክንያት በመስጠት የቤተ ክርስቲያንን ችግር ችላ በማለት አሁንም ከከሓዲዎች ካህናትና ጳጳሳት ጋር በመተባበራቸውና ገንዘባቸውን በቤተ ክርስቲያን በማፍሰሳቸው ከዐመፁ ሥራ ተባባሪነት ማምለጥ አልቻሉም። ምክንያቱም ፓትርያርኩም ሆኑ ግብር አበሮቻቸው የጥፋት ሥራቸውን ለማከናወን የሚጠቀሙት ከምእመናን በተሰበሰበው ገንዘብ ነውና። በሌላ በኩልም ለቤተ ክርስቲያን ከኛ በላይ ተቆርቋሪ የለም ባይ የሆኑ አንዳንድ ቡድኖች በቤተ ክርስቲያን ውሥጥ ባለፉት ፲፰ ዓመታት የደረሱትን የትምህርተ ሃይማኖትና የሥርዓት መፋለሶች፥ እንዲሁም በደሎች ችላ በማለት ብቻ ሳይወሰኑ በቤተ ክርስቲያን ምንም ችግር ያልደረሰ በማስመሰል አሁንም በ"ጉባኤ"፥ በ"መዝሙር"ና በ"መንፈሳዊ ጉዞ" ስም ሕዝበ ክርስቲያኑን በማዘናጋት ለአባ ጳውሎስና ለግብር አበሮቻቸው ያላቸውን አጋርነት በማስመስከር ላይ ናቸው። በሊቃውንት ጉባኤ የተላለፈውን ውግዘትም ምእመናን እንዳይከተሉ የተለያዩ ስንኩል ምክንያቶችን በመደርደር ዕንቅፋት ሆነው ይታያሉ። ይህም ሁኔታ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያባባሰው ይገኛል። ስለዚህ ካህናትና ምእመናን ወገኝተኝነታቸውን ለዐመፀኞችና ለከሓዲዎች ማድረጋቸውን አቁመው ከሐሰተኞች መምህራን በመለየት ለቤተ ክርስቲያንና ለእምነቷ እንዲሁም ለሥርዓቷ በመቆም ቤተ ክርስቲያንን ከወደቀችበት ዐዘቅት ለማውጣት ቢሞክሩና ከእግዚአብሔር ፍርድ ለማምለጥ ቢጥሩ መልካም ነው።
እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያናችንን ከችግሯ ለማላቀቅ የሚያስችለንን ኃይልና ልቡና ያድለን። አሜን።