መግቢያየሕይወት ታሪክመጻሕፍትየድምፅ ማኅደርቃለ ውግዘትግምጃ ቤት
 


ጋድ (ገሃድ) እና ጥምቀቱ ለእግዚእነ፡፡
ጥር ፲፩ ቀን ፳፻፯ ዓ∙ ም∙

«ጾመ ገሃድ (ጋድ)፦ የቃሉ ትርጕም «ገሃድ» ሲል መገለጥ፥ «ጋድ» ሲል ለውጥ ማለት ነው። ቅዱሳን ሐዋርያት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ የልደቱና የጥምቀቱ በዓል በሳምንት ሁለት ቀን በምንጾምባቸው ጾም በተሠራባቸው በረቡዕና በዓርብ የዋለ እንደ ሆነ የጾሙ ሥርዓት ሳይጠበቅ፤ ፩ኛ፤ ታኅሣሥ ፳፰ ቀን ለ፳፱ አጥቢያ፤ ፪ኛ፤ ጥር ፲ ቀን ለ፲፩ አጥቢያ በመንፈቀ ሌሊት ቅዳሴ እንዲፈጸምና ምእመናን በትንሣኤው የአከባበር ሥርዐት ዐይነት በዓሉን በደስታ እንዲያከብሩ አዝዘዋል። ስለዚህ ሁለቱም ማለት የልደት፥ የጥምቀት ዋዜማ በጾም እንዲታሰብ ሆኗል።

በአንድ በኩል የጌታን መገለጥ የምናስብበት ነው። መገለጥ ሲባልም እንደ በዓላቱ ጠባይ ሁለት ነው። በልደት መገለጥ ሲባል ሰው ሆኖ የማያውቅ አምላክ በሥጋ ሰው ሆኖ በአጭር ቁመት፥ በጠባብ ደረት ተወስኖ ስለ ተገለጠና ሰዎች ሊያዩት ሊዳስሱት ስለ ቻሉበት ነው።

በጥምቀት መገለጥ መባሉ፤ ሰው የሆነው አምላክ በዓለም ሲኖር እስከ ፴ ዓመት ዕድሜው ድረስ ሰዎችን ለማዳን የመጣ መሲሕ፥ ሰው የሆነው አምላክ አማኑኤል ኢየሱስ ክርስቶስ እሱ መሆኑን ሳያውቁ ከኖሩ በኋላ በ፴ ዓመት ዕድሜው በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ ሲጠመቅ፤ አብ፤ «የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እሱን ስሙት፤» ብሎ በሰጠው ምስክርነት መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ሲያርፍ በመታየቱ ነቢያት የተነበዩለት የሰው ልጆች መድኃኒት ሥግው አምላክ ማለት ሰው የሆነ አምላክ እሱ መሆኑ ስለ ተገለጠበት ነው።

ጾመ ገሃድ ወይም ጋድ ቅዳሜ፥ እሑድ ቢሆን በሰንበት ጾም ስለ ሌለ ሥርዓተ ጾሙ ከጥሉላት ምግብ በመከልከል ብቻ ይፈጸማል።»

(የጽድቅ በር፤ ፲፱፻፸፱ ዓ ም፤ ገጽ፤ ፳፯ - ፳፱።)

የጥምቀት በዓል

ይህ በዓል በፊት የጥፋት ውሃ ከምድር ላይ በጥር ወር ጨርሶ ስለ ጎደለ ኖኅ በዓል አድርጎበታል፡፡ ኋላም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ሲጠመቅ በጥምቀቱ ጥምቀታችንን ቀድሶበታል፡፡ የባሕርይ አምላክነቱን፣ የባሕርይ ልጅነቱን ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ አስመስክሮበታል፡፡ ስለዚህም ስሙ ኤጲፋንያ (አስተርእዮ) መገለጥ ይባላል፡፡ ኢትዮጵያ ይህንን በዓል በሕገ ልቡና ከአበው፣ በሕገ ኦሪት ከነቢያት፣ በሕገ ወንጌል ከሐዋርያት ጋራ በመተባበር ታከብረዋለች፡፡ በየዓመቱም ጥር ፲፩ ቀን ወደ ወንዝ እየወረደች፤ የእግዚአብሔር ቃል በውሆች ላይ ተገለጠ፤ የምስጋና አምላክ ድምጡን ሰጠ፤ እግዚአብሔር በውሆች ላይ ታየ ባለው ቃል መሠረት መታሰቢያውን ታከብራለች፡፡ መሠረቱም ጌታ እግዚአብሔር ተገልጦልናልና በደስታ በዓል አድርጉ የሚለው ቃለ ትንቢት ነው፡፡ መዝ፤ ፳፱ ቁ፤ ፫፡፡ ፻፲፰ ቁ፤ ፳፯፡፡ ማቴ፤ ም፤ ፫፡ ፲፫ - ፲፯፡፡

(የኢትዮጵያ እምነት በሦስቱ ሕግጋት፤ ገጽ ፪፻፴፮፡፡)

«በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ። ልዩ ሦስት አንድ አምላክ በሚሆን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እንባርካለን፤ መልእክታችንንም እንጀምራለን። «ይቤ እግዚአብሔር ወፂእየ እገብእ ወእትመየጥ እንተ ቀላየ ባሕር።»

የጥምቀት በዓል ከአባቶቻችን ዘመን ጀምሮ በኢትዮጵያ በታላቅ ሥነ ሥርዐት ከሚከበሩት በዓላት አንዱ ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ ሕዝበ ክርስቲያን በየትኛውም ሥፍራ ብትሆኑ እንኳን ለዚህ በዓል አደረሳችሁ እላለሁ። በነቢያትም በልዩ ልዩ ሥፍራ በትንቢት እንደ ተጠቀሰው ነቢዩ ዳዊት፤ «ይቤ እግዚአብሔር ወፂእየ እገብእ ወእትመየጥ እንተ ቀላየ ባሕር።» «እስራኤልን ይዤ ከወንዝ ከወጣሁ በኋላ እንደገና ወደ ጥልቁ ባሕር እመለሳለሁ ብሏል እግዚአብሔር፤» ይላል። ጌታ እስራኤልን በሙሴ መሪነት ቀይ ባሕርን ከፍሎ ካስገባቸው በኋላ በኢያሱ መሪነት ደግሞ ዮርዳኖስን ከፍሎ አሻግሯቸዋል። ቀደም ሲል ከሦስት ቀን በፊት ኢያሱን ቀስቅሶ ሕዝቡ ከሦስት ቀን በኋላ ዮርዳኖስን ስለሚሻገር ተዘጋጅ የሚል ትእዛዝ ሰጠው። በሦስተኛው ቀን ታቦተ ጽዮንን የተሸከሙ ካህናት ቀድመው ሕዝቡ ተከትሎ ሺ ሜትር ያህል ርቆ እያጀበ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ገቡ። የካህናት እግር ውሃውን ሲረግጥ ውሃው ከመውረድ ተገታ። ጊዜው በሀገሩ ሥነ ሥርዐት ክረምት ስለ ነበረ ውሃው ተርፎ ይፈሳል ነገር ግን የካህናት እግር ሲረግጠው ውሃው ተቋረጠ። ወደ ታች ያለው ጨው ባሕር ገብቶ አለቀ። ወደ ላይ ያለው ግን ተቆልሎ ይታይ ነበር ይባላል። ይህን በመሰለ ኀይል ነው ዮርዳኖስን ያሻገራቸው።

ይህ ተአምራት ከሆነ ከሺ ፭፻ ዓመት በኋላ ጌታ ሰው ሆኖ ሥጋ ለብሶ ወደ ዓለም መጣ። በ፴ ዘመኑ በእደ ዮርዳኖስ በዮርዳኖስ ወንዝ በዚሁ እስራኤል በተሻገሩበት ወንዝ ላይ ተጠምቆ ከአባቱ ፥ ከመንፈስ ቅዱስ የባሕርይ ልጅነቱን፥ አምላክነቱን አስመስክሮ ይህን በዓል መሥርቶታል። በወንጌል እንደ ተጻፈው፤ ተጠምቆ ከውሃው ወጥቶ ሲጸልይ ሰማይ ተከፈተ። የሚያስደንቅ ቃል ነው። እስከዚህ ዘመን ድረስ ወይም ከዚያ ዘመን በኋላ ሰማይ ተከፈተ የሚል ቃል ተጽፎ አናገኝም። ሰማይ ተከፈተ፤ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ዐረፈ። «የምወደው ልጄ ይህ ነው፤» የሚል የእግዚአብሔር አብ የምስክርነት ቃልና ዐዋጅ፤ «እሱን ስሙት፤» ከሚል መልእክት ጋር ተላለፈ። ከዚያ ጊዜ ከምሮ ሰውና እግዚአብሔር ፊት ለፊት የተያዩበት ነው።

ስለዚህም ይህን በዓል የምናከብረው። የበዓሉ አከባበርም ከሌሎች በዓላት ሥርዐት ለየት ያለ መልክ አለው። ይህ በዓል ኢትዮጵያ ሁለት ጊዜ ያከበረችው ነው። አንደኛ በብሉይ ኪዳን በበዓለ መፀለት ሥርዐት ከቤት ወጥቶ፥ ወንዝ ወርዶ፥ ወይንም ድንኳን ተክሎ በማኅበር የመከሩን መጨረሻ ዘመን ማክበር የተለመደ ሥርዐት ነበር። አሁን ግን ያ በጥምቀት በዓል ተለወጠ። ጌታ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ወረደና ዮሐንስ ወዳለበት ሄደ። ከዚያም በዮሐንስ ተጠመቀ። በዮሐንስ እጅ ይጠመቁ የነበሩ ሰዎችም እዚያው ስለ ነበሩ ይህ በዓል በየዓመቱ መታሰቢያቸውን በነበረበት መልኩ ለማቆየት ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ ቤተ ክርስቲያን ከወንዝ ወርዳ፥ ድንኳን ጥላ ታከብረዋለች። በዚህም ትንቢት ሁሉ መፈጸሙን ታረጋግጣለች። ቀደም ብዬ እንደ ተናገርኩት የትንቢቱ መሠረት እስራኤል ወንዝ ከፍለው መሻገራቸው ሲሆን ፍጻሜውም የጌታ ጥምቀት መሆኑ ነው። እስራኤል ዮርዳኖስ ተከፍሎላቸው ወደ ምድረ ርስት እንደ ገቡ ጌታም ጥምቀትን ባርኮ ወደ መንግሥተ ሰማያት ለሚሸጋገሩ ምእመናን ሁሉ በር መክፈቱ ነው።

እርግጥ ሠሪና ተቀባይ ሥርዐታቸው እኩል አይደለም። ጌታ ሠሪ ስለ ሆነ ሁሉን ነገር ከ፴ ዘመን በኋላ ነው ያከናወነው። ከግዝረትና ወደ ቤተ እግዚአብሔር ከመግባት በስተቀር የቀረው ሁሉ ከ፴ ዘመን በኋላ በሥነ ሥርዐት የተፈጸመ ነው። የተጠመቀውም በ፴ ዘመኑ ነው። ለእኛ ግን በ፵ ቀን፥ በ፹ ቀን ነው ጥምቀት የተሰጠን። ይህም በኦሪት ዘሌዋውያን ምዕራፍ ፲፪ ስለ ወላዲቱ በተጻፈው ተደንግጓል። እግዚአብሔር የሰጠው ትእዛዝ ነው። መጀመሪያ ለሙሴ የሰጠውን ትእዛዝ ሰው ሆኖ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወልዶ በሥጋ በተገለጠ ጊዜ በ፵ ቀኑ ወደ ቤተ እግዚአብሔር በመግባት አጽንቶታል። በ፵ ቀን፥ በ፹ ቀን ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ፥ ከማሕፀነ ዮርዳኖስ ወይንም ከውሃና ከመንፈስ ቅዱስ ለሚወለዱ ሁሉ መሠረት አድርጎታል። ይህንንም በ፴ ዘመኑ አጽንቶታል። ምክንያቱም እሱ የሚጠመቅ ለአባትነት ነው፤ ወላጅ ነው። እኛ ግን የምንጠመቀው ለልጅነት ነው። ስለዚህም እኛ በ፵ ቀን፥ በ፹ ቀን እንጠመቃለን። ከዚህ ያለፈ ቢመጣም አልተከለከለም። የጥምቀት ሥርዐት በወንጌል የተቀመጠው በሁለት መልኩ ነው። አንዱ፤ «ሂዱና እስከ ምድር ዳርቻ አስተምሩ፤ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም አጥምቋቸው፤ ያዘዝኳችሁንም ሁሉ አስተምሯቸው፤» የሚል ነው። ይህ በልጅነታቸው ለሚጠመቁ የተሰጠ ነው። ሌላው፤ «ሂዱ፤ ለፍጥረት ሁሉ ወንጌልን ስበኩ፤ ያመነ የተጠመቀ ይድናል፤ ያላመነ ያልተጠመቀ ይፈረድበታል፤» የሚለው ነው። ይህ ደግሞ ፵ ቀን፥ ፹ ቀን ካለፈ በኋላ ቢመጣም ጥምቀት የማይከለከል መሆኑን ነው የሚያሳየን። ሥርዐቱ በሁለት መልክ የሚከናወነው ለዚህ ነው። ለሁሉም ግን መሠረቱ ጌታ ዮርዳኖስ ወርዶ በመጠመቅ ከአብ፥ ከመንፈስ ቅዱስ የባሕርይ ልጅነቱን አስመስክሮ፤ «እሱን ስሙት፤» የሚለውን ዐዋጅ አሳውጆ ስለ መሠረተው ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ጥር ፲፩ ቀን የዚህ በዓል መታሰቢያ ሆኖ እስከ ዛሬ ደርሰንበታል። ለዚህ ነው በተለይም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የምታከብረው ይህን መንፈሳዊ ሕግ መሠረት በማድረግ ነው።

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከመሠረቱ ጀምሮ የሃይማኖትን ትምህርት እድገት እየተከታተለች የኖረችና መጀመሪያ በሕገ ልቡና የኖኅ ልጆች ምድርን ዕጣ በዕጣ ብለው ተከፋፍለው በየአገራቱ ሲሰማሩ የእኛም አባት ካም ልጆቹን ኩሽን፥ ሚዝራይምን፥ ኦፌርንና ኦጋድን ይዞ ወደ ኢትዮጵያ በመጣ ጊዜ ለኖኅ እግዚአብሔር የሰጠውን የዕርቅ ምልክት ቀስተ ደመናውን ምልክት አድርጎ ነው የገቡት። የሰንደቅ ዓላማችን ቀለም ያን ጊዜ የተገለጠና የዕርቅ ምልክት የሆነ ነው። በዚህ ጊዜ ከሳምንት በዓላት ሰንበትን፥ ቀዳምን፥ ከዓመት በዓላት የዘመን መለወጫን ይዘው ነው የገቡት። ኋላ በብሉይ ኪዳን ደግሞ የቅዳሜ ሰንበትነት ሳይለወጥ በዚያ ላይ በዓለ መፀለትን፥ በዓለ ፋሲካን ጨምረው ተቀብለዋል። ይሁን እንጂ በዓለ ጥምቀትን ኢትዮጵያውያን በነበረው ሥርዐት ከማክበር በስተቀር አልለወጡትም። የዘመን መለወጫም መስከረም ነው፤ አልተለወጠም። ለምሳሌ የእስራኤል የዘመን መለወጫ ሚያዝያ ነው። እኛ ግን ከአበው ከሔኖክና ከኒኅ በተቀበልነው መሠረት እያከበርን ነው፤ አልለወጥንም። ዓመተ ምሕረትንም እንዲሁ ኢትዮጵያውያን የተቀበሉት ከፅንሱ ጀምሮ ነው። ጌታ በመጋቢት ተፀንሶ በታኅሣሥ ተወለደ። በመሓል መስከረም ነበር፤ የዘመን መለወጫ። ከዓመተ ብሊት ወደ ዓመተ ምሕረት የተሸጋገርነው በፅንስ ነው። የሰው ልጆችም ተስፋ በዚህ መሠረት ነው የሚሄደው። ቅዱስ ገብርኤል፤ «ወንድ ልጅ ትወልጃለሽ፤ ስሙን ኢየሱስ ትዪዋለሽ፤ እግዚአብሔር አምላክ የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል፤ በያዕቆብ ወገንም ለዘለዓለም ነግሦ ይኖራል ፤ ለመንግሥቱም ፍጻሜ የለውም፤» ካለበት ጊዜ ጀምሮ ሥጋ የባሕርይ አምላክ ሆኖአል፤ አምላክም ሰው ሆኖአል። እሷ፤ «እኔ የእግዚአብሔር ባርያው ገረዱ ነኝ፤ እንደ ቃልህ ይሁንልኝ፤» ብላ ስለ ተቀበለችው ዋሕድ ቃለ እግዚአብሔር በማሕፀንዋ በመጠነ ሕፃናት ተቀረጸ። ዓመተ ምሕረትም ተጀመረ። ይህ ነው መሠረቱ። አውሮፓውያን እኛ ከሰማን በኋላ ፯ ዓመት ቆይተው ነው የሰሙት እያሉ ዛሬም ይቀልዳሉ። ነገር ግን የሚቀልዱት በራሳቸው ነው። የነሱን ዓመተ ምሕረትም የወሰኑት ዓመተ ምሕረት ካለፈ ከሺ ዓመት በኋላ በአንድ ጳጳስ አማካይነት ነው። ከዚህ ውጪ ከመጀመሪያ የቈጠሩት ቊጥር የላቸውም፤ ሲያዘባርቁት ነው የኖሩት። ይልቁን ሊጠይቁን ከፈለጉ ኢትዮጵያውያንን መጠየቅ ነበረባቸው። ምክንያቱም ለራሳቸው ለአይሁድ እንኳ፤ «ኮከብን በምሥራቅ አይተን ልንሰግድለት መጥተናልና የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ የት ነው?» ብለው በመጠየቅ የአይሁድ ንጉሥ መወለዱን ለእስራኤላውያን ያበሰሯቸው ኢትዮጵያውያን ናቸው። ወርቅ፥ ዕጣን፥ ከርቤ ያቀረቡ፥ በትንቢትም የተጠሩ ኢትዮጵያውያን ናቸው። ኋላም ሥርዐቱ የተፈጸመላቸው በኢትዮጵያውያን ስለ ሆነ ሳያፍሩ እኛን ሊጠይቁ ይገባ ነበር። መማር አያሳፍርም። መቼም ከማቃለል መጠየቅ የሚያሳፍር አይመስለኝም። ስለዚህ በዓለ ልደቱም ሆነ የዓመተ ምሕረት አቆጣጠሩ፥ የበዓል አከባበሩም ጭምር የኢትዮጵያን ሕይወት መሠረቱን ጠብቆ የመጣ እንጂ አንድም የተዛነፈና የተሳሳተ የለበትም።

የተሳሳተ ነገር አለ ከተባለ በዚህ ፴ ዓመት ውስጥ የሆነው ብቻ ነው። አዎን፤ ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት ተለያይተዋል የሚል ሕገ መንግሥት ከተረቀቀበት ጊዜ አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ የተለወጠው ሥጋዊ አስተዳደር ብቻ ሳይሆን መንፈሳዊያኑ ሥርዐታቸውን መጠበቅ አልቻሉም። ደርግ፤ «እግዚአብሔር የለም፤» ብሎ ሲነሣ ቤተ ክርስቲያንም፤ «ወንጌልና ሶሻሊዝም አንድ ነው፤» ብላ ዐብራ መጮህና መደናቆር ጀመረች። «ሃይማኖት አይለያየንም፤» ብላ ሁሉንም ያቀላቀለ ማኅበር መመሥረት ጀመረች። የእናት አገር ጥሪ ብላ በዐቢይ ጦም እያሳረደች አበላች። ይህን ያደረገችው ቤተ ክርስቲያን በጥፋተኛ መሪዎቿ ግዴለሽነት ነው። ይባስ ተብሎ ጨርሶ ስሟም ጠፍቶ፥ ክብሯም ተራቁቶ የካቶሊክ ጥገኛ ከመሆን ደርሳለች። በዚህ ምክንያት፤ «የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት፥ ሥርዐተ አምልኮትና የውጭ ግንኙነት፤» በሚባለው መጽሐፋቸው ተምህርተ ሃይማኖቱን ከመለወጣቸውም በላይ፤ «ከእሑድ በቀር ኤጲስ ቆጶስ ሊሾም አይገባውም፤» የሚለውን ሕገ ቤተ ክርስቲያን ሻሩ። ይህ ጌታ ራሱ በትንሣኤው ቀን የመሠረተውን ንደው በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሥርዐት ሰኞ ቀን ፲፮ ኤጲስ ቆጶሳትን ሾመዋል። ይህ ራሱ ለዘመናት ያልተደፈረችውን ቤተ ክርስቲያን፥ ለዘመናት በጒልበት ያልተደፈረውን ነጻነታችንን አሳልፈው የሰጡ የዛሬዎቹ የቤተ ክርስቲያን ጳጳሳት ናቸው። ይህም ሳይሰማቸው ቀርቶ ጳጳሳትና ካህናት ዐምፀው እስከ ዛሬ ድረስ ሕዝቡን አፍነው እንደ ያዙት ናቸው።

በአሁኑ ጊዜ የምንመለከተው ሁሉ እንደ ፖለቲካው ባሕሪ ሃይማኖቱም በዚያው መልኩ እየተመራ መሆኑን ያስረዳናል። ከዚያም ብሶ የቴአትር መልክ ይዞ ይታያል። የሩቁን ንቀን እንተወው ብንል እንኳ ባለፈው ስለ ዘመን መለወጫና ስለ ልደት በዓል የሆነውን ብንመለከት የሦስት ሃይማኖት ባለቤቶች ቀርበው የኢትዮጵያን ሕዝብ እንኳን አደረሰህ ይሉ ነበር። ይህን የሚሉት የማን ነው ብለው ነው? መቼም የኢትዮጵያ አይደሉም፤ ይህ የታወቀ ነው። ካቶሊክ የሮም፥ ፕሮቴስታንት የአውሮፓ ነው ወይም የጀርመን፥ የእንግሊዝና የስዊድን። የዛሬዎቹ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መሪዎችም የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን እንደራሴዎች ናቸው። ታዲያ የማን ነን ብለው ነው የኢትዮጵያን ሕዝብ እንኳን አደረሰህ የሚሉት? በየትኛውስ ሥርዐት? እነሱ የዘመን መለወጫ ያደረጉት በታኅሣሥ ነው። የእኛ የዘመን መለወጫ ደግሞ መስከረም ነው። እነሱ የልደትን በዓል ያከበሩት ታኅሣሥ ፲፭ ቀን ነው። እኛ በዓሉን ያከበርነው ታኅሣሥ ፳፰ ቀን ነው። በምን ተገናኝተን እንኳን አደረሳችሁ ይሉናል? ጉዳዩ እንዲህ ሆኖ ሳለ በመድረክ ላይ ወጥተው የሚቀልዱት በእግዚአብሔር ወይንስ በሰው ነው? እውነት ሃይማኖት አለን ካሉ፥ እንበልጣለን እናስረዳለን ካሉ መድረክ ይከፈትና እንነጋገርበት። ቅር የሚያሰኝ ነገር የለም።

የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እኮ ይህን መንፈሳዊ ትምህርት የተማረችው ከሰው አይደለም፤ ከመንፈስ ቅዱስ ነው። ሐዋርያው ፊሊጶስ ሲያስተምር ከነበረበት ቦታ፤ «ሂድ ይህን ሠረገላ ተከተለው፤» ሲል ያዘዘው መንፈስ ቅዱስ ነው። ወንጌላዊ ሉቃስ በግብረ ሐዋርያት ላይ ጽፎታል። በምዕራፍ ፰ ከቊጥር ፳፮ እስከ ፴፱ ያለውን መመልከት ይቻላል። የኢትዮጵያ ንግሥት ጃንደረባ የነቢዩን የኢሳይያስን ትንቢት ያነብ ነበር፤ «እንደ በግ ሊታረድ መጣ፤» የሚለውን። ሐዋርያው ሲሰማው ተደነቀ። ሐዋርያው ይህን ትምህርት ያገኘው ከተቀበለው ከጰራቅሊጦስ መንፈስ ቅዱስ ነው እንጂ ቀድሞ አያውቀውም፤ አልተማረውም። ጃንደረባው ግን ከመሠረቱ ጀምሮ የኢሳይያስን ትንቢት በትምህርት ያውቀው ነበረ፤ በተስፋም ይጠብቀው ነበረ። ኢየሩሳሌም በዓለ ፋሲካን አክብሮና ተሳልሞ ሲመለስ መንፈስ ቅዱስ ፊልጶስን፤ «ይህን ሠረገላ ተከተለው፤» አለው። ጃንደረባው ወደ ጋዛ የሚያወርደውን መንገድ ይዞ ይወርድ ነበር። ተከተለው። ትንቢቱን ሲያነብ ሰማው። «የምታነበውን ታውቀዋለህ ወይ?» አለው ሐዋርያው። ጃንደረባው፤ «ያስተማረኝ የለም፤ በምን ዐውቀዋለሁ፤ ካወቅህ ሠረገላው ላይ ውጣና አስረዳኝ፤» አለው። ከሠረገላው ወጣ። ሐዋርያው የመንፈስ ቅዱስ ምሩቅ ነበረ። የባለ ፸፪ ቋንቋ ባለቤትም ነበረ። እሱም ግእዝ አልተማረም። ነገር ግን በግእዝ ቋንቋ ሲያነብ ለነበረው ሰው ያስተማረው በግእዝ ቋንቋ ነው። በዚያው መጽሐፍ ስለ ጌታ ጠቅላላ ትምህርት ሰጠው። አምላክ ሰው ስለ መሆኑና ስለ ልደቱ፥ ስለ ጥምቀቱ፥ ስለ ስቅለቱና ከዚያም ለቤተ ክርስቲያን ስለ ሰጠው ትምህርት ሁሉ አጠቃሎ እያስተማረው ሳለ ውሃ ካለበት ደረሱ። አስቀድሞ ስለ ጥምቀት ተነጋግረው ነበረና፤ «ታዲያ ውሃ ይኸውና፤ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ማነው?» አለ ጃንደረባው። ሐዋርያውም እዚህ ላይ ተጠነቀቀ። «ግዴለም ትችላለህ፤» አይደለም ያለው። «በፍጹም ልብህ ልታምን ይገባሃል፤» ነው ያለው። ልብ እንበል። «ልታምን ይገባሃል፤» ብቻ አይደለም ያለው። «በፍጹም ልብህ ልታምን ይገባሃል፤» ሲል ነው የገለጠለት። የመንፈስ ቅዱስ ተጠሪ የሆነው ጃንደረባው፤ «እኔ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ፤» አለ። ይህን ከተናገረ በኋላ አጥማቂውና ተጠማቂው ወደ ወንዝ ወረዱ፤ አጠመቀው። ተጠማቂው ጥምቀቱን ተቀብሎ፥ መልእክቱን ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ገባ። አጥማቂውም በመንፈስ ቅዱስ ትእዛዝ ወደ ሌላ ቦታ ሄደ። በዚህ መሠረት ነው ኢትዮጵያም ሃይማኖትን የተቀበለችው። ያ ሰው ሲናገር፤ «የእግዚአብሔር ልጅና ሰው የሆነው፤» አላለም። «ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ፤» ነው ያለው እንጂ። «ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ እና ሰው እንደ ሆነ ዐውቃለሁ፤» የሚል ሁለት ባሕርይ አድርጎ አልገለጠም። አንድ አካል አንድ ባሕርይ መሆኑን አረጋግጦ፤ «እኔ ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ፤» ነው ያለ። ይህ ሰውና ጴጥሮስ ጋር በእምነት እኩል ናቸው። ይህም ስለ ሆነ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ከሮም ቤተ ክርስቲያን ጋር የሚቀላቅላት ምንም ነገር የለም። ዛሬ የሮም ቤተ ክርስቲያን የኢትዮጵያን ክርስቲያኖች እንኳን አደረሳችሁ ልትም መብቱም የላትም። ሁለተኛ፤ «እኔ ኢየሱስ አማላጅ መሆኑን አምናለሁ፤» አይደለም ያለው። «ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን አምናለሁ፤» ነው ያለ። «ኢየሱስ አማላጅ ነው፤» የምትል መካነ ኢየሱስ የኢትዮጵያን ሕዝበ ክርስቲያን፤ «እንኳን ለልደቱ አደረሳችሁ፤» ማለት መብቷም አይደለም። የዛሬዎቹም የካቶሊክ ጥገኞች እዚያው በበሉት ፍርፋሪ ሄደው መጮህ አለባቸው እንጂ እዚህ መጮህ የለባቸውም።

የኢትዮጵያ ሕዝበ ክርስቲያን! ጳጳሳትና ካህናት ዐምፀው ኢትዮጵያን ከሃይማኖቷና ከሃይማኖት ጸጋ አራቁተዋታል። እያየን ነው። በዚህ ፴ ዘመን የሚነደው እሳት፥ የሚወርደው መቅሠፍት ከሰው አእምሮ በላይ መሆኑን እያየን ነው። ረኀቡ፥ ቸነፈሩ፥ ልዩ ልዩ መቅሠፍት፥ በሽታዎች፥ አረሙ ሳይቀር ጥንዚዛ እየበቀለበት ነው። ጥንዚዛ ደረቅ ዕንጨት የሚበላ እንጂ ከመሬት ፈልቆ አዝመራ የሚያጠፋ ሆኖ እንኳን እኛ፥ አባቶቻችን አላዩም። ዛሬ ግን የሚሆነው ሁሉ እየሆነ ነው። ታዲያ አንድም የተገሠፀና የተመለሰ የለም። እንደ ትናንትናው ሁሉ ዛሬም ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት ተለያይተው ነው ያሉት። መንግሥት በሃይማኖት ጣልቃ አልገባም ብሏል። የሚሆነውን ሁሉ በዝምታ እየተመለከተ ነው። ነገር ግን ከእግዚአብሔር በትር አላመለጠም። ራሱም መንግሥት እየተገረፈ ነው። ሕዝቡም ከቅጣት አላመለጠም፤ እየተገረፈ ይገኛል።

አሁንም ይህን በዓል በማክበር ላይ ያለ ምእመን ሁሉ ስለ ሃይማኖቱ በጥሞና ሊያስብበት ይገባል። የሩቁን ይተወው። ብዙ በደል በሃይማኖት መሪዎች ተፈጽሟል። ምናልባት ስለ እኔ ሲነገር፤ «ይህን የሚለው ጥቅሙ ስለ ተነካ ነው፤» እያሉ ሕዝቡን የሚያደናግሩ ብዙዎች አሉ። እኔ ምንም የተነካብኝ ጥቅም የለም። ደግሞስ ጥቅም ብፈልግ ኖሮ አሁን እንዳሉት ሰዎች ምላሴም አሳርፌ መብላት ያቅተኝ ነበርን? አያቅተኝም ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር የሰጠኝን ዐደራ አልለውጥም ብዬ ነው የማስተምረው።

እንደ ተናገርኩት የሩቁን ብንተወው፤ ታኅሣሥ ፲፪ ቀን ፲፱፻፺፮ ዓመተ ምሕረት ካርዲናል ጳውሎስ በሞቱ ጊዜ የእኛ ጳውሎስ መቃብሩ ላይ ባራኪ ነበሩ። ይህ ልክ ነው ወይ? በእኛ ሥርዐት አለ ወይ? ይህንን ዐይናችሁ አላየም ወይ? ማን ነው በማን ቤት ገብቶ ባራኪ የሚሆን? እነሱም አይቀበሉት እኛም አናደርገውም ነበር። ከእኛ የተሻለ ባለ ቡራኬ አለ ብለው በእነሱ ቤተ መቅደስ ላይ ቡራኬ የሚፈቅዱበት አንድም የእኛ ሰው የለም። አባ ጳውሎስ ግን አባላቸው ስለ ሆኑ ነው የፈቀዱላቸው። ታዲያ ይህን እያያችሁ ምእመናን ዝምታን መምረጣችሁ በጣም አስደንጋጭ ነው። አሳዛኝም ነው። አሳፋሪም ነው። እንዴ! እናንተ ሞኞች መሰላችሁኝ በቃ። እስከ አሁን ጌታ የቀጣው ቅጣት አልሰማችሁ ብሎ ከሆነ እንጃ። እኔ ከዚህ በፊትም ሰማይም ምድርን ምስክር አድርጌ ያስተላለፍኩትን ቃል አስታውሳለሁ። አሁንም ደግሞ እንቢ ካላችሁ እግዚአብሔር ለዚህም ደግሞ ሀብታም ነው። የሚያመጣው አያጣም። ኋላ እንዳይቆጫችሁ አሁኑኑ ንስሐ ብትገቡ ይሻላል። በዓል እናከብራለን ካላችሁ ቶሎ ንስሐ ግቡ። ያለዚያ መለየት ነው ያለባችሁ። ዝም ብላችሁ በእግዚአብሔር ማሾፍ የሚያዋጣ አይመስለኝም። በዚህ ዐሥር ዓመት ጥምቀቱ በሥነ ሥርዐቱ አልተከበረም፤ ታውቃላችሁ። በየዓመቱ የውጭ ዕንግዳ እየመጣ እየተደባለቀ የበዓሉ መልክ እየተቀየጠ ከሚታይ በስተቀር በሥነ ሥርዐቱ፥ በነበረ ጠባዩና ባሕሪው አልተከበረም። ካለፉት ፲፪ ዓመታት ወዲህ ይህ በዓል አልተከበረም ማለት ይቻላል። በነዚህ ዓመታት ውስጥ በዓለ ጥምቀቱ አለመከበሩን እያወቃችሁ እስካሁንም ለመመለስ አልቻላችሁም። ተዉ የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ተመለሱ። ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ።

እግዚአብሔር በረከተ ጥምቀቱን ለአገራችን ለሕዝባችንም ይፍቀድልን። አሜን።»

(ኢትኦጵ ጋዜጣ ጥር ፲፪ ቀን ፲፱፻፺፮ ዓ∙ ም∙)

 

ተጨማሪ ገጾች።
 ዜናዎች
 አስተያየቶትን ይጻፉልን
 የ aleqayalewtamiru.org አባል ይሁኑ
ይህንን ገጽ ለወዳጆችዎ ያሳውቁ።
የኒውስሌተራችን ተጠቃሚ ይሁኑ
በየጊዜው የሚደረጉ ለውጦችን ለማወቅ ይመዝገቡ።
ሙሉ ሥም
የኢሜይል አድራሻ
መውረድ የሚችሉ ፋይሎች
የክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ የመንፈቅ መታሰቢያ። (.zip, 28.3 MB)
የክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ የመንፈቅ መታሰቢያ። (light weight) (.zip, 2.4 MB)
Unable to read the text?
Download Font (nyala.ttf, 427KB)
For PC users: download and save the font file in "C:\Windows\Fonts" folder and restart your browser
(Nyala.ttf, © 2006 Microsoft Corporation. All Rights Reserved. Nyala is either a registered trademark or a trademark of Microsoft Corporation in the United States and/or other countries.)
መግቢያየሕይወት ታሪክመጻሕፍትየድምፅ ማኅደርቃለ ውግዘትግምጃ ቤት
Copyright  , aleqayalewtamiru.org