መሠረተ ቃል፤ ‹‹ኵለንታኪ ሠናይት አንተ ኀቤየ፤ አልብኪ ነውር ወኢምንትኒ ላዕሌኪ። ንዒ እምሊባኖስ መርዓት ንዒ አምሊባኖስ።» «የእኔ ሆይ ሁለንተናሽ ያማረ ነው፤ በአንቺ ላይም ምንም ምን ነውር የለብሽም። ከሊባኖስ ነዪ፤ እቴ ሙሽራ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ።›› (መኃ. ፬፥ ፯።)
እስከ አሁን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዚህ ዓለም በሕይወተ ሥጋ ሳለች የተፈጸሙትን ሁኔታዎች አሳይተናል። ከዚህ ጀምሮ ግን የምንመለከታቸው ከሞት በኋላ ያሉትን ነው፡፡
እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እግዚአብሔር ቃል ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስዋ ነፍስ ነሥቶ ከእርስዋ ሰው ሆኖ ከተፀነሰበት፥ ከተወለደበት ጊዜ ጀምሮ እስካረገበት፥ ቀጥሎም እርስዋ ከዚህ ዓለም በሞት እስከ ተለየችበት ጊዜ ድረስ ብዙ ደስታ ተደርጎላታል፤ ብዙም መከራና ኀዘን ደርሶባታል። ከመፀነሱ አስቀድሞ፥ በማሕፀንዋ ሳለ ጀምሮ የመላእክትን ብሥራት፥ የመላእክትን ምስጋና በመስማት፤ ኋላም በልደቱ ኖሎት፥ መላእክት ሲያመሰግኑት፥ ሰብአ ሰገል ሲገብሩለት በማየት በእርስዋ ላይ የተፈጸመውን ዕፁብ ድንቅ የማይመረመር ምሥጢር የሆነውን በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና መወለዱን በመገንዘብ ጥቂት በጥቂት ባደገበትና ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ወንጌልን ባስተማረበት ዘመን ሁሉም ባደረገው ተአምራት፥ በሠራው ምግባር ትሩፋት፤ በሰማቸው፥ ባየችው፥ በተገነዘበችው ግሩም ድንቅ በሆነ ኀይሉ፥ ጠባዩ፥ ግብሩ፥ ፈቃዱ፥ መልኩ፥ ደም ግባቱ፥ በኋላም በትንሣኤው፥ በዕርገቱ እጅግ ደስ ያላት ብትሆንም፤ ሄሮድስ ሊገድለው ሲያድነው በነበረበት ጊዜ፥ ካህኑ ስምዖን አይሁድ እንደሚገድሉት ትንቢት በተናገረበት ጊዜ፥ ለበዓልም ወጥቶ ሳይመለስ በመቅረቱ በደረሰባት ድንጋፄ፥ አይሁድ ሁል ጊዜ ለጠላትነት ሲዘጋጁበት በመመልከቱዋ፥ ኋላም ሕማሙን፥ ስቅለቱን በማየቷ የደረሰባት መከራና ኀዘን እጅግ በጣም ከባድና አሳዛኝ ነው፡፡ ከዚህም በቀር ጌታ ካረገ በኋላ ዐሥራ አምስት ዓመት ይኸው የዕለተ ስቅለቱ ኀዘን ከልብዋ ሳይወጣላት ስታዝን፥ ስትተክዝ ኖራለች፡፡ ምናልባት ይህ ኀዘን ተስፋ ከመቊረጥ የመጣ ሊመስለን አይገባም። ከእናትነቷ የመጣ እንጂ፡፡ ማንኛውም ወላድ ክፉ በጎ ሳይባል ለልጇ እንዲሁ ናትና፡፡ ከዚህ በላይ በገለጥነው ሁኔታ ፷፫ ዓመት ያህል ከኖረች በኋላ በ፷፬ኛ ዓመቷ ጥር ፳፩ ቀን ዐርፋለች፡፡
ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ጥር ፳፩ ቀን የዕረፍትዋን መታሰቢያ በዓል ታከብራለች፡፡ በዚህ ቀን ከላይ በመኃልይ እንደ ጠቀስነው ቃል ሁሉ ሐዋርያት ተሰብስበው በተገኙበት ልጅዋ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዕረፍቷ ጊዜ ወዳለችበት መጥቶ ነፍስዋን ከሥጋዋ ለይቶ ወደ ሰማይ ሲያሳርጋት፥ ሥጋዋን ደግሞ ሐዋርያት በጌቴሴማኒ መቃብር አሳርፈውታል። በዚህም፤ ‹‹እቴ ሙሽራ ከሊባኖስ ከእኔ ጋር ነዪ፤›› የሚለው ቃል ተፈጽሞላታል። ጌታችን በሞቱ ጊዜ ነፍሱን ከሥጋው በገዛ ሥልጣኑ ከለየባት ቅጽበት ወዲህ እንኳን የቅድስት ድንግል እናቱ የሌሎች ቅዱሳን ነፍስም የምትለየው በእርሱ እጅ ነው፡፡ ስለዚህ ነፍስዋን ተቀብሎ እልፍ አእላፍ መላእክት በቀኝ በግራ፥ በፊት በኋላ እያመሰገኑት ወደ መንግሥተ ሰማይ አሳርጓታል፡፡ ይህም ሰው በመጠኑ እንዲሰማው ያህል እንጂ ሙሉ በሙሉ ዘርዝሮ መናገር የማይቻል ነው። የታሪክ መጻሕፍት እንደሚያስረዱት ጌታ በዐረገ ጊዜ የተፈጸመው ሥርዓትና እመቤታችን ባረፈችበት ጊዜ የሆነው ነገር ዕፁብ በማለት ብቻ የሚወሰን ነው እንጂ አይመረመርም። የዕለተ ዕረፍትዋ ታሪክ ስለ ፍልሰታ በጻፍነው ተሟልቷል ያን መመልከት ነው፡፡
በዓሉ አስተርእዮ መባሉ ግን ሁለት ጠባይ ያሳያል። አንዱ ወራቱን ማለት ጥር ጌታችን በጥምቀቱ ምሥጢረ ሥላሴን፥ ከዚህም ጋር አምላክነቱን ለዓለም የገለጸበት በመሆኑ ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ የአምላክ እናት እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አምላክን በወለደችበት፥ ስብሐተ መላእክትን በሰማችበት፥ ባየችበት የልደት ወራት አካባቢ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይታ ወደ ሰማይ ስትወጣ በሰማይም በምድርም ለሰውም ለመላእክትም ከልጅዋ፥ ከባሕርይ አባቱ ከእግዚአብሔር አብ፥ ከባሕርይ ሕይወቱ ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ የተሰጣት ጸጋና ክብር መገለጡን ያሳያል። አስተርእዮ ማለት መታየት፥ መገለጥ ማለት ነውና፡፡
ኢትዮጵያውያን ሊቃውንት በዚህ ቃል ሐሳባቸውን ያስተባብራሉ። ቅዱስ ያሬድ አምላክ በሥጋ ከድንግል መወለዱን፥ በዚህ አካል መጠን ለዓለም መገለጡን አስተርእዮ ብሎ ሲናገር፤ ሌላው ሊቅ ደግሞ፤ ‹‹እግዚአብሔር ጽጌ ትንቢት ለቢሶ ሥጋኪ ሥጋ ዚአነ፤ ከመ አስተርአየ በምድር ወተአምረ ለነ፤ ንዌድሰኪ እንዘ ንብል ምክሐ ዘመድነ፤ ዮም በፍሥሓ ለማርያም እምነ አስተርእዮ በሰማይ ኮነ።» «የትንቢት አበባ እግዚአብሔር የእኛ ሥጋ የሆነውን ያንቺን ሥጋ ለብሶ በምድር እንደ ተገለጠ፥ ለእኛም እንደ ታወቀ፤ ድንግል ሆይ! የወገናችን መመኪያ ዛሬ ለእናታችን ለማርያም በሰማይ በፍጹም ደስታ መገለጥ ሆነ እያልን እናመሰግንሻለን፤›› ብሏል፡፡
ይህ በዓል እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከዚህ ዓለም ወደ ዘለዓለም ሕይወት የተሸጋገረችበት በመሆኑ ቤተ ክርስቲያን የዕረፍትዋን መታሰቢያ በክብር ታደርጋለች። ጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ ወደ ፊያታዊ ዘየማን መለስ ብሎ፤ ‹‹አንተ ሰው እመነኝ፤ ዛሬ በገነት ከእኔ ጋር ነህ፤›› ብሏል፡፡ ይህም ለቅዱሳን ሁሉ በዕረፍታቸው ጊዜ ከቸሩ አምላካቸው ለሚደረግላቸው ክብር በር ከፋች ሆኗል፡፡ እመቤታችንም በዚህ በዕረፍትዋ ቀን ከልጅዋ፥ ከፈጣሪዋ ልዩ ጸጋ ተደርጎላታል። በመጀመሪያ ዐብረዋት የኖሩት ልጆችዋ ቅዱሳን ሐዋርያት በሥጋ ያሉት ከየሀገረ ስብከታቸው ተሰብስበው፥ ከዚህ ዓለም የተለዩት በአካለ ነፍስ ተገኝተው የዕረፍቷን ጊዜ እየተጠባበቁ ሳሉ፤ እመቤታችን፤ ‹‹ማዕጠንት አምጡ፤ በጸሎትም ጌታችንን ኢየሱስ ክርስቶስን ጥሩት፤›› አለቻቸው፡፡ እነርሱም ትእዛዟን በመፈጸም ላይ ሳሉ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳን መላእክትን አስከትሎ በክብር፥ በጌትነት ተገለጠ። እናቱንም፤ ‹‹የተወደድሽ እናቴ ሆይ! ዛሬ ድካምና ሕማም ወደሌለበት ወደ ዘለዓለም መንግሥት ላሳርግሽ መጥቻለሁ፤ ወደ እኔ ነዪ፤›› እያለ ሲያነጋግራት ቅድስት ነፍስዋ ከክቡር ሥጋዋ በልጅዋ ሥልጣን ተለየች፤ ልጅዋም በክብር ተቀበላት። በዚህ ጊዜም ነቢዩ ዳዊት፤ ‹‹ወትቀውም ንግሥት በየማንከ በአልባሰ ወርቅ ዑጽፍት ወኁብርት፤›› እያለ ያመሰግናት ነበር። ቅዱሳን መላእክት፥ ነቢያት፥ ሐዋርያት፥ ጻድቃን፥ ሰማዕታት በዚያው ከበው ቆመው፤ «ጸጋን የተመላሽ ሆይ! እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነውና ደስ ይበልሽ፤» እያሉ ያመሰግኗት ነበር፡፡ በዚህ ዓይነት ጸጋና ክብር በልጇ ሥልጣን፥ በልጇ ቸርነት ወደ መንግሥተ ሰማያት አሳርገዋታል፡፡ ሥጋዋንም ቅዱሳን ሐዋርያት ለጊዜው ጌቴሴማኒ በተባለ ቦታ አሳርፈውታል። በሦስተኛው ቀን ግን መላእክት ከዚያ አፍልሰው በገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አኑረውታል። ከመቃብር እስከ ተነሣችበትና ፍጹም ዕርገት እስካገኘችበት እስከ ነሐሴ ፲፮ ቀን ለሁለት መቶ አምስት ቀኖች በዚያው ቆይቷል፡፡ በዕለተ ዕረፍቷ ብዙ ተአምራት ተደርገዋል። ለድውያን የፈውስ ጸጋ ታድሏል፥ ስሟን ለሚጠሩ ሁሉ ፍጹም በረከት ተሰጥቷል። የፈውስ ጸጋ ከደረሳቸው አንዱ ታውፋንያ ወይም ሶፎንያስ የሚባለው አይሁዳዊ ነው፡፡
ቅዱሳን ሐዋርያት የቅድስት ድንግል እመቤታችን አስከሬን ወደ ጌቴሴማኒ መቃብር በሚወስዱበት ጊዜ አስከሬንዋን ለማቃጠል የተሰለፉ የልጇና የእርሷ ጠላቶች ነበሩ። ስሙ እላይ የተጠቀሰው ሰውም አስከሬንዋን ከአልጋው ለመጣል ተረማምዶ ተደፋፍሮ ያልጋውን ሸንኮር ሲጨብጥ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ከሁለት ትከሻው ላይ በሰይፍ ቀጣው፤ ሁለቱ እጆቹ ከአልጋው ሸንኮር ላይ ተንጠልጥለው ቀሩ። ይህም ቅጣቱ ስላስደነገጠውና በይበልጥም ምክር ስለ ሆነው ወዲያውኑ ተጠጥቶ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክ፥ እርሷም ወላዲተ አምላክ መሆኗን አምኖ በእርሱ በልጇ ቸርነት፥ በእርሷ አማላጅነት ተማጽኖ ምሕረትና ይቅርታን ስለ ለመነ በቅዱሳን ሐዋርያት ጸሎት፥ በእመቤታችን አማላጅነት እጆቹ እንደ ነበሩ ተመልሰውለታል፡፡
በዕለተ ዕረፍትዋ የተደረገውን ሁሉ የታሪክ መጻሕፍት በሰፊው ዘርዝረው ያስረዳሉ እኛ ከዚህ የጠቀስነው በአጭሩ ነው፡፡
ጌታ በሕይወተ ሥጋ በዚህ ዓለም በነበረበት ጊዜ ሽቱ ለቀባችው ሴት ወንጌል በተሰበከበት ሁሉ ያቺ ሴት የሠራችው እንዲነገርላት፥ ወንጌል በተነበበበት ቦታ ሁሉ እንድትታሰብ ጌታ ቃል ሰጥቷል፡፡ (ማቴ. ፳፮፥ ፲፫።) እንግዲህ፤ ‹‹መርጫታለሁና አድርባታለሁ፤›› ሲል ለመሰከረላት አምላክን ለወለደች የተስፋችን መድረሻ፥ ፍጻሜ፥ የድኅነታችን ምክንያት ለሆነችው ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም በቤተ ክርስቲያን ወንጌል በሚነበብበት፥ አምላክን የመውለዷ ምስክርነት በሚሰጥበት ቦታ ሁሉ ልናስባት ልናከብራት ይገባል፡፡
ይህም ብቻ አይደለም። እኛ ስሟን ብናከብር፥ መታሰቢያዋን ብናደርግ የምንጨምርላት ክብር የለም፤ ባናደርግም የምናጎድልባት ነገር የለም። እግዚአብሔር አንድ ጊዜ እናቱ እንድትሆን በመምረጥ ከፍጥረት ሁሉ አልቋታል፤ አክብሯታልና፡፡
ስለዚህም፤ ‹‹ወቢጻሂ ይወስዱ ለከ።» «ባልንጀሮቿን ላንተ ይወስዱልሃል።» ‹‹ህየንተ አበውኪ ተወልዱ ለኪ ደቂቅ።» «በአባቶችሽ ፈንታ ልጆች ተወለዱልሽ።» ‹‹ወትሰይሚዮሙ መላእክተ ለኵሉ ምድር።» «ለምድር ሁሉ አለቆች አድርገሽ ትሾሚያቸዋለሽ።›› ‹‹ወይዘክሩ ስመኪ በኵሉ ትውልደ ትውልድ።» «ለዘለዓለም ስምሽን ይጠራሉ።» ‹‹ዕግትዋ ለጽዮን ወሕቀፍዋ።» «ጽዮንን ክበቧት ዕቀፏት።›› ‹‹ወተናገሩ በውስተ መኅፈዲሃ።» «በቤቷ ውስጥም በጸሎት በምስጋና ተነጋገሩ።›› ‹‹ደዩ ልበክሙ ውስተ ኃይላ።» «ልባችሁን በረድኤቷ ላይ አሳርፉ።›› ‹‹ወትትካፈልዎ ለክበዲሃ።» «ሀብቷን በረከቷን ትካፈላላችሁ፤›› ይላልና፤ በፍቅሩ ተማርከው እርሷን መስለው በድንግልና እግዚአብሔርን ለማገልገል የቆረጡ ደናግል፥ በጸሎት በምስጋና ስሟን የሚጠሩ፥ በልጇ ቸርነት፥ በእርሷ አማላጅነት የሚታመኑ ምእመናን ሁሉ በረከቷን ይሳተፋሉ፤ ልጆቿ ተብለው ይጠራሉ። ወላዲተ አምላክ መሆኗን፥ ክብሯን፥ ድንግልናዋን፥ ንጽሕናዋን፥ ቅድስናዋን የሚመሰክሩ፥ ስምዋን ለልጅ ልጅ የሚያስተምሩ መምህራን ሊቃውንትም በቤተ ክርስቲያን ወንበር ላይ ይሾማሉ። ስለዚህ ሁልጊዜ፤ ‹‹ሰአሊ ለነ ቅድስት።» «ቅድስት ሆይ ለምኝልን፤ አማልጅን፤›› እያልን በጸሎት ልንጠራት ይገባል፡፡
ይልቁንም እኛ ኢትዮጵያውያን በዚህ ሁኔታ እጅግ በጣም ከፍ ያለ አስተሳሰብና አስተያየት ሊኖረን ያሻል፡፡ ባዕድ ባዕድ ነው። ሰው ከተባለ የወላጆቹን ክብር የማያስቀድም የለም፤ ለእርሱ የክብሩ መሠረቶች ናቸውና፡፡ አንደበታቸውን የማይገቱ ሰዎች ተላልፈው የወላጆቹን ክብር ቢነኩበት እስከ መሞት ወይም እስከ መግደል ይደርሳል፤ ይህም እንኳ ባይሆን ከዚያ ቀን ጀምሮ የወላጆቹን ክብር ከደፈሩት ሰዎች ጋር ያለውን አንድነት ያቋርጣል፡፡
ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች ለእመቤታችን የዐሥራት ልጆቿ ናቸው፡፡ እነርሱም ይህን ዐውቀው ክብሯን ጠብቀው ይኖራሉ። ነቢዩ ዳዊት ስለ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያውያን በመዝሙር ፹፮/፹፯ በተናገረው ቃል እንዲህ ይላል፤ ‹‹ወሕዝበ ኢትዮጵያ እለ ተወልዱ በህየ፤ እምነ ጽዮን ይብል ሰብእ።» «በዚያው ከተወለዱት ከኢትዮጵያ ሰዎች ሰው እናታችን ጽዮን ይላል፤›› ብሏል፡፡
እንግዲህ፤ ‹‹ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች፤›› ከሚለው ቃል ጋር፤ «ሰው እናታችን ጽዮን ይላል፤» የሚለው ቃል የኢትዮጵያውያንን ዕድል እንደሚያመለክት አያጠራጥርም። አባቶቻችን በዚህ ተጠቅመውበት ኖረዋል፡፡ ጸጋውም ከእነርሱ ለልጆቻቸው በመተላለፍ ደርሷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከልዩ ልዩ ዓለም የተሰበሰቡ ባዕዳን ከእግዚአብሔር ቃል ተላልፈው ከሥነ ሥርዓት ውጪ በእመቤታችን ላይ ክርስቲያኖች ሊናገሩት የማይገባ ቃል ሲናገሩ እንሰማለን፡፡
ከዚህም ይበልጥ እነዚያ በልጅዋ በአምላካቸው በኢየሱስ ክርስቶስ ቸርነት የልጅነት ማዕርግ የተሰጣቸው፤ ‹‹ስለ አባቶችሽ ፈንታ ልጆች ተወለዱልሽ፤ ስምሽን ለልጅ ልጅ ይጠራሉ፤›› ተብሎ ከተመሰከረላቸው ኢትዮጵያውያን መካከል አንዳንድ የባዕዳን ተባባሪዎች ሆነው ይታያሉ። አባትን እናትን በመድፈር የሚገኝ በረከት የለምና ኢትዮጵያውያን ሁሉ በቅድስት ድንግል እመቤታችን፥ በእግዚአብሔር በአምላካችን የማይገባ ቃል ከመናገር አንደበታችንን መግታት ይገባናል፡፡
ወደ ጥንተ ነገራችን እንመለስና ይህ በዕረፍትዋ ምክንያት በጥር ፳፩ ቀን የተጀመረው የበዓል መታሰቢያ በየወሩ ወር በገባ በ፳፩ ቀን እንዲታሰብ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሥርዓት ስለ ሆነ በየወሩ ወር በገባ በ፳፩ ቀን የዕረፍትዋ መታሰቢያ፥ በ፳፱ ቀንም አምላክን የመውለዷ መታሰቢያ ይከበራል። ይህም በቀድሞ የመባቻ በዓል ፈንታ የገባ ነው፤ ያ ጥላ ምሳሌ ስለ ነበረ አማናዊው ተተክቶበታል፡፡
(ወላዲተ አምላክ በኢትዮጵያ፤ ገጽ ፴፰ - ፵፭።)