የዘመን መለወጫ በዓል የታወቀው ፫ ዐይነት ነው። አንደኛ እስራኤል በብሉይ ኪዳን ያከብሩት የነበረው ሚያዝያ ፩ ቀን፤ ሁለተኛ የዓለም ክርስቲያን የክርስቶስን ልደት ተቀዳሚ በማድረግ የሚያከብሩት ጥር ፩ ቀን፤ ሦስተኛ ኢትዮጵያ ጥንት መሠረቱን መሠረትነቱን ዐውቃ የምታከብረው መስከረም ፩ ቀን ነው። እስራኤል የዘመን መለወጫ በዓልን በሚያዝያ ማድረጋቸው፤ በዚሁ ወር ከግብጽ ባርነት ነጻ ስለ ወጡና እግዚአብሔር ይህንን የነጻነት በዓል በየዓመቱ እንዲያከብሩ ስላዘዛቸው መሆኑና የዓለም ክርስቲያን ጥር ፩ ቀን ማክበራቸው የክርስቶስን ልደት ምክንያት በማድረግ መሆኑ የታወቀና ብዙ ማተት የማያሻው ስለ ሆነ፤ ለወጣቶች አስቸጋሪ መስሎ ስለሚታያቸው ስለ ኢትዮጵያ ዐውደ ዓመት መስከረም ፩ ቀን ዐሳባችንን እንሰጣለን።
ኢትዮጵያ ይህንን በዓል የተቀበለችው ከካም ነው። የተጀመረበትም ካምና ኩሳ ልጁ ወደ ኢትዮጵያ የገቡበት፥ አኵስም በኩሳ ስም የተመሠረተችበት ጊዜ ነው። ዘመኑም በኢትዮጵያ ላይ ከአራት ሺሕ ዘጠኝ መቶ በላይ ሲሆን፤ ከጥፋት ውሃ በኋላ በኖኅ ዕድሜ በስድስት መቶ አንድ ዓመት ጀምሮ ሲከበር ዐምስት ሺሕ ዐምስት መቶ ዐምሳ ሁለት ዓመት አሳልፎ እነሆ ደርሰንበታል። ኖኅም ሲያከብረው ጥንቱን ዓለም የተፈጠረበት ወር እንደ መሆኑ መጠን፤ ከአዳም ጀምሮ የወረደ፥ በአበው እየተላለፈ እስከሱ የደረሰ እንደ መሆኑና ኋላም የቀላይ አፎች የተከፈቱበት፥ የጥፋት ውሃ መጕደል የጀመረበት፥ ለመጀመሪያ ጊዜ ከጥፋት ውሃ ወዲህ ክረምትና በጋ መፈራረቅ የጀመሩበት፥ ምድር የፍሬ ፅንስ የአበባ መልክ ያሳየችበት ስለ ሆነ ነው።
የፊተኛው ሲጨመር ሰባት ሺሕ አራት መቶ ዐምሳ ሁለት ዘመኖች ማሳለፉ ነው። ስሙም በግእዝ ርእሰ ዐውደ ዓመት፥ በዐማርኛ የዘመን መለወጫ፥ ዕንቍጣጣሽ፥ ቅዱስ ዮሐንስ እየተባለ ይጠራል። ርእሰ ዐውደ ዓመት ማለት የዘመን መለወጫ መጀመሪያ፤ ዕንቍጣጣሽ ማለት ዕንቍ ዕፅ አወጣሽ ብሎ የአበባውን መፈንዳት ወይም ዕንቍ ዕጣ ወጣሽ ብሎ መልካሚቱ ምድር ኢትዮጵያ በዕጣ ለካም መድረሷን የሚያመለክት፤ ቅዱስ ዮሐንስ ማለት በዓሉ ከመጥምቁ ዮሐንስ ዕረፍት ጋራ የተደጋገፈ መሆኑን የሚገልጥ ስለ ሆነ ነው።
በዕብራውያን ቍጥር በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር መስከረም ፩ ቀን የነበረው ጥቅምትን ይነካል። እግዚአብሔርም በ፯ኛው ወር ከወሩም በመጀመሪያ ቀን ለእግዚአብሔር የተቀደሰች በዓል አድርጉ፤ በዓሉም ተዝካረ (በዓለ) በጥቅዕ ይባላል ሲል ሙሴን ያዘዘው ስለዚሁ ነው። ይህም በዓል ለዓመት ጥንት እንደ መሆኑ መጠን የአውራኅም ጥንታቸው ነውና በዓመት ወሮች መጀመሪያ በመጀመሪያ ቀን ይከበራል። ምክንያቱም ለወር፥ ለዓመት ጥንት፥ መጀመሪያ ስለ ሆነ ነው። በዓለ መጥቅዕ፥ ተዝካረ መጥቅዕ መባሉም መጥቅዕ ደወል በተደወለ ጊዜ ሁሉን እንዲሰበሰብ፤ ይህም ልዑል እግዚአብሔር የሐልዮ የነቢብ ቃሉን ከሰጠበት ቀን ጀምሮ ዕለትን፥ ሰዓትን፥ ወርን፥ ዓመትን ሰብስቦ የሚያስገኝ ስለ ሆነ ነው። ስለ አቆጣጠሩ ፊትና ኋላ መሆን ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት፥ አይሁድ ሚያዝያ ፲፬ ቀን ያከበሩት የፋሲካ በዓል በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር መጋቢት ፳፯ ቀን እንደ ሆነ መመልከት ብቻ ሊያስረዳን ይችላል። (ዘሌ፤ ም ፳፫ ቍ ፳፫ና ፳፬።)
አባቶቻችን ጥንተ ፍጥረትን መጋቢት፥ ጥንተ ቀመርን ሚያዝያ ሲያደርጉ ሰምተናል። ማስረጃም ያደረጉት ቃል፤ «ይህ ወር የወሮች መጀመሪያ ይሁናችሁ፤» ያለውን ነው። እግዚአብሔር፤ ሚያዝያ የወሮች መጀመሪያ ይሁናችሁ ብሎ ሲያዝዝ ምክንያቱ ለጊዜው እስራኤል ከግብጽ ስለ ወጡበት፥ ኋላም የሰው ልጆች ከሲኦል ስለ ወጡበት እንደ ሆነ ግልጥ ነው። እግዚአብሔር የሚያዝያ ወር ለእስራኤል የወሮች መጀመሪያ እንዲሆን ሲያዝዝ፤ ለእስራኤል የነጻነት መጀመሪያቸው በመሆኑ እንጂ ጥንተ ፍጥረት በመሆኑ አይደለም። ይህስ ባይሆን ቀዳማዊውን ቀዳማዊ ባላለው ነበር፤ ስለ በዓልም ሚያዝያ በገባ በ፲፬ ቀን በዓለ ፋሲካን አክብሩ ብሎ በዓለ መጥቅዕን ሠርቀ ወርኅ (መባቻ) በጥቅምት እንዲያከብሩ ባላዘዛቸውም ነበር። (ዘፀ፤ ም ፲፬ ቍ ፪።)
እግዚአብሔር የፋሲካን በዓል እስራኤል በሚያዝያ እንዲያከብሩ ሲያዝዛቸው የመባቻን በዓል ደግሞ በ፯ኛው ወር መጀመሪያ እንዲያከብሩ፤ ይኸውም በዓለ መጥቅዕ ለፍጡራን ያይደለ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ በዓል መሆኑና ዐውቀው እንዲጠብቁት በማዘዙ፤ ጥንተ ፍጥረት፥ ጥንተ ወርኅ፥ ጥንተ ዓመት ያው በዕብራውያን አቆጣጠር ጥቅምት፥ በኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ግን መስከረም ተብሎ የሚጠራው መሆኑ ግልጥ ነው። ሚያዝያ ቀዳማዊ በሆነስ ኖሮ የመባቻን በዓል ሚያዝያ ፩ ቀን፥ ፋሲካንም በ፲፬ኛው ቀን አክብሩ በማለት ፈንታ ከሚያዝያ አውጥቶ ለሌላ ወር ባልሰጠውም ነበር።
መስከረም ማለትም እግዚአብሔር ከዚህ እስከ ብሩህ ሰማይ ድረስ መልቶ የነበረውን ውሃ ከሦስት ከፍሎ በጠፈር፥ በሐኖስ፥ በውቅያኖስ ከወሰነ በኋላ ደረቁ ይገለጥ ባለ ጊዜ፤ ምድር ገበሬ አርሶ አለስልሶ እንዳከረማት ሁሉ ለዘር የተመቸች ሆና ተገኝታ ነበርና መሐሰ (ቈፈረ)፥ ከረመ (ከረመ) የሚሉትን ሁለቱን ግሶች በማቀነባበርና በማስተባበር መስከረም አጥብቆ ታርሶ ከረመ እንደ ማለት ስሙን ከግብሩ ነሥቶ የሚጠራበት ነው። ክቡር አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም አታሚን አታኒም የተባለውን ቃል ሲተረጕሙ አታን ወይም ኤታን ማለት ጥንተ ፍጥረት እንደ ሆነ ዕብራይስጢውን በማዋሐድ ገልጠው ይኸውም በዕብራውያን ፯ኛ ወር ጥቅምት፥ በኢትዮጵያውያን በፀሓይ አቈጣጠርና በአቡሻክር ጠንቃቃ ቍጥር ግን መስከረም መሆኑን አስረድተዋል። (የግእዝ መዝገበ ቃላት ፪፻፵፱ ገጽ ተመልከት።)
መስከረም ማለትም እግዚአብሔር ከዚህ እስከ ብሩህ ሰማይ ድረስ መልቶ የነበረውን ውሃ ከሦስት ከፍሎ በጠፈር፥ በሐኖስ፥ በውቅያኖስ ከወሰነ በኋላ ደረቁ ይገለጥ ባለ ጊዜ፤ ምድር ገበሬ አርሶ አለስልሶ እንዳከረማት ሁሉ ለዘር የተመቸች ሆና ተገኝታ ነበርና መሐሰ (ቈፈረ)፥ ከረመ (ከረመ) የሚሉትን ሁለቱን ግሶች በማቀነባበርና በማስተባበር መስከረም አጥብቆ ታርሶ ከረመ እንደ ማለት ስሙን ከግብሩ ነሥቶ የሚጠራበት ነው። ክቡር አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌም አታሚን አታኒም የተባለውን ቃል ሲተረጕሙ አታን ወይም ኤታን ማለት ጥንተ ፍጥረት እንደ ሆነ ዕብራይስጢውን በማዋሐድ ገልጠው ይኸውም በዕብራውያን ፯ኛ ወር ጥቅምት፥ በኢትዮጵያውያን በፀሓይ አቈጣጠርና በአቡሻክር ጠንቃቃ ቍጥር ግን መስከረም መሆኑን አስረድተዋል። (የግእዝ መዝገበ ቃላት ፪፻፵፱ ገጽ ተመልከት።)
፸ወ፬፻ ፶ወ፫ ዓመተ ዓለም በዘመነ ማቴዎስ ወእምኔሁ ፶ወ፭፻ ዓመተ ኵነኔ ፲ወ፱፻ ፶ወ፫ ዓመተ ምሕረት እያለች ደምራ፥ ዘርዝራ፥ ዐጥፋ፥ ነጥላ፥ ጠቅልላ፥ ከፍላ የምትሰጠው የዘመን ቍጥርም የጥንትነቷ ፍሬ ነው። መስከረም ፩ ቀን በዓል ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ለክብራችን፥ ለታሪካችን ጥንት መሠረት ነውና ዐውቀን እንጠቀምበት። (ኩፋ፤ ም ፯ ቍ ፲፱ - ፴።)
(የኢትዮጵያ እምነት በሦስቱ ሕግጋት፥ ፲፱፻፶፫ ዓ∙ ም∙፥ ገጽ ፪፻፴፫ - ፪፻፴፭)