«ተንሥአ በከመ ይቤ።» «እነሣለሁ እንዳለ ተነሣ።» (ማቴ፤ ም ፳፰፥ ቍ ፰።)
ሰው እግዚአብሔር የሰጠውን ትእዛዝ በመተላለፉ ምክንያት በሕይወቱ ሞት ተፈረደበት። «አንተ መሬት ነህ፤ ወደ መሬት ትመለሳለህ፤» ተባለ።
ማንኛውም ወንጀለኛ በሠራው ጥፋት ሲፈረድበት ሁለት ዐይነት መቀጫ አለ። ከእነዚህም አንዱ ሕግን በመተላለፉ የሚከፍለው መቀጫ ሲሆን፤ ሁለተኛው ለተበዳዩ የሚከፍለው ካሣ ነው። አዳም ሕግን በመተላለፉ በሥጋው ወደ መቃብር፥ በነፍሱ ወደ ሲኦል መውረድ ተፈርዶበት በሞተ ሥጋ፥ በሞተ ነፍስ ተቀጣ። ካሣ ግን የሚከፍለው አልነበረውምና እግዚአብሔር ሰው ሆኖ ካሠለት። ስለዚህም ከሕይወት ወደ ሞት እንደ ሄደ ከሞት ወደ ሕይወት መመለስ ያስፈልገው ነበር። ስለዚህ ሰው የሆነው አምላክ በሞቱ ሞትን አጠፋለት። በመቃብሩም ሙስና መቃብርን አስቀረለት። በትንሣኤውም ትንሣኤን መሠረተለት። ይህን የቤዛነት ሥራ ለመፈጸም ክርስቶስ የሄደበትን የመስቀል ጉዞ ስንመረምር ከመሥዋዕትነቱ ማለት ከስቅለቱ፥ ከሞቱ ተነሥተን ትንሣኤውን ዕርገቱን እናያለን። ለሰውም የሰጠውን አዲስ ሕይወት እንመለከታለን።
ጌታችን ኀሙስ ማታ ሥጋውን ደሙን ለደቀ መዛሙርቱ ከሰጠ በኋላ በጌቴሴማኒ የአትክልት ቦታ ሲጸልይ ቆይቶ በይሁዳ አማካይነት ለአይሁድ ተሰጠ። ተይዞ ታሰረ። ተገፈፈ፤ ተገረፈ፤ ተሰቀለ፤ ሞተ። ወደ መቃብር ወረደ። በሦስተኛውም ቀን ከሙታን ተለይቶ ተነሣ። ስለዚህም፤ «ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ዘተንሥአ እሙታን፤» እያልን እናመሰግነዋለን። ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የሚለው ቃል፤ በምስጢረ ሥላሴ ሦስት ጊዜ ቅዱስ ካለ በኋላ እግዚአብሔር የሚለውን ቃል ያስከትላል። በዚህ ግን ቅዱስ እግዚአብሔር ቅዱስ ኃያል ቅዱስ ሕያው ዘኢይመውት ይላል። ምስጢረ ሥጋዌ ነው። ይህ ዘተወልደ ካለ ጀምሮ ዘተጠምቀ ዘተሰቅለ ዘተንሥአ የሚለውን ጨምሮ መዋዕለ ፅንስን፥ መዋዕለ ውርዙትን፥ መዋዕለ ስብከትን በእነዚህ ጊዜዎች የተፈጸመውንም ሥርዐት ትስብእትን በየክፍሉ የሚያሳይ ነው። ከዚህም ጋር ጌታችን ቅድስት ነፍሱን ከክብርት ሥጋው ከለየባት ዘጠኝ ሰዓት ጀምሮ እስከ እሑድ ሌሊት ስድስት ሰዓት ድረስ ሠላሳ ሦስት ሰዓት ይገኛል። ከዚህም እስከ ዘጠኝ ሰዓት ያለው ሦስት ሰዓት ሲጨመር ሠላሳ ስድስት ሰዓት ይሆናል። ይህም ጌታችን በዚህ ዓለም ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ለሕያዋን ያስተማረውን ትምህርት፤ እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ አነጋገር፤ «ቀኝ እጄን ሰጠኋቸው፤ ጥምቀትም ሆነቻቸው፤» ላላቸው ለሙታን ወንጌል እንደ ሰበከላቸው እናያለን። የሥጋውያኑ በዓመት የሙታኑ በሰዓት ተለክቷል። ፊተኛው ሥጋዊ፥ ሁለተኛው ነፍሳዊ ነው። ከዚህ በኋላ እነሣለሁ እንዳለ ተነሣ። ደቀ መዛሙርት አንድም ሁለትም እየሆኑ ወደ መቃብሩ እየሄዱ ብሥራተ ትንሣኤውን ከመላእክት አንደበት ቢሰሙም በሙሉ ሐሳባቸው አላመኑም ነበር። ስለዚህ በትንሣኤው ቀን ማታ ጌታችን ራሱ ደቀ መዛሙርት ተሰብስበው ወዳሉበት ቤት በዝግ ደጅ ገብቶ የተወጋ ጎኑን፥ የተቸነከረ እጁን እግሩን አሳይቶ፤ «እኔ ነኝ፤ እመኑ፤ አትጠራጠሩ፤» በማለት ትንሣኤውን ከሰበከላቸው በኋላ፤ «በሙሴ ኦሪት በነቢያት፥ በመዝሙር የተጻፈው ሊፈጸም እንዲገባው አስቀድሞ ነግሬአችሁ አልነበረም?» አላቸው። ይህንንም ብሎ ልባቸውን ከፈተላቸው። መጻሕፍቱንም አስተዋሉ፤ ትንሣኤውንም አመኑ። በዚህም በዘፍ ም ፵ ቍ ፱፥ ሆሴ ም ፲፫ ቍ ፲፬፥ መዝ ም ፲፩ ቍ ፮፥ መዝ ም ፷፯ ቍ ፩፥ መዝ ም ፸፯ ቍ ፶፭ የተጻፈውን፥ የመሰለውንም ሁሉ እንዲያውቁ አድርጓቸዋል። ይህን በመጻሕፍት ቃል ሃይማኖትን የማወቅ ጸጋ በዚያን ጊዜ ከነበሩት ጀምሮ እስከ ዓለም ፍጻሜ ለምእመናን ሁሉ ይሰጣል።
ከተነሣም በኋላ መጽሐፈ ኪዳንን አስተምሯቸው በተነሣ በዐርባ ቀን ወደ ሰማይ ዐረገ፤ በአብ ቀኝ ተቀመጠ። ዕርገቱም እንደ ኤልያስ በእሳት ፈረስ፥ በእሳት ሠረገላ፥ እንደ ሄኖክ፥ እንደነ ዕዝራ በነፋሳት አይደለም። ሁሉን ቻይ ኃያል እንደ መሆኑ መጠን በፊት በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና እንደ ተወለደ፥ በመዋዕለ ስብከቱም እንደ ጥርጊያ ጎዳና በባሕር ላይ እየተራመደ፥ ማዕበልን ሞገድን እየጠቀጠቀ ሲሄድ እንደ ታየ፤ በዕለተ ዕርገቱም ነፋሳትን እየጠቀጠቀ፥ ደመናትን እየተራመደ ወደ ሰማይ ዐረገ እንጂ ምክንያት አልፈለገም። ሲዐርግ በታየበት ቦታ ወደፊት ይመጣል፤ ይህን እናምናለን። እስከዚህ የእሱ ትንሣኤ ነው።
ከዚህ ቀጥሎ የእኛን ትንሣኤ በመጠኑ እናያለን። በአዳም ምክንያት ሁላችን እንደ ሞትን በክርስቶስ ቤዛነትም ሁላችን እንነሣለን። (፩ ቆሮ፤ ም ፲፭፥ ቍ ፳።) የሰዎች ትንሣኤ ሁለት ዐይነት ነው። አንደኛው በዮሐንስ ወንጌል ም ፭ ቍ ፳፭ - ፳፯ የተገለጠው ትንሣኤ ልቡና ነው። ይህንንም ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፤ «እውነት እውነት እነግራችኋለሁ፤ ሙታን የእግዚአብሔርን ልጅ ቃል የሚሰሙባት ቀን ትባላለች እሷም ዛሬ ናት፤ የሚሰሙም ይድናሉ፤» በማለት ገልጾታል። ይህም በራእይ ም ፳ ቍ ፫ - ፯ ያለውን ያጠቃልላል። ሁለተኛው በዮሐንስ ወንጌል ም ፭ ቍ ፳፰ - ፴ የተገለጠው ትንሣኤ ሥጋ ነው። ይህንንም ጌታችን፤ «በመቃብር ያሉ ሁሉ ድምፅን የሚሰሙባት ጊዜ ትመጣለች፤ መልካም የሠሩ ለሕይወት፥ ክፉ የሠሩ ለቅጣት ይነሣሉ፤»በማለት የተናገረው ነው። ይህም በራእይ ም ፳ ከቍ ፱ እስከ መጨረሻው የተገለጸውን ያጠቃልላል። ሰው ሁሉ ጌታችን በሚመጣበት ጊዜ ከሞት ይነሣል። በማይለወጥ ሕይወትም ይታደሳል። ቅዱስ ጳውሎስ፤ «የመጨረሻው መለከት ሲነፋ ሁላችን በቅጽበት እንለደጣለን፤ ይህ የሚሞተው የማይሞተውን፥ ይህ የሚለወጠው የማይለወጠውን ይለብሳልና። የሚለወጠው የማይለወጠውን፥ የሚሞተውም የማይሞተውን በለበሰ ጊዜ ሞት በመሸነፍ ተውጦ ሞት ሆይ ሥልጣንህ የት አለ! መቃብር ሆይ አሸናፊነትህ የት አለ! የተባለው ይፈጸማል፤» ብሏል። (፩ ቆሮ ም ፲፭፥ ቍ ፴፮ - ፶፯።)
የዛሬ በዓል በተለመደው ቋንቋ በዓለ ትንሣኤ ይከበራል። ነገር ግን ቁርባን የለም፤ በረከት የለም፤ ጸጋ የለም፤ ጥምቀት የለም፤ ሥርየት፥ ጸጋ የለም፤ ሥርየተ ኃጢአት የለም። ይሁን እንጂ ጾሙን ጾም ውሎ የሚበላ አለ። ብዙ ምእመናንም የእግዚአብሔር መሆናቸውን ዐውቀው ቃለ ግዝቱን አክብረው በቤተ ክርስቲያን የደረሰውን ጉዳት ተመልክተው በጾም በጸሎት ከእግዚአብሔር ጋር የቆዩ እንዳሉ ዐውቃለሁ። ብዙዎች በየዋሻው፥ በየበረኃው፥ በየዱሩ፥ በየሸንተረሩ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አቤት የሚሉ መኖራቸውን አምናለሁ።እነዚያ ይህን በዓል እንደሚጠብቁት እረዳለሁ። በየቤተ ክርስቲያኑ ተሰብስበው ለይስሙላ የሚያጨበጭቡት ግን ፍርዳቸውን ይቀበላሉ። ይህ በዓል ክርስቶስ ደሙን ያፈሰሰላቸው፥ በደሙ የዋጃቸው ክርስቲያኖች በዓል እንጂ አባ ጳውሎስ በውስጥ የገዟቸው ሰዎች በዓል አይደለም። በእውነተኛ ሃይማኖት፥ በትሕትና፥ በንጽሕና ጾሙን አክብራችሁ እግዚአብሔርን ደጅ ስትጠኑ የቆያችሁ ሕዝበ ክርስቲያን እንኳን ለዚህ ታላቅ የትንሣኤ በዓል አደረሳችሁ።
በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ድል መንሣትን የሰጠን እግዚአብሔር ይክበር ይመስገን። አሜን።
አለቃ አያሌው ታምሩ።
(ሚያዝያ ፲ ቀን ፲፱፻፺ ዓ∙ ም∙)