«እግዚአብሔር ያጥናችሁ የሚባል ሰው የለኝ፤ ኀዘንተኛዪቱም ሟቺቱም እኔው ነኝ።» (ቤተ ክርስቲያን።)
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን።
«ንዑ ትልዉኒ።» «ኑ ተከተሉኝ።» (ማቴ፤ ፬፥ ፲፱።)
«ይበጽሕ መዋዕል አመ ይነሥእዎ ለመርዓዊ እምኔሆሙ ይእተ አሚረ ይጸውሙ።» «ሙሽራውን ከእነሱ የሚወስዱበት ቀን አለ፤ ያን ጊዜ ይጾማሉ።» (ማቴ፤ ፱፥ ፲፬ - ፲፯። ሉቃ፤ ፭፥ ፴፫ - ፴፰።)
የተወደዳችሁ ምእመናን ሕዝበ ክርስቲያን! በታላቂቱ፥ በነባሪቱ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዐት ይህ ሳምንት የቅበላ ሳምንት ሲባል ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ለ፶፭ ቀናት ከእግዚአብሔር ጋር የምንቆይበት ወርኀ ጾም፥ የጾም ወራት ነው። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዐት ዓመት ክፍላተ ዘመን አሉት። ክፍላተ ዘመን መደባቸው ፺ ቀን ሆኖ በ፺ ቀን ውስጥ ደግሞ የተከፋፈሉ ወቅቶች አሉ። ይህ ያለንበት ክፍለ ዘመን በግእዙ ቋንቋ ሐጋይ (በጋ) ይባላል። የዋእይ ምግብና አለው። የሙቀት ዘመን ነው። ነገር ሁሉ ያልበሰለው ይበስላል፤ ያልደረቀው ይደርቃል፤ ይታጨዳል፤ ይወቃል፤ በሪቅ፥ በጎታ በጎተራ ይከተታል። «በየካቲት ነገር ክተት፤» ይባላል።
በሌላ በኩልም በቤተ ክርስቲያን የውሥጥ ሥርዐት ዘመነ ልደት፥ ዘመነ አስተርእዮ፥ ዘመነ መርዓዊ ወይም ቅበላ ተብሎ ይከፈላል። ዘመነ መርዓዊ፥ ቅበላ የሚባለው ከጾመ ነነዌ ፋሲካ እስከ ዐቢይ ጾም መግቢያ ዋዜማ ዘወረደ እሑድ ያለው ቀን ነው። ሙሽራ ያለው ቤተሰብ በማንኛውም ሰዓት ሙሽራውን መጠበቅ እንዳለበት ክርስቲያኖችም ሙሽራውን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመቀበል የሚዘጋጁበት ሳምንት ነው። ጌታችንን ሙሽራ ስንል በእኛ ዐሳብ፥ ግምገማ የሰጠነው ስም አይደለም። መጥምቁ ዮሐንስ፥ የሙሽራው ሚዜ፤ «ሙሽራ ያለችው እሱ ሙሽራ ነው፤» ሲል መስክሮለታል። በኋላ እሱ ራሱ፤ «ሙሽራው ከሚዜዎቹ መሐከል የሚወሰድበት ቀን ይመጣል፤» ሲል አጽድቆታል።
ቅዱስ ጳውሎስም፤ «የእግዚአብሔርን ቅናት እቀናላችኋለሁ፤ ለአንዱ ንጹሕ ድንግል ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ እሱ ላቀርባችሁ አጭቼአችኋለሁና፤» ይላል። ይህም በመሆኑ ሐዋርያት ጌታ በሰጣቸው ትእዛዝ መነሻነት በዲድስቅልያ መጽሐፋቸው በአንቀጽ ፳፱ ምእመናን የጌታን ጾም፥ የሕማሙንና የሞቱን መታሰቢያ በዓመት በዓመት እንዲያደርጉ፤ በጾማቸው ፍጻሜም በዓለ ትንሣኤውን እንዲያከብሩ አዝዘዋል። በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በትምህተ ሃይማኖቷ በተሠራው ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን ለ፶፭ ቀናት የጌታን ጾም ትጾማለች። በዚህም፤ «ኑ ተከተሉኝ፤ መታሰቢያዬን አድርጉ፤» ያለውን ተቀብላ የእሱን ጾም ትጾማለች። የሕማሙን፥ የሞቱን መታሰቢያ ታደርጋለች።
ጾመ ኢየሱስ ይባላል። እሱ የጾመው፥ ከእሱ የተቀበልነው ነውና። ዐቢይ ጾም ይባላል። እስከ ፶፭ በሚደርሱት የቀኖች ቁጥር ምሳሌነት የሰው ዘር በመንጸፈ ደይን ወድቆ በእግረ አጋንንት ሲጠቀጠቅ፥ በሥቃየ ገሃነም በፍዳ ቁራኝነት ሲጨነቅ የኖረበት የ፭ሺ፭፻ ዘመን ዓመተ ፍዳ፥ ዓመተ ኩነኔ ተፈጽሞ በክርስቶስ ጾም፥ በክርስቶስ ሕማም በሰማይ በምድር ነጻነትን፥ በጠላቱ በሰይጣን ላይ ድል አድራጊነትን ያገኘበት ነውና። ስለዚህ ዐቢይ ይባላል። ለዚህ ጾም ተመሳሳይ፥ እኩያ፥ ጓደኛ የለውም። ፈሪሳውያን የጌታ ደቀ መዛሙርት የእሱን ዐይነት ጾም እንዲጾሙ ጠይቀውት ነበር። እሱ ግን፤ የአዲስ ልብስ እራፊ በአሮጌ ልብስ ላይ አይጣፍም፤ ብሎ አምላክ ራሱ ጾሞ ለምእመናኑ የሰጠው የክርስቲያን ጾም ከሰው ሠራሽ ሊነጻጸር፥ ሊመሳሰል፥ ሊደባለቅና ሊቀላቀል እንደማይችል አስረድቷል። በኋላ ዘመን የተነሡት ተፈታታኞች ደግሞ፤ ጾም የለም፥ እሱ ጾሞልናል፤ የሚሉ ሆነው ተገኝተዋል። ክርስቶስ ግን፤ «የሙሽራ ሚዜዎች ሙሽራው ከእነሱ ጋር ሳለ ሊጾሙ አይችሉም፤ ግን ሙሽራው ከእነሱ የሚወሰድበት ቀን ይመጣል፤ ያን ጊዜ ይጾማሉ፤» በማለት በጊዜው የሥርዐት መሥራች ጓደኛ እንደ ሌለው፤ በኋላ ግን ምእመናን ሁሉ በጾም ሊመስሉትና ሊከተሉት እንደሚቻላቸው፥ እንደሚገባቸውም አስረድቷል።
በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለተከታዮቿ የአምላካቸውን ጾም ታውጃለች። በዚህ ጊዜ ያለው የቤተ ክርስቲያን ሥርዐት እጅግ ልዩ ነው። ፍጹማኑ የዕረፍት ጊዜ የላቸውም። ወጣንያኑና ማእከላውያኑም ቤተ ክርስቲያን የሰጠቻቸውን መመሪያ ተከትለው በሥርዐት ይጾማሉ። ካህናት ሌሊቱን በሰዓታት ያድራሉ። ቀንም እግዚአብሔር ለቅዱስ ያሬድ በገለጸው መመሪያ መሠረት ከመዝሙረ ዳዊት፥ ከልዩ ልዩ ቅዱሳት መጻሕፍት በዜማ በተቀናበረው ጾመ ድጓ፥ ምዕራፍ፥ ዝማሬ በተባለው ክፍለ መዝሙራት በጸሎት፥ በምስጋና እግዚአብሔርንና ቤተ ክርስቲያኑን ሲያገለግሉ ይውላሉ። የመዓልት ሰዓታትና ምህላም አለ። ከዚህም ጋር፤ «ሰብሕዎ ለእግዚአብሔር ስብሐተ ሐዲሰ።» «እግዚአብሔርን አዲስ ምስጋና አመስግኑት፤» ተብሎ በቅዱሳት መጻሕፍት በመታዘዙ (መዝ፤ ፺፭፥ ፩፣ ፺፯፥ ፩።) እንደየአግባቡ አዲስ የቅኔ ድርሰት ይታከልበታል።
በዚህ የጾም ወራት አበው የጌታን ነገረ ስቅለቱን በሚያስታውስ ሥርዐት ከ፲፰ እስከ ፳ ሰዓታት የሚውሉት በጾምና በአገልግሎት ነው። ይህም ኢትዮጵያን ከማንኛውም አሳዛኝ ፈተና ለረጅም ጊዜ ጠብቆ የኖረ ነው። የዚህ መጓደልም ነው በ፳ኛው ክፍለ ዘመን ይልቁንም በእነዚህ ፳፭ ዓመታት ኢትዮጵያን ከነሕዝቧ በመከራና በውርደት አዘቅት ውስጥ የጣለ። ይህም በግዳጅ አልመጣም። ኢትዮጵያውያን ራሳቸው በፖለቲካ ውዥምብር ስለ ተጠመዱ፥ ሃይማኖታቸውን ስለ ካዱ፥ ዓላማቸውን ስለ ሳቱ፥ የባዕድ ወራዳ ጠባይ ስለ ጎተቱ እንጂ አሁንም እንመለስ። ልዑል እግዚአብሔር አሁንም በጾም በጸሎት ወደ እኔ ተመለሱ፤ እኔም ወደ እናንተ እመለሳለሁ፤ ልብሳችሁን ሳይሆን ልባችሁን ቅደዱ፤ መለከት ንፉ ማለት ምከሩ፥ አስተምሩ፥ ቀስቅሱ፥ ጹሙ ማለት በመብል አትጠመዱ፥ ማኅበራችሁን ቀድሱ፥ ከርኩሳን ተለዩ፤ ወንድ ሙሽራ ከጫጉላው፥ ሴት ሙሽራ ከመጋረጃዋ ይውጡ፤ ሰዎችን ሰብስቡ ጡት የሚጠቡ ሕፃናት ሳይቀሩ ፤ ለጌታቸው መሥዋዕት የሚያቀርቡ ካህናት ያልቅሱ ብሎአል። በዚህ መሠረት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ሰዓት ወስነው፥ ምግብ ለይተው፥ ዕረፍትና ምቾት ትተው ለረጅም ጊዜ ሲጾሙት ኖረዋል። ልዩ ምልክታቸው ነው።
እንደ ዛሬው፤ እግዚአብሔር ምን ሠራችሁ እንጂ ምን በላችሁ አይልም፥ የተፈቀደለትን ምግብ ከልክሎ በጾም ሥጋን መበደል በእግዚአብሔር ፊት ያስጠይቃል፤ የሚሉ ፌዘኞች ከመነሣታቸው አስቀድሞ ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን፥ ቤተሰባቸውን፥ አገራቸውን፥ ሃይማኖታቸውን፥ ክብራቸውን ከማንኛውም ጥፋት፥ ከማንኛውም ውርደት ጠብቀው የኖሩት በዚህ ማንም በማይቋቋመው በእግዚአብሔር ኃይል ነው።
በአሁኑ ጊዜስ የኢትዮጵያ የሕዝቧ፥ የቤተ ክርስቲያንስ ሕይወት እንዴት ነው? ብዙ መናገር ይቻላል። ግን ተከድኖ ይብሰል ካላልን በስተቀር ምን እንዳለ እናውቃለን። ይልቁንም በቤተ ክርስቲያን አንጻር ትምህርተ ሃይማኖቷ ፈልሷል፤ ሥርዐቷ ፈርሷል፤ ሕጓ ተጥሷል፤ ክብሯ ተገሷል። የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች ዓለም እንኳ በማያደርገው ሥጋዊ ኀይል ታጥቀው ግድያን፥ ድብደባን፥ ምዝበራን፥ ልዩ ልዩ ቅሌትን ከማካሄዳቸውም በላይ ሲኖዶሷን በማፍረስ ስለ ተፈታተኗት ሕልውናዋ በሞትና በሕይወት መካከል ይገኛል። አቤቱታ የሚሰማ ዳኛ የለም። አቤት የሚሉ ይታፈናሉ። በጠላትነት የተሰለፉባት ልዩ ልዩ ተቃዋሚ የእምነት ድርጅቶች የራቁትን በገመድ፥ የቀረበውን በጫማ ስፍር በመከፋፈልና በሀገረ ስብከቷ ላይ አዲስ ዓለም ለመመሥረት በመዘጋጀት ላይ ሲሆኑ፤ የውስጥ መሪዎቿና ቤተሰቦቿ ደግሞ ከውስጥ ግድግዳዋን፥ ከውጪ አጥሯን እያፈረሱ ለጠላት በማስረከብ መቃብር እንኳ እንዲተርፋት አላደረጉም።
የሚገርመው በውስጥም ሆነ በውጭ ቆመው ክንድ ለክንድ ተደጋግፈው ቤተ ክርስቲያኒቱን ለማፍረስ የሚጣደፉ ሁሉ የራሷ የቤተ ክርስቲያኒቱ ልጆችና የልጅ ልጆች መሆናቸው ነው። የዘመኑ ትውልድ የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከነ ሃይማኖቷ፥ ከነ ሥርዐቷ፥ ከነ ምልክቷ፥ ከነ ታሪኳ የራሱንና የአባቶቹን ታሪክ ከርሷ ጋር ዐብሮ ገድሎ፥ ቀብሮ የዕዝን ለመብላትና እግዚአብሔር ያጥናችሁ ለመባል የተዘጋጀ መስሎ ነው የሚታየው። ግን የቤተ ክርስቲያን ህልውና ከሌለ ገዳዩም፥ ማቹም ራሱ ዘመናዊው ትውልድ ነው። እግዚአብሔር ያጥናችሁ የሚናልም የለም። «እግዚአብሔር ያጥናችሁ የሚባል ሰው የለኝ፤ ኀዘንተኛዪቱም ሟቺቱም እኔው ነኝ፤» ትላለች ቤተ ክርስቲያን።
ምእመናን! ስለ ክብራችሁ፥ ስለ ቤተ ክርስቲያናችሁ፥ ስለ አምላካችሁ ክብር በእነ አባ ጳውሎስ፥ በጳጳሳቶቻቸው፥ በአለቆቻቸው፥ በካህናቶቻቸው፥ በግብር አበሮቻቸው ጒልበት የተፈጸመውን በደል በመዘርዘር፥ ልታደርጉት የሚገባችሁን በመዘከር አቤቱታ ማቅረብ ከጀመርኩ ድፍን ሁለት ዓመት ሆነኝ። አባ ጳውሎስና ግብር አበሮቻቸው ዓለም ሊያደርገው የሚጸየፈውንና የሚነቅፈውን፥ ሌላውን የሚነቅፍበትንና የሚከስበትን በደል ሁሉ በቤተ ክርስቲያን ላይ ያለማቋረጥ እየፈጸሙ መንግሥትም ሕዝብን እነሱን ዐቅፎ፥ አዝሎ ከመንከባከብና እሹሩሩ ከማለት በስተቀር ለራሱም ሆነ ለአገሪቱ የሚበጅ ሥራ መሥራት አልቻለም።
እንግዲህ በእኔ በኩል አቤቱታዬን ሁሉን ማድረግ ለሚቻለው ለኢትዮጵያ አምላክ ማቅረብ ብቻ ነው። እናንተም ምእመናን ፈቃዳችሁ ከሆነ በፖለቲካ ስብከት የሚደረደርላችሁን ሁሉ ወደ ጎን ትታችሁ በዚህ የዐቢይ ጾም ወራት በየቀኑ ጧትና ማታ ለተወሰኑ ደቂቃዎች በኃያሉ አምላክ ፊት ስለ ቤተ ክርስቲያናችሁ፥ ስለ ሃይማኖታችሁ፥ በዚህ ምክንያትም ከሚመጣው ፍርድ ለመዳን በእግዚአብሔር ፊት በመቆምና አቤቱታ በማቅረብ እንድትተባበሩኝ በኢትዮጵያ አምላክ ስም እጠይቃችኋለሁ። ግን በአሁኑ ጊዜ ሁሉን ነገር እንደ ፌዝ በመቊጠር የዓለማዊ ቋንቋ ትርጕም በመስጠት በየስብሰባው የአንድ ደቂቃ የሕሊና ጸሎት እንደሚባለው ዐይነት አድርጋችሁ እንዳትወስዱትና እንዳይፈረድባችሁ ዐደራ እላለሁ።
ኀሙስ ማታ በስቅለቱ ዋዜማ ሌሊት በጌቴሴማኒ የአትክልት ቦታ ጌታ የተናገረውን ላስታውሳችሁ። «ወደ ፈተና ወይም ወደ ጥፋት እንዳትገቡ ትጉ፤ ጸልዩ። መንፈስ ብርቱ ነው፤ ሥጋ ደካማ ነውና።» «ትግሁ ወጸልዩ ከመ ኢትባዑ ውስተ መንሱት፤ እስመ መንፈስ ይፈቅድ ወሥጋ ይደክም።» (ማቴ፤ ፳፮፥ ፵፩።) ስለዚህ ዐሳቤን እንደ ፌዝ ሳትቈጥሩ በየቤታችሁም ሆነ በቤተ ክርስቲያን፥ በሆነው ስፍራ ሁሉ ቢቻል፤ «ወአንበርኩ አንብዕየ፤» ብሎ ነቢዩ እንደ ተናገረ ከዕንባ ጋር በየቀኑ ጧትና ማታ ዐምስት ዐምስት ደቂቃ በኢትዮጵያ አምላክ ፊት በጸሎት ቁሙ። ስለ ሀገራችን ጸልዩ። አትጠራጠሩ። የኢትዮጵያ አምላክ ለጸሎታችሁ መልስ ይሰጣል። ጥሪዬ ለኢትዮጵያውያን ሁሉ ነው።
«ንዑ ስምዑን እንግርክሙ ኵልክሙ እለ ትፈርህዎ ለእግዚአብሔር።» «እግዚአብሔርን የምትፈሩ፥ የምታመልኩ ሁሉ ልንገራችሁ፤ ኑ ስሙኝ።»
አለቃ አያሌው ታምሩ።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ጉባኤ ዋና ሰብሳቢ።
(ማዕበል ጋዜጣ፥ የካቲት ፲፬ ቀን ፲፱፻፺ ዓ∙ ም∙)