መግቢያየሕይወት ታሪክመጻሕፍትየድምፅ ማኅደርቃለ ውግዘትግምጃ ቤት
 


ያለፈውን ማስታወስ በሚመጣው ለመጠንቀቅ ይረዳል።

(አለቃ አያሌው ታምሩ)

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን።

«ቀላይ ለቀላይ ትጼውዖ በቃለ አስራቢከ።» «በፏፏቴ ድምፅ ቀላይ ቀላይን ትጠራለች።» (መዝ፤ ፵፩ ፥ ፯።)

ታሪካዊ ንጽጽር ያላቸውን ጊዜዎች፥ ቦታዎች፥ ምክንያቶች በሚመለከት የተነገረ ቃል ነው። በተለይ መተርጕማን አበው፤ በሙሴና በኢያሱ ዘመን በኤርትራ፥ በዮርዳኖስ የተደረገውን ተአምር፥ ከዚያም ዐልፎ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ጊዜ የሆነውን ለመግለጽ ሰፊና ጥልቅ ትምህርት ሰጥተውበታል። የእኔ አስተሳሰብ ይህን አይመለከትም። እንደምታውቁት ዛሬ ኅዳር ፮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስንና የእመቤታችንን የቅድስት ድንግል ማርያምን ወደ ግብጽ መሰደድና በጊዜው ፍጻሜም ወደ ምድረ እስራኤል መመለሳቸውን መታሰቢያ በዓል የምታደርግበት ዕለት ነው። ይህ በዓል በቤተ ክርስቲያናችን ስያሜ ቍስቋም እየተባለ ይጠራል። ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆኖ በዚህ ዓለም በተገለጠበት ወቅት ከፈጸማቸው ሥራዎች የአንዳንዶቹ መታሰቢያ በቤተ ክርስቲያናችን የሚታወቀው ሥራው በተፈጸመበት ቦታ ስም ነው። ለምሳሌም ቃና ዘገሊላ፥ ደብረ ዘይት፥ ደብረ ታቦር፥ እንዲሁም ቍስቋም የመሳሰሉት ሁሉ ናቸው።

ቍስቋም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ልጇን ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አዝላ የሦስት ዓመት ከመንፈቅ የስደት ጉዞ ከፈጸመች በኋላ ወደ ምድረ እስራኤል ስትመለስ ለመጨረሻ ጊዜ በአፍሪካ ምድር በአንድ የፈረሰ ግንብ ውሥጥ ያደረችበት፤ «ወፍም ለራሷ ቤት አገኘች፤ ዋኖስም ግልገሏን የምታሳርፍበት አገኘት፤» ሲል ነቢዩ የተናገረው ትንቢት የተፈጸመበት ስፍራ ሲሆን፤ ከሦስት መቶ ዓመት በኋላ የእስክንድሪያ ሊቀ ጳጳሳት ቅዱስ ቴዎፍሎስ በእመቤታችን ስም ቤተ ክርስቲያን ሠርቶበታል። አገልግሎት ሲጀምርም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እናቱንና ሐዋርያቱን ይዞ በመገለጥ ቅዳሴ ቤቱን አክብሮለታል። ኢትዮጵያውያን ነገሥታትም ለዚህ በረከት ብዙ ተሳትፎ ያደርጉ እንደ ነበረ ታሪክ ይናገራል። ይልቁንም የዐፄ ኢያሱ እናት እቴጌ ምንትዋብ በሊቃውንቱ አስመክረው ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፭ ለሦስት ዓመት ከመንፈቅ የስደት ዘመን የዐርባ ቀን የጾም፥ የምስጋና፥ የበዓል መታሰቢያ ከማቆማቸውም በላይ በታላቁ የጥበብ መዲና የጎንደር ከተማ በእመቤታችን ስም ቤተ ክርስቲያን አሠርተው፥ ቦታውን ደብረ ቍስቋም አሰኝተው በየዓመቱ ኅዳር ፮ ቀን የአምላካችንና የእናቱ የእመቤታችን የስደት መታሰቢያ እንዲከበር አድርገዋል። ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክም የቀደሟቸውን አርኣያ በመከተል መንበረ መንግሥት ቍስቋም ቤተ ክርስቲያንን አሠርተው አነሆ ምእመናን በዓሉን በየዓመቱ ያከብሩታል።

ይህ በዓል በዚህ ብቻ የተሰወነ አይደለም። በዓለ እግዚአብሔር እንደ መሆኑ መጠን ጾሙ ጾመ ጽጌ ወይም የጽጌ ጾም፥ ምስጋናው ማኅሌተ ጽጌ፥ ግብዣው ጽጌ እየተባለ በመላ ኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያን የሚታሰብ ሲሆን፤ በልዩ ልዩ ስፍራ ደግሞ በቍስቋም ስም ብዙ አብያተ ክርስቲያን ተሠርተው በዓሉ ሲከበር ኖሯል። በዓሉ ስሙን ያነሣው ወይም ያገኘው ከቦታው ቢሆንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ግን የእመቤታችን መታወቂያ ሆኗል። ሌሎችም ይህን የመሰሉ አሉ። ለምሳሌ ፅንሰታ፥ ልደታ፥ በዐታ፥ ሕንጸታ፥ ኪዳነ ምሕረት እነዚህን የመሳሰሉ ሁሉ እየተለመዱ ሲሄዱ የመጠሪያ ስሟ ያህል የእመቤታችን መታወቂያ ሆነዋል። ፅንሰታ ማለት መፀነሷን፥ ልደታ ማለት መወለዷን፥ በዐታ ማለት ወደ ቤተ መቅደስ መግባቷን፥ ሕንጸታ ማለት በስሟ ቤተ ክርስቲያን መሠራቱን፥ ኪዳነ ምሕረት ማለት የዕርቅ ምልክት መሆኗል፥ አስታራቂ መሆኗን፥ ስለዚህም ከልጇ የተቀበለችውን ቃል ኪዳን የሚያመለክቱ ሲሆን፤ ቍስቋም ለስደት ከአገር መውጣቷን፥ ኋላም ወደ አገር መመለሷን፥ ስትመለስም ለመጨረሻ ጊዜ በአፍሪካ ምድር በዚህ ስፍራ ማደሯን የሚያመለክት ቃል ነው። አሁን የምንነጋገረው በታሪኩ ጫፍ ላይ ነው።

በዝርዝር ሳይሆን በማሳጠር፥ በመጠቅለልም ቢሆን ወደ ታሪክ እንመለስ። በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ የታሪክ መሥመር የኢትዮጵያ ዕድል ከዓለም አህጕር ልዩ፥ እጅግ በጣም ልዩ መሆኑን የማያውቅ ካለ እኛ ራሳችን ኢትዮጵያውያን ብቻ ነን፤ ከዚያም የዘመኑ ኢትዮጵያውያን ነን። እግዚአብሔር እንደ ልቤ የታመነ ሰው ሲል የጠራው ነቢዩ ዳዊት በመንፈስ ቅዱስ እየተቃኘ ከተናገራቸው ቃላት አንዱ በመዝሙር ፷፯ ቍ፤ ፴፩ ላይ የሚገኘው፤ «ይምጽኡ ተናብልት እምግብጽ፤ ኢትዮጵያ ታበጽሕ እደዊሃ ኀበ እግዚአብሔር፤» የሚለው ነው። ትርጕሙም፤ «ገባሮች ወይም አስታራቂዎች ከግብጽ ይምጡ፤ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች፤» ማለት ነው። ነቢዩ ይህንን የሚናገረው በኢትዮጵያ እንዳለ ሆነ ነው ማለት ነው። ተናብልት የሚለው የግእዝ ቃል ሁለት ትርጕም ያሳያል። በአንድ በኩል የዓመት ግብር ወይም ገጸ በረከት ይዘው ከመንግሥታት ወደ መንግሥታት የሚላኩትን መልእክተኞች የሚያመለክት ሲሆን፤ በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያውያን ነገሥታት ለረጅም ጊዜ ግብጽን የገዙበት ዘመን እንደ ነበረ የሚያስታውሰን ከመሆኑም በላይ በዐባይ ውሃ ምክንያት ግብጾች ለኢትዮጵያ ግብር ሲከፍሉ እንደ ነበረ ያመለክታል። በሁለተኛው ትርጕሙ ደግሞ አስታራቂዎች፥ አማላጆች ማለትን የሚያመለክት ሲሆን፤ በመጀመሪያ ክፍል እግዚአብሔር ዓለምን የታረቀበት ልጁ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስና፤ «አገሪቱን ርስት፥ ሕዝቧን ዐሥራት አድርጌ ሰጥቼሻለሁ፤» ብሎ ልጇ ጌታችን ቃል ኪዳን የገባላት እናቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በስደታቸው ጊዜ ከግብጽ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን፥ ኢትዮጵያም በጌታችን ልደት ከተደረገላት ትንቢታዊ ጥሪና ካገኘችው የእጅ መንሻ ማቅረብ ተሳትፎ ሌላ ሰው የሆነውን አምላክ አማኑኤልንና ወላዲተ አምላክን ንጽሕት ድንግል እናቱን በሃይማኖት፥ በክብር፥ በፍቅር እጇን ዘርግታ ለመቀበልና ለማስተናገድ መታደሏን ያሳያል።

በሁለተኛውም መተንብላን ሊቃነ ጳጳሳት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ማለት እስከ ፲፱፻፵ ዓመተ ምሕረት ድረስ ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን፥ ኢትዮጵያም እነሱን እየተቀበለች ስታስተናግድ መኖሯን ያመለክታል። በዚህ ታሪክ መሠረት ጻድቁ ዮሴፍ ሕፃኑን አማኑኤልንና እናቱን ይዞ ከሄሮድስ ሸሽቶ ወደ ግብጽ በመጣ ጊዜ ዕድሉ የግብጽ ብቻ አልነበረም፤ የኢትዮጵያም ጭምር ነበር። ነቢዩ ኢሳይያስ፤ «ጌታ በፈጣን ደመና ሆኖ ወደ ግብጽ ይወርዳል፤ የግብጽ የእጃቸው ሥራ ይነዋወጣል፤» ብሎ ሲናገር፤ (ኢሳ፤ ፲፱ ፥ ፩።) ነቢዩ ዕንባቆም ደግሞ፤ «ወፍኖቶሂ ዘእምዓለም ርኢኩ፤ አዕፃዳተ ኢትዮጵያ ይደነግፃ።» «ከጥንት የታሰበ መንገዱን አየሁ፤ የኢትዮጵያ አውራጃዎች ይደነግጣሉ፤» አለ። ጌታ ወደ ግብጽ ሲገባ አምልኮተ ጣዖትን ከግብጽ ለማፍረስ፥ ምድረ ግብጽን በኪደተ እግሩ ለመቀደስ ሲሆን፤ ወደ ኢትዮጵያ መግባቱ ደግሞ በኢየሩሳሌም በሄሮድስ ዘመን የነበረው መቅደስ ከጽላት፥ ከሕግ ባዶ ስለ ነበር፤ «መሥዋዕተ ወቍርባነ ኢፈቀድኩ መሥዋዕተ ዘበእንተ ኃጢአት ኢሠመርኩ ውእተ ጊዜ እቤ ነየ መጻእኩ ውስተ ርእሰ መጽሐፍ ተጽሕፈ በእንቲአየ።» «መሥዋዕትን ቍርባንን አልወደድኩም፤ ስለ ኃጢአት የሚቀርበውን መሥዋዕት አልወደድኩም፤ ብለሃልና በመጽሐፍ አርእስት ስለ እኔ እንደ ተጻፈ ያን ጊዜ እሺ በጄ ብየ መጣሁ፤» ሲል የተናገረውን ትንቢት ለመፈጸም ጽላትና ሕግ ወዳሉበት ወደ ኢትዮጵያ ወደ አኵስም ቤተ መቅደስ ለመግባት ፈቃዱ ስለ ሆነ ነው። ስለዚህ ሁለቱም አገሮች ማለት ግብጽና ኢትዮጵያ በረከተ ስደቱን ለመሳተፍ ታድለዋልና ጌታና እናቱ ከኢየሩሳሌም ወደ ግብጽ፥ ከግብጽም ወደ ኢትዮጵያ መጡ። ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡም ዛሬ ደብረ ዳሞ ቀድሞ ደብረ ሃሌ ሉያ ተብሎ በሚጠራው በአቡነ አረጋዊ ገዳም ሊቃነ መላእክት፥ ሠራዊተ መላእክት ሃሌ ሉያ እያሉ በዳዊት የምስጋና መዝሙር ተቀበሏቸው። ከዚያም ወደ አኵስም ቤተ መቅደስ ሲገቡ ሁሉን ቻይ አምላካችን የሚሳነው ነገር የለምና በዚያ ትንቢተ ነቢያትን ፈጸመ። ምሳሌም የውጣ አማናዊው አካላዊ ቃል ሲመጣ በኢየሱስ ተፈጸመ። ምሳሌዪቱ ጽዮንም በአማናዊት ጽዮን ድንግል ማርያም ታድሳ ወደ ሐዲስ ኪዳን ተላለፈች።

ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሃይማኖትን የተቀበሉ እንደ አባቶቻቸው በምሳሌ ሳይሆን በወልደ እግዚአብሔር ደም ታድሰውና ተቀድሰው ደቂቀ ጽዮን ተባሉ፤ አዋልደ ጽዮን ተባሉ። እምነ ጽዮን (እናታችን ጽዮን) ብለው ለማመን፥ ለማመስገን ታደሉ። ይህም በረከተ ስደት በምድረ ትግሬ ብቻ ሳይወሰን በመላው ምድረ ኢትዮጵያ ተዳርሶ ከዕንቢተኞች በቀር ዕድሉ ለአመኑ ሁሉ ተፈቅዷል። በዚህ ምክንያት ነው ከመስከረም ፳፮ እስከ ኅዳር ፮ የጾም፥ የምስጋና፥ የበዓል መታሰቢያ የታወጀው፤ ጸንቶ የኖረው። ዛሬ የቍስቋምን በዓል የምናከብረው በዚህ ምክንያት ነው። ቀደም ሲል፤ «በፏፏቴ ድምፅ ቀላይ ቀላይን ትጠራለች፤» ያልኩትም ግብጻዊት ገዳመ ቍስቋም፥ ደብረ ሃሌ ሉያ ደብረ ዳሞ፥ ደብረ ጽዮን አኵስም፥ ገዳመ ዋሊ ዋልድባ፥ ደሴተ ጣናና ገዳማቶቿ፥ መንዝና ምድረ ጉራጌ፥ ሌሎችም የኢትዮጵያ ቅዱሳት መካናት ታሪክ ያስተሳሰራቸው፥ የታሪክ ተዘምዶ ያላቸው መሆናቸውንና ዛሬ በቍስቋም ስም በዚህ ስፍራና በሌላ ቦታም የምናከብረው በዓል በታሪክ የፏፏቴ ምድፅ የሚገናኙ መሆናቸውን ለማመልከት ነው።

ያለፈን ማስታወስ በሚመጣው ለመጠንቀቅ ይጠቅማል እንዳልኩት አሁንም የማስታውሳችሁ ነገር አለ። በ፲፱፻፹፭ ዓመተ ምሕረት በዛሬው ቀን በመንበረ መንግሥት ቍስቍም ቤተ ክርስቲያን ተገኝቼ ይህንኑ ታሪክ የሚመለከት ሰፊ ትምህርት መስጠቴንና ታላቁ የትግሬ ክርስቲያን ሕዝብ የኢትዮጵያ አምላክ የሰጠውን ጣምራ ዕድል ከታሪክ ጋር አገናዝቦ መጠበቅ እንደሚኖርበት ያቀረብኩት ጥያቄ ያዘለ ማስታወሻ ትዝ ይለኛል። ምድረ ትግሬ ከታቦተ ጽዮንና ከጽላተ ኪዳን፥ ከሕገ ኦሪት ጀምሮ ለምድረ ኢትዮጵያ የልዩ ልዩ ሥጋዊና መንፈሳዊ በረከት ምንጭ፥ ቦይ ሆና መኖሯ የታወቀ ነው።

ከለውጥ ወዲህ ደግሞ ኢትዮጵያ ሰይጣንና ሠራዊቱ እየነቀነቁ ባመጡት የመከራ ማዕበል ተውጣ በምትገኝበት ጊዜ ልዑል እግዚአብሔር ሥጋዊና መንፈሳዊ ሥልጣን ለትግሬ ሕዝብ በመስጠቱ ቸርነቱ የዚህን ታላቅ ሕዝብ እምነት የሚያመለክት ስለሆነ፤ እምነቱ ጸንቶ ከትዝብት እንዲድን፥ አገሩንና ቤተ ክርስቲያኑንም ከውድቀት እንዲያድን ቀንም ሌትም ተግቶ መሥራት ያለበት መሆኑን ማስታወሴ ትዝ ይለኛል። በልዩ ልዩ ጊዜ ልዩ ልዩ ዐሳቦችን በመቈርቈር በቅንነት አቅርቤአለሁ። ተንኮለኞች ግን ቀናውን እያጣመሙ ብዙ አሉባልታ መንዛታቸውንንም ዐውቃለሁ። እኔ ግን ከእውነት በስተቀር በዚህ ታላቅ ሕዝብ ላይ መጥፎ አስተሳሰብ እንደሌለኝ አምላኬ ያውቃል።

ለፍርሃቴ ምክንያት ከሆኑ ነገሮች ግን ብዙዎቹ ተፈጽመዋል። የሥጋዊውን መሥመር ብንተወው እንኳ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ ከነ አክሊላቸው፥ ከነ ልብሰ ተክህኗቸው ለሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ወግባት (የጌታ ዐዳር) መግባታቸው፥ በተራ ምእመን ደረጃም ከፓፓው ቡራኬ መቀበላቸው፥ የክሕደትና የኑፋቄ መጽሐፍ ማሳተማቸውና መበተናቸው፥ ኦርቶዶክሳዊውን የሊቃውንት ጉባኤ ማፍረሳቸው፥ ተጠሪ የሆኑለትን ሲኖዶስ መሻራቸው፥ በኢየሱስ ክርስቶስና በመንፈስ ቅዱስ ፈንታ ርእሰ ቤተ ክርስቲያን፥ ለሲኖዶስ አመራር ሰጪ አድርገው ራሳቸውን መሰየማቸው፥ ሲኖዶሱን የግል ተጠሪአቸው ማድረጋቸው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን ልዕልና፥ የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ሃይማኖትን እውነትነት፥ የአኵስምንና የታላቁን የትግሬን ክርስቲያን ሕዝብ ታላቅነት የሚፈታተንና በትዝብት ላይ የሚጥል ነው።

ሌላው በደብረ ዳሞ አደገኛ ሁኔታ ላይ አባ ጳውሎስ ያሳዩት ፌዝ ወይም ቸልታ ነው። በነጻው ፕሬስ እንደ ተገለጠው በደብረ ዳሞ ቤተ ክርስቲያን ታሪካዊ ግምጃ ቤት ላይ የደረሰው አደጋ ነሐሴ ፲፫ ቀን ፲፱፻፹፰ ዓመተ ምሕረት ሲሆን ዜናው የተሰማው ግን ከስድሳ ቀን በኋላ ወይም ከሁለት ወር በኋላ ነው። አባ ጳውሎስም ቦታውን የጎበኙት ጥቅምት ፲፫ እና ፲፬ እንደ ሆነ ተነግሯል። እስከዚህ ለምን ተደበቀ? ለምን ተሸፈነ? የቦታው ርቀት ከልክሎ፥ መገናኛ ጠፍቶ አይመስልም። እንግዲያስ የተሰዓቱ ቅዱሳን ወደ ኢትዮጵያ መሰደድና የሮም ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሥራ፤ «በፏፏቴ ድምፅ ቀላይ ቀላይን ትጠራለች፤» እንደ ተባለው ዐይነት ስለ ሆነ አባ ጳውሎስ በደብረ ዳሞ በደረሰው አደጋ ላይ ያሳዩት ቸልታ፥ የፈጸሙት ፌዝ ከዚያ ተለይቶ አይታይም።

ሌላው የማስታውሳችሁ ባለፈው ዓመት በአኵስም ቤተ መቅደስ የጽዮን ማርያም በዓል በሚከበርበት ጊዜ ጳጳሳት ትምህርት በመስጠት ላይ ሳሉ አንድ ተአምራት ተደርጓል። ለረጅም ጊዜ በቤተ ክርስቲያኑ ውሥጥ የኖረ የወይራ ዛፍ ያለ አንድ ግፊት ድምፅ አሰምቶ ተሰንጥቆ በመውደቁ አደጋ ማድረሱ ይታወሳል። ይህ ምልክት ሃይማኖት አልባ ጳጳሳትና ፓትርያርካቸው በአኵስም ቤተ መቅደስ የሚፈጽሙትን ደባ፥ በደል፥ ተጋፊነት ሰዎች እያወቁ ዝም ቢሉም ሥነ ፍጥረት መስክሯል ማለት ነው። አሁን በቅርቡ ደግሞ የዓለም አብያተ ክርስቲያናት ጉባኤ በመቀሌ አስተናግደዋል። መቼም ለጽድቅ አለመሆኑ የታወቀ ነው። ጠላቶቻችንም በዚህ ዐይነቱ ሁኔታ ወዳጅ መስለው እየቀረቡ ነው ንዋያተ ቅድሳቶቻችንን የሚዘርፉት። በቅርቡ ቀን በነጻው ፕሬስ እንደ ተገለጠው የዓለም ልዩ ልዩ ክፍሎች አባል መሆናቸው በፎቶግራፍ ጭምር ተደግፎ ወጥቷል። ስለዚህም በደብረ ዳሞ የታየው ተንኮል የተሞላበት ሥራ በአኵስም እንዳይደገም ትልቅ ጥንቃቄ ያሻል። ነቢዩ፤ «ዕግትዋ ለጽዮን ወሕቀፍዋ ወተናገሩ ውስተ ማሕፈዲሃ ደዩ ልበክሙ ውስተ ኃይላ ወትትካፈልዎ ለክበዲሃ።» «ጽዮንን ክበቧት፤ ዕቀፏት፤ በቤተ መቅደሷ ስለ እሷ ተነጋገሩ፤ ታድነናለች፥ ትጠብቀናለች፥ ትረዳናለች ብላችሁ አምናችሁ ልባችሁን በልጇ በኃይሏ ላይ አሳርፉ፤ በረከቷን ትታደላላችሁ፤» ብሏል።

ስለዚህ የጸጋ ብኵርና የታደላችሁ እናንተ አኵስማውያን! ጳጳሳቶቻችንና ፓትርያርካቸውም እምነት የምንጥልባቸው ሆነው ስላልተገኙ ጽዮንን ከነክብሯ መጠበቅ የመላው ኢትዮጵያውያን ድርሻ መሆኑ ቢታወቅም በቅድሚያ የእናንተ ጥንቃቄ ያሻል።

አሁንም ታላቁ የክርስቲያን ሕዝብ ዳኝነት እንዲያይልኝ እጠይቃለሁ። አባ ጳውሎስና አባ ገሪማ ከነ ግብር አበሮቻቸው የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ልዕልና አዋርደዋል። መጻሕፍቶቿን በመለወጥ ላይ ናቸው። አቤቱታ ማቅረብ ከጀመርኩ ሁለት ዓመት ዐለፈ። ሌሎች ክርስቲያኖችና የምእመናን ኮሚቴ አባሎችም ከእኔ ጋር አቤቱታ ማቅረብ ከጀመሩ ሰባት ወር ዐልፏል። ጌታ፤ «እኔ በአባቴ ስም መጣሁ አልተቀበላችሁኝም፤ ሌላው በራሱ ስም ቢመጣ እሱን ትቀበላላችሁ፤» እንዳለው፤ ለኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንና ለአምላኳ ክብር፥ ለሃይማኖቷ፥ ለሥርዐቷ ይቆማሉ፥ ይከላከላሉ ተብለው የተሾሙ ጳጳሳት፥ መነኮሳት፥ የአድባራትና የገዳማት አስተዳዳሪዎች፥ ቀሳውስትና ዲያቆናት፥ የሰበካ ጉባኤ አባላት እግዚአብሔርን ንቀው ጥፋቱን እያወቁ ከአባ ጳውሎስ ጋር ወግነው እንኳን ዳኝነት ሊያዩ አቤቱታችንን መስማት አልፈለጉም። በመልእክተኛና በመንግሥት ፖስተኛ የላክነውን አቤቱታ ሳይቀር አንቀበልም ብለው የመለሱ አሉ። መንግሥትም በሃይማኖት ጉዳይ አያገባኝም ብሎ ዝም ብሏል። ሌላው ሕዝብ እንዳይናገር የመንግሥትን አባባል ለአባ ጳውሎስ ድጋፍ እንደ መስጠት የቆጠረው ይመስላል። ማለት ብንናገር መንግሥት ይጠላናል የሚል ዐሳብ ያለው ይመስላል። ስለዚህ ታላቁና ክርስቲያኑ የትግሬ ሕዝብ ትናንትም የታሪክ ባለቤት የነበርክ፥ ዛሬም የታሪክ ትዝብት የሚጠብቅህ፥ ከኢትዮጵያ አምላክ ታላቅ ዐደራ የተሰጠህ ስለ ሆንክ አባ ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚፈጽሙትን ዐመፅ እየተመለከትክ በቸልታ እንዳታልፈው፥ እውነቱን እንድትናገር፥ እውነቱን እንድትፈርድ በታቦተ እግዚአብሔት ጽዮንና በአምላኳ ስም ተማጽኜ አቤቱታየን አቀርባለሁ።

ክብር ምስጋና ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ይሁን። የእግዚአብሔር በረከት ለቤተ ክርስቲያናችንና ለልጆቿ ይሁን።

አለቃ አያሌው ታምሩ። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ጉባኤ ዋና ሰብሳቢ።

(ማዕበል ጋዜጣ፤ ኅዳር ፯ ቀን ፲፱፻፺፰ ዓ∙ ም∙ )

 

ተጨማሪ ገጾች
 ዜናዎች
 አስተያየቶትን ይጻፉልን
 የ aleqayalewtamiru.org አባል ይሁኑ
ይህንን ገጽ ለወዳጆችዎ ያሳውቁ።
የኒውስሌተራችን ተጠቃሚ ይሁኑ
በየጊዜው የሚደረጉ ለውጦችን ለማወቅ ይመዝገቡ።
ሙሉ ሥም
የኢሜይል አድራሻ
መውረድ የሚችሉ ፋይሎች
የክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ የመንፈቅ መታሰቢያ። (.zip, 28.3 MB)
የክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ የመንፈቅ መታሰቢያ። (light weight) (.zip, 2.4 MB)
Unable to read the text?
Download Font (nyala.ttf, 427KB)
For PC users: download and save the font file in "C:\Windows\Fonts" folder and restart your browser
(Nyala.ttf, © 2006 Microsoft Corporation. All Rights Reserved. Nyala is either a registered trademark or a trademark of Microsoft Corporation in the United States and/or other countries.)
 
መግቢያየሕይወት ታሪክመጻሕፍትየድምፅ ማኅደርቃለ ውግዘትግምጃ ቤት
Copyright  , aleqayalewtamiru.org