መግቢያየሕይወት ታሪክመጻሕፍትየድምፅ ማኅደርቃለ ውግዘትግምጃ ቤት
 



እኛ የእግዚአብሔር እንጂ የዓለም አይደለንም።

(አለቃ አያሌው ታምሩ)

«እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ እነሱም ከዓለም አይደሉም።» (ዮሐ፤ ፲፯፥ ፲፮።)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን፡፡

«ንዑ ትልዉኒ።» «ኑ ተከተሉኝ።» (ማቴ፤ ፬፥ ፲፱።)

«ወንትልዎ ለፍጹም መልአክነ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘተዐገሠ ኀፍረተ መስቀል አናኅስዮ በእንተ ፍሥሓሁ ዘጽኑሕ ሎቱ ወመነና ለኀፍረት፤ ወነበረ በየማነ መንበረ እግዚአብሔር።» «ፍጹም አለቃችንን ኢየሱስ ክርስቶስን እንከተለው፤ ኀፍረተ መስቀልን የታገሠውን፤ አቃሎ፤ ለእሱ ስለ ተጠበቀው ደስታው ኀፍረትን የናቃትን፤ በእግዚአብሔር የጌትነት ክብርም ተቀመጠውን፡፡» (ዕብ፤ ፲፪፥ ፲፪።)

ምእመናን! አባቶቻችን ሲናገሩ፤ «ክፉ ባላጋራ ይተክላል፤ መልካም ባላጋራ ይነቅላል፤» ይሉ ነበር፡፡ በድሮ ጊዜ ኢትዮጵያውያን የርስት ባለቤት በነበሩበት ጊዜ የሚነሣ የርስት ክርክር ነበር፡፡ አንዳንዱ ባላጋራ አነሳሡ በሐሰት መሆኑን ሲያውቅ ድነበሩን ለይቶ የሚያውቅ ሽማግሌ እስኪታጣ፥ ምስክር እስኪጠፋ አንገቱን ቀብሮ፤ ወዳጄ፥ ወንድሜ ሲል ቆይቶ ጊዜ ጠብቆ ነው የሚነሣ፡፡ አንዳንድ ችኩል ደግሞ በአንድ ጊዜ ሁሉን ያገኘ እየመሰለው በተለይም ሀብት፥ ሹመት፥ ወይም ወገን ያገኘ ሲመስለው ያንንም ያንንም እንቅ እንቅ ያደርጋል፡፡ ሁሉን ልያዘው፥ ልጨብጠው ይላል፡፡ ያን ጊዜ ሰዎችን ያነቃቸዋል፡፡ ሰዎችም ወሰኑን፥ ድንበሩን፥ ሕጉን፥ ወጉን፥ ሐረገ ትውልዱን፥ ታሪኩን በሚያውቁ ምስክሮችና ሽማግሌዎች አስመስክረው፥ በብሔራዊ ዳኛ፥ በሕዝባዊ ሸንጎ ተከራክረው ርስታቸውን ከመነጠቅ፥ መብታቸውንም ከመገፈፍ ያድናሉ፡፡

በአሁኑ ጊዜ እንደሚታየው ጠላት የዘራቸው የእንክርዳድ ዘሮች፥ የጠላት ልጆች ትምህርተ ሃይማኖታችንን ሊያፈልሱ፥ ቤተ ክርስቲያናችንን ሊያፈርሱ እየታገሉን ነው፡፡ በሀብታቸው በሹመታቸው የሚያደርሱት ዐመፅ፥ ግፍ፥ ረገጣ ሳያንስ ጥቅማቸውን ለማስከበር ብቻ የመንግሥት መስለው ከመንግሥት ሊያጋጩን ይሞክራሉ፡፡ አባ ገሪማና አባ ጳውሎስ፥ ተባባሪዎቻቸውም የራሳቸው ናቸው እንጂ እግዚአብሔርም የመንግሥትም አይደሉም፡፡ እኛ የእግዚአብሔር እንጂ የዓለም አይደለንም፡፡ እነ አባ ገሪማ ባልዋልንበት ሊያውሉን፥ ባልተሰለፍንበት ሊያሰልፉን፥ ባልተመደብንበት ሊመድቡን ይፈልጋሉ፡፡ እነሱ በልብስ ቤተ ክርስቲያንን፥ በጠባይ ሰይጣንን፥ በሸር ፖለቲካን ተጠግተው መሥራቱን ለምደውታል፡፡ በስንዴ መሐከል ጠላት የዘራው እንክርዳድ ቡቃያው ስንዴ ቢመስልም በአደገ ጊዜ ይለያል፡፡ እነ አባ ገሪማም ክርስቲያን ያውም መነኮሳት ከዚያም አልፎ ጳጳሳት ቢመስሉም ሲገቡ መሰሉ እንጂ አሁን ግን እያደጉ ሲመጡ ማንን እንደሚመስሉ ለግብር አባታቸውም ዳግማውያን እየሆኑ መምጣታቸው በሥራ እየተገለጠ ነው፡፡ እኛ ጥሪኃችን የእግዚአብሔር ነው። «ኑ ተከተሉኝ፤» ብሎ የጠራን መሪያችን፥ ፊታውራሪያችን እኛን ለማዳን ሲል በቀራንዮ ዐደባባይ ግንድ ተሸክሞ፥ ጨርቅ አጠርቅሞ የዋለው ሰማይን፥ ምድርን፥ ባሕርን በውስጣቸው ያለውንም ሁሉ ፈጥሮ የሚገዛ ሁሉን ቻይ፥ ኃያል፥ ምንም የማይጎድለው ባለ ጠጋ ሲሆን በአይሁድና በሮማውያን ፊት ራቁቱን ሲቆም፥ ሲገፈፍ፥ ሲገረፍ፥ ሲቸነከር፥ ሲሰቀል ቅር ያላለው፥ ኀፍረተ መስቀልን የታገሠው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ አዝማቻችንም፤ «ፍጹም አለቃችንን ኢየሱስ ክርስቶስን እንከተለው፤» እያለ ወደፊት የሚገሠግሠው ቅዱስ ሐዋርያ ነው፡፡ እኛ ከዓለም አይደለንም፡፡ የማንኛውም ፖለቲካ ቡድን አዳባሪዎች፥ አጫፋሪዎች፥ አጀርጃሪዎችም አይደለንም፡፡ ይህ ጠባይ ያላቸው ሌሎች ናቸው፡፡ ጥያቄዎቻችን፤ «የተቀበሉትን ዐደራ ያልጠበቁት ፓትርያርክና ሊቃነ ጳጳሳት በቤተ ክርስቲያንና በምእመናኖቿ ላይ ከሚፈጽሙት ዐመፅና በደል ይመለሱ፤ ይታገሡ። ክብረ ቤተ ክርስቲያንን አይርገጡ፤ አያስረግጡ። ሃይማኖቷን፥ ትምህርቷን አያፋልሱ፤ ሥርዓቷን አይጣሱ፤ ሕጓን አያፍርሱ። በመምህራኖቿ ወንበር ከተቀመጡ በሚቀርብላቸው ሃይማታዊ ጥያቄ ሃይማኖታዊ መልስ ይመልሱ፡፡ ከዚያ አልፎ የምእመናኖቿን ደም ዐውደ ምሕረት ላይ አያፍስሱ፡፡ ይህን ካደረጉ ደግሞ፤ «ነፍስ አትግደል፤ ወንድምህን በከንቱ አታሳዝን፤» ያለውን አምላካዊ ሕግና ብሔራዊ መንግሥታዊ ሕግ የጣሱ ያፈረሱ እነሱ ናቸውና በሕግ ለፍርድ ይቅረቡ እንጂ ሌላውን በሐሰት አይክሰሱ፤» የሚሉ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ከተዘረዘሩት ጥቄዎች የትኛው ነው ሃይማኖትን ከለላ አድርጎ መንግሥትን ለመቃወም የተነሣ ነው፥ ወይም በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ላይ ለመሪዎቿ መቅረብ የማይገባው ነው የሚባለው የትኛው ነው; ጥቄዎቻችን በሙሉ መንፈሳውያን፥ ሕጋውያን፥ ኢትዮጵያውያን፥ ኦርቶዶክሳውያን ናቸው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት ላይ ለመሪዎች፥ ለአስተማሪዎች መቅረብ የሚገባቸው ትምህርታውያን ናቸው፡፡ እርግጥ ዓለማውያንና ፖለቲካውያን አይደሉም፡፡ አዎ፡፡ ለነ አባ ገሪማና ለደጋፊዎቻቸው ሊጡላቸው አይችሉም፡፡ ስለዚህም በሆነላቸው ጊዜ በጉልበታቸው በሥልጣናቸው ሊያጠቁን፥ ሳይሆንላቸው ደግሞ ከመንግሥት ሊያጋጩን ይፈልጋሉ፡፡ አዲስ አይደለም፡፡ ያረጀ ያፈጀ የካህናትና የሮማውያን ፖለቲካ ነው፡፡ በቀራንዮ ዐደባባይ የተፈጸመው ያስረዳል፡፡ የአይሁድ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስ ሕዝብ ለመንግሥት (ለቄሣር) ግብር እንዳይከፍሉ ቅስቀሳ ደርጋል እያሉ በሮማውን ዳኝነት ሲከሱ፥ ኦሪትን ነቢያትን ሊሽርባችሁ ነው እያሉ ሕዝቡን ሲያነሳሡ፥ ሲቀሰቅሱ መዋላቸው፤ ሮማውን ጭፍሮችም ከካህናት ጉቦ፥ መቅቡጥ፥ ገንዘብ ተቀብለው እኛ እንደ ተኛን ደቀ መዛሙርቱ ሰርቀው ወሰዱት እያሉ ትንሣኤውን ማስተባበላቸውን ቅዱስ ወንጌል ገልጾታል፡፡ ከዚያ ቀን እስከ ዛሬ በዓለም እየተነገረ ነው። የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ገዢዎና ግብረ በላዎች ከጌቶቻቸው በተማሩት ፈሊጥ እውነቱን በሐሰት እየለወጡ ቢከሱን አንደነቅም፡፡

አንደኛ፡- ለጥቅማቸው የቆሙ፤

ሁለተኛ፡- እውነቱ ቢጋለጥ በሰውም በእግዚአብሔርም ፊት ራቁታቸውን እንደሚቀሩ ስላወቁ ነው፡፡ መንግሥት የራሱ የሆነ የአመራር ሥርዓት አለው፡፡ ማንም ሊያጭበረብረው አይችልም፤ አይገባምም፡፡ ጥያቄያችን ይኸው ነው፡፡ ከስንዴ ጋር በቤተ ክርስቲያን የተዘሩት እንክርዳዶች ይነቀሉ፡፡ ከበጎች ጋር በበጎች ስፍራ የተቀላቀሉት ተኵላዎች ይለዩ፡፡ በክርስቶስ ስም በሐዋርያዊት መንበር ላይ ሠርጎ ገብቶ የተቀመጠውና የሚያጭበረብረው፥ መንግሥትን ከቤተ ክርስቲያን፥ ቤተ ክርስቲያንን ከመንግሥት ለማጋጨት የሚሞክረው ሰይጣን ከመንበሩ ይውረድ፤ ከቤተ ክርስቲያን ይሰደድ፡፡ «ተፈጸም ወፃእ መንፈስ ርኩስ፤» «አንተ ርኩስ መንፈስ አንዱን ከአንዱ ማጋጨትህን፥ የሆነ ያልሆነ መቀባጠርህን ትተህ ውጣ፤» የሚል ነው የምእመናንና የቤተ ክርስቲያን ጥያቄ፡፡ ይህ መሆኑ እየታወቀ እነ አባ ገሪማ የሚያግተለትሉት ዘባተሎ ቋንቋ ትርጉም የለሽ ነው፡፡

በነገራችን ላይ ለመሆኑ ጥር ፰ የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ በርእሰ አንቀጹ የጻፈው አስተያየት ምን ለማለት፥ ምን ለማሳየት ፈልጎ ነው፡፡

አንደኛ፡- ኢትዮጵያ ከእነዚህ ስድስት ዓመታት በፊት ሃይማኖት አልባ እንደ ነበረችና በአሁኑ ጊዜ ሃይማኖትን እንዳገኘች፤

ሁለተኛ፡- ቀደም ሲል ኢትዮጵያ የአንድ ሃይማኖት ደሴት ተብላ ሌሎች ሲቸገሩ እንደ ነበሩ፤

ሦስተኛ፡- የእምነት ነጻነት የተገኘው በታጋዮች ደም እንደ ሆነ፤

አራተኛ፡- ጥር ፩ ቀን በቅዱስ እስጠፋኖስ ቤተ ክርስቲያን የቀረበውን ጥያቄ ያለ ቦታው የቀረበ ካስመሰለ በኋላ በዘመናዊ መሣርያ ታጥቀው ለጸሎት ለምስጋና በተሰበሰቡት ምእመናን ላይ ባሩድ እንደ ክረምት ዝናም ያርከፈከፉትን ወንጀለኞች የተገፉ፥ የተበደሉ ጻድቃን አስመስሎ ሲያቀርብ፤ የተገደሉትን፥ የተደበደቡትን፥ ሃይማኖታዊ ጥያቄያቸውን በቦታው በሚገባው ያቀረቡትን ኮንኖአል፡፡ እሱ ማነው; ብዕሩስ የማነው; ከዚያም አልፎ በኅብረት ልንታገላቸው ይገባል ሲል ጥሪ አቅቦአል፡፡ እሱ ማነው; አስቀድመን ወደ ታሪክ እንመለስ፡፡ አንደኛ፡- ኢትዮጵያ ከዓለም አህጉር በፊት ሃይማኖት ያላት፥ ያለ ሃይማኖት የኖረችበት ጊዜ የሌለ ሲሆን በዚህም ብሉይ፥ ሐዲስ ስለሚመሰክሩላት ማንም ጣቱን ሊቀስርባት፥ አንደበቱን ሊሰነዝርባት አይችልም፡፡

ሁለተኛ፡- የአንድ ሃይማኖት ደሴት ትባል ነበር ለማለት ሞክረዋል፡፡ መባል ብቻ አይደለም ናት፡፡ ማንም ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት በፊት የተሰበከ የለም፡፡ «ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ፤» ብሎ በልቡ አምኖ፥ በአፉ ታምኖ ከተጠመቀው ኢትዮጵያዊ በቀርም ሌላ ተወዳዳሪ ባለ ታሪክ የለም፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ አለን አለን፥ ፈጀን ፈጀን የሚሉት ልዩ ልዩ የሃይማኖት ድርጅቶች ሁሉ ከ፬፻ ዓመት በኋላ የተነሡ፥ ግማሹ በስደት ሌሎችም በፖለቲካ ወታደርነት የመጡ እንጂ መሠረታውያን ባለቤቶች አይደሉም፡፡ ይህን ራሳቸውም ያውቁታል፡፡ ያም ሆኖ በየጊዜው ራሳቸው በሚያደርጉት ስርሰራ፥ ቡርቦራ እንጂ በሃይማኖታቸው ምክንያት የፈለጉትን ሃይማኖት ስለያዙ የደረሰባቸው ከሰሳ፥ ወቀሳ የለም፡፡

እነሱ የፈጸሙትን ሥራ በጉዲት፥ በግራኝ፥ በሱስንዮን ዘመን፥ በአድዋ፥ በማይጨው፥ በአምባላጌ፥ በሰለክለካ፥ በኦጋዴን ጦርነት የተደረገባቸው ሜዳዎች፥ አደባባዮች በልዩ ልዩ ጸሐፊዎች የተዘገቡ ታሪኮች ይመሰክሩታል፡፡ ክርስቲያኑም እስላሙም ይህን ያውቃል፡፡ «ሃይማኖት የግል ነው፤ አገር የጋራ ነው፤» የሚለው አዋጅም በአጤ ኃይለ ሥላሴ መነገሩንና መታወጁን፤ ከዚያ ጊዜ ጀምሮም ክርስቲንንም እስላምም በእኩልነት መተዳደራቸውን፤ የካቶሊክ መንበር፥ የመካነ ኢየሱስ ወንጌላዊት ቤተ ክርስቲያን፥ የአንዋር መስጊድ በይፋ መክፈታቸውን፤ ካቶሊክ፥ ፕሮቴስታንት፥ እስላም የሆኑ ሚኒስትሮች፥ አገረ ገዢዎች፥ በጦር በሲቪል ይሠሩ የነበሩ ሹማምንትና ባለ ሥልጣኖች እንደ ነበሩ ታሪክ ከሚያውቀው በላይ ያን ጊዜ የነበሩ ዛሬ ያሉ ዕድሜአቸው የ፵ የ፶ ዘመን የሆኑ ሰዎች የሚያውቁት፥ የሚመሰክሩት ነው፡፡ የዛሬው የአዲስ ዘመን ርእሰ አንቀጽ ጸሐፊ ይህን ሁሉ የሚተቸው፥ ያውም ደግሞ በግል ጉዳያችን ገብቶ የሚፈተፍተው፥ ከዚያም አልፎ መንግሥትንና ክርስቲያኑን ሕዝብ ለማጣቆስ የሚሞክረው ከየት መጥቶ፥ የት ኑሮ፥ መቼ ተወልዶ ነው; አዎ አዲስ ዘመን፡፡ ለመሆኑ ጋዜጣው (አዲስ ዘመን) ይህን ስም ያገኘው መቼ ነው; ርእሰ አንቀጽ ጸሐፊው ያውቀዋል; ጋዜጣው ስሙን ያገኘው፥ አዲስ ዘመን በመባል የተሰየመው ከአጤ ኃይለ ሥላሴ፥ በአጤ ኃይለ ሥላሴ ዘመንና ታሪክ ነው፡፡ እስከ ደርግ ዘመን ድረስም በዚሁ ስሙ የዘውድን መንግሥት ይልቁንም የአጤ ኃይለ ሥላሴን ታላቅ ሰውነትና ከፍተኛ መሪነት፥ ጥልቅ አስተዋይነት፥ ሰፊ ችሎታና ቸርነት፥ ፖለቲካና ጀግንነት ሲመሰክር ኖሮአል፡፡ በደርግ ዘመንም በሶሺያሊስት ኢትዮጵያ ይህንኑ ስሙን እንደ ያዘ በአዲስ ዘመን ኮሚኒስታዊ ቋንቋ ደርግን ሲያሞካሽ፥ በፈጸመው ሥራ ሁሉ ደርግን ሲያሞግስ ኖሮአል፡፡ አሁን ደግሞ በዘመነ ኢሕአዴግ ለሦስተኛ ጊዜ በዚያው ስሙ ማለት በአዲስ ዘመን ዘውድንና የቀደመውን አስተዳደር እያማ ኢሕአዴግን ሲያመሰግን፥ የዕለት ተለት ሥራውንም እጋነነ ሲያወራ እያየን እየሰማን ነው፡፡ አይ አዲስ ዘመን! እውነትም በየቀኑ አዲስ ዘመን፡፡ «ያለ ዛሬ ጥሩ ወጥ በልቼ አላውቅም የሚል መራቂ ወዳጁን ሳያውቀው ያረጃል፤» ይባላል፡፡ አጤ ኃይለ ሥላሴንም፥ ደርግንም፥ ኢሕአዴግንም በአንድ ቋንቋ ሲያመሰግን ፶ ዘመን አለፈው፡፡ ወዳጁን ሳያውቀው ማርጀቱ ነው፡፡ ለዚህም የሚያበቁት ከእውነት ውጪ የራሳቸውን አስተሳሰብ በሌላው አእምሮ ለማሳደር የሚጣጣሩ ጸሐፍት ናቸው፡፡ ነገሩ ስላነሳሣኝ እንጂ እኔ በጋዜጣው የሥራ ጉዳይ የፈለገውን ቢያማ፥ የፈለገውን ቢያመሰግን ግድ የለኝም፡፡ ግን ቤተ ክርስቲያናችንን ለመጻረር፥ ክብረ ሃይማኖታችንን ዝቅ ለማድረግ፥ በእኛ ላይ ጉዳት ለማድረስ፥ ሞራላችንንም ህልውናችንንም ለመጉዳት የመንግሥትን ሥራ ሽፋን አድርገው የሚዋጉን ሁሉ እንዳወቅንባቸው ሊያውቁን እንደሚገባ ማሳወቅ እወዳለሁ፡፡ የእስልምና እምነት የተለየ መሥመር ያለው ነው፤ አያከራክርም፡፡ ያም ቢሆን የድሮዎቹ ሳይሆኑ የዛሬ የዛሬ ጸሐፊዎች ከወሰን እያለፉ እንደ ጻፉ በቅርብ ጊዜ ተመልክቼአለሁ፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ በገዛ መጽሐፋችን ሃይማኖታችንን ሊያስተምሩን እንደ ሞከሩ ተመልክቼአለሁ፡፡ ከፈለጉ መድረኩ ይከፈትና፥ ፈቃደኝነታቸውን ይግለጡና፥ መንግሥትም ይወቀውና በመጽሐፍ ቅዱስ ሳይሆን በቁርዓን እውነቱን መነጋገር እንችላለን፡፡ በክርስትና ስም ከልዩ ልዩ አገር የዘመቱብን፥ ልዩ ልዩ ወሬ የሚያወሩብን ክፍሎችም የእኛይቱ እናታችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከሰበከችው ሌላ ከአውሮፓ፥ ከአሜሪካ ያመጡት ሌላ ኢየሱስ ካለ፥ ወይም ቤተ ክርስቲያናችን የማታውቀው ሌላ መንፈስ ካለ፥ ወይም ቤተ ክርስቲያናችን ያልሰበከችው ሌላ ወንጌል ካለ መድረኩ ይከፈትና ያቅርቡት፤ እንይላቸው፤ እንስማላቸው፤ ያስረዱን፤ እናስረዳቸው፡፡ ያለበለዚያ የእምነት ነጻነት በሚል ሽፋን በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚደርጉትን ወረራ ያቁሙ፡፡ እግዚአብሔር አንድ ነው፤ ሃይማኖት አንድ ነው፤ ጥምቀትም አንዲት ናት፡፡ የታወቀ ሃይማኖታዊ መሥመር ከሌለው ሀገር በቀር በማንኛውም ዓለም አህጉር ለአንድ መንግሥት አንድ ሃይማኖት ነው፡፡ ይህን የሚያስተባብል የለም፡፡ በኢትዮጵያ ብቻ እንደ ክረምት አግባ ምድር ያፈራችው ሃይማኖት ሁሉ ብሔራዊ መሆን አለበት የሚባለው አስተሳሰብ ትክክል አይደለም፡፡ ማንም ሰው የወደደውን ሃይማኖት ሊይዝ፥ በዚያው ሊኖር ይችላል፡፡ ሁሉ ብሔራዊ ሃይማኖት መሆን አለበት የሚለው አስተሳሰደብ ግን እውነት አይደለም፡፡  ሃይማኖት ከመባል ጥያቄ ውጪ ነውና፡፡ ተከራክሮ አሸንፎ መንበሩን መያዝ ይቻላል። ያለዚያ በወሬ እያታለሉ፥ በገንዘብ እየደለሉ የሕዝብን መንፈስ መበረዝ፥ ያለዚያም መንግሥትንና ሕዝብን በማጋጨት ያውም በማያገባ እየገቡ ደም ለማፋሰስ መሞከር ለአንድ አገር ጉዳትን እንጂ ጥቅምን አያመጣም፡፡ ለእኔ እንደሚሰማኝ ከሆነ ለመንግሥትም ቢሆን ዓለም የወለደውን ሃይማኖት ሁሉ ተሸክሞ እንኳን ሥራ ሊሠራ ለእነሱ ቦታ መድቦ ማኖሩ እንኳ የሚያስቸግረው ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ ሊያስብበትና በኢትዮጵያዊ አስተሳሰብ ለአንድ ሀገር፥ ለአንድ መንግሥት አንድ ሃይማኖት ያውም ጎረቤት፥ ውሽማ የሌላትን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖን ቢመርጥ፥ እሷንም ቢጠብቅ የሚሻለው ይመስለኛል፡፡ በኢሕአዴግ ዘመነ መንግሥት በሥራው ተገምግሞ ለአንድ ሥራ ይበጃል፥ ይበቃል ተብሎ መመረጥ የተለመደ እንደ ሆነ ሁሉ፥ ተገምግሞ ቀሎ፥ ጎድሎ፥ እምነቱን አጉድሎ ሲገኝም ከነበረበት መሻር፥ መውረድ በሕግ መጠየቅም የተለመደ ሆኖአል፡፡ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችም ተባባሪዎቻቸውም ይሆናሉ ተብለው ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብተው ነበር፡፡ አድገው፥ ተሹመው፥ ከብረው ነበረ፡፡ አሁን ግን ለተመረጡበት ሳይበቁ ስለ ቀሩ፥ ቀልለው፥ ጎድለው፥ እውነት አጉድለው ስለ ተገኙ ከወንበራቸው መውረድ፤ በቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት በታቦተ እግዚአብሔር ፊት ሰው በመግደል፥ ደም በማፍሰስ የእግዚአብሔርንም የመንግሥትንም ሕግ ተላልፈው ስለ ተገኙ ለሕግ እንዲቀርቡ፤ መንግሥትም ከቤተ ክርስቲያን ጎን ሆኖ በወንጀለኞች ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ እንጠይቃን፡፡ እኛ መሪያችን ክርስቶስ ነው፡፡ የምንከተለውም እሱን ነው፤ የምናዳምጠውም የእሱን ጥሪ ነው፡፡ የማንም ፖለቲካ ፓርቲ ተከታዮች አይደለንም፡፡ የክርስቶስ እንጂ የዓለም አይደለንም፡፡ ሁሉም ይህን ይወቅልን፡፡ ከዚህ ጋር አንድ ነገር ላስታውስ፡፡ ፓትርያርኩ በጥምቀት በዓል ላይ በአንድ በኩል ባለፉት ቀኖች የተደረገውን በቀል የሚያስታውስ ዛቻ የተሞላበት ቃል ሲነዙ በሌላ በኩል ደግሞ ከዚህ በፊት እንዳልተጠየቁ ሆነው ጥያቄ የሚያቀርብ ካለ ጥያቄውን ለመቀበል ዝግጁ መሆናንውን፥ በራቸው ክፍት መሆኑን ሲያስተጋቡ ነበር፡፡ ይህም በራዲዮ ተላልፎአል፡፡ እኔን ያስደነቀኝ፤ «የተበደለ ቢኖር፤» ሲሉ የተናገሩት ቃል ነው፡፡ በደል ብቻ ሳይሆን መግደል የፈጸመ ሰው በእግዚአብሔርም በሰውም ፊት ሲዋሽ ማየት መስማት ምን ያህል አሳፋሪ ነው; በብዙ ሺሕ የሚቆጠር ምእመን ባለበት ጥይት እንደ አፈር ሲረጩ፥ ሲያስረጩ ውለው ጻድቁን ገድሎ፥ አስገድሎ ሳይከሰሱ መቅረብ፥ ከሕግ ፊት አለመቅረብ እንዲህ እንደልብ ያናግር ይሆን; እግዚአብሔር ይስማው፤ እግዚአብሔር ይየው፤ እግዚአብሔር ይፍረደው፡፡

(ጦማር ጋዜጣ፤ ጥር ፲፬ ቀን ፲፱፻፹፱ ዓ∙ ም∙ )

ተጨማሪ ገጾች
 ዜናዎች
 አስተያየቶትን ይጻፉልን
 የ aleqayalewtamiru.org አባል ይሁኑ
ይህንን ገጽ ለወዳጆችዎ ያሳውቁ።
የኒውስሌተራችን ተጠቃሚ ይሁኑ
በየጊዜው የሚደረጉ ለውጦችን ለማወቅ ይመዝገቡ።
ሙሉ ሥም
የኢሜይል አድራሻ
መውረድ የሚችሉ ፋይሎች
የክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ የመንፈቅ መታሰቢያ። (.zip, 28.3 MB)
የክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ የመንፈቅ መታሰቢያ። (light weight) (.zip, 2.4 MB)
Unable to read the text?
Download Font (nyala.ttf, 427KB)
For PC users: download and save the font file in "C:\Windows\Fonts" folder and restart your browser
(Nyala.ttf, © 2006 Microsoft Corporation. All Rights Reserved. Nyala is either a registered trademark or a trademark of Microsoft Corporation in the United States and/or other countries.)
 
መግቢያየሕይወት ታሪክመጻሕፍትየድምፅ ማኅደርቃለ ውግዘትግምጃ ቤት
Copyright  , aleqayalewtamiru.org