መግቢያየሕይወት ታሪክመጻሕፍትየድምፅ ማኅደርቃለ ውግዘትግምጃ ቤት
 


ዐቢይ ጾም።
የካቲት ፲፫ ቀን ፪ሺ፩ ዓ∙ ም∙

ጾም በብሉይ ኪዳን በተወሰነ፥ ባልተወሰነ ጊዜም ይፈጸም ነበር። በሐዲስ ኪዳንም የዘወትርና የተወሰነ ጾም አለ።

የጾም መሠረቱ፤ «ቀድሱ ጾመ ወሰብኩ ምህላ፤» «ጾም ለዩ ምህላ ያሉ፤» የሚለው ነው። (ኢዮ፤ ፪፥ ፲፮ - ፲፰።) ጾም በብዙ ወገን ስለ ሆነ፤ ክፉ ከማየት ዐይንን፥ ክፉ ከመስማት ጆሮን፥ ክፉ ከመሥራት እጅን፥ ወደ ኀጢአት ከመሄድ እግርን፥ ክፉ ከመናገር መላስን፥ ክፉ ከማሰብ ልብን መከልከል ታላቅ ጾም ነው። ሥራውም ከፍጹምነት በላይ ነው።

ስለዚህ ቅዱስ ጾም መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲያስተምር ልቡናቸውን ከክፉ ዐሳብ ንጹሕ ያደረጉ ሰዎች ብፁዓን ናቸው፤ እነሱ እግዚአብሔርን ያዩታል ብሏል። (ማቴ፤ ፭፥ ፯።)

አንደበትን ክፉ ከመናገር መከልከል ስለሚገባ፤ «ከትእዛዛት አንዲቱ ታንሳለች፥ አንዲቱ ትበልጣለች ብሎ ለሌላው የሚያስተምር፥ ራሱም የሚሠራ በመንግሥተ ሰማያት ታናሽ ይሆናል፤ ከትእዛዛት አንዲቱ ካንዲቱ አታንስም ብሎ ራሱ የሚሠራ፥ ለሌላው የሚያስተምር በመንግሥተ ሰማያት ታላቅ ይሆናል።» (ማቴ፤ ፭፥ ፲፱።)

ከእናንተ አስቀድሞ ለነበሩ ሰዎች በሐሰት አትማል ተብሎ ነበር፤ እኔ ግን በሰማይ፥ በምድር፥ በኢየሩሳሌም (ቤተ ክርስቲያን)፥ በራሳችሁም አትማሉ ብያችኋለሁ። ሰማይ የእግዚአብሔር ዙፋን ምድርም መመላለሻው፥ ኢየሩሳሌምም አገሩ ናትና። ከራስ ጠጒራችሁም አንዱን ነጭ፥ አንዱን ጥቊር ማድረግ አትችሉምና። (ማቴ፤ ፭፥ ፴፫ - ፴፮።)

እጅን ክፉ ከመሥራት ስለ መከልከል፤ «ከእናንተ አስቀድሞ ለነበሩ ሰዎች ነፍስ አትግደል፤ የገደለ ይፈረድበታል አንደ ተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን ወንድሙን በከንቱ የሚያሳዝን ኃጥእ ነው፤ ይፈረድበታል ብያችኋለሁ። ቀኝ እጅህ ምክንያተ ስሕተት ሆና ብታስትህ ቈርጠህ ጣላት።» ዐይንን ክፉ ከማየት ስለ መከልከል፤ «ቀኝ ዐይንህ ምክንያተ ስሕተት ሆና ብታስትህ አውጥተህ ጣላት።»

በኢየሱስ ክርስቶስ አምናችሁ ጸንታችሁ የምትኖሩ ምእመናን ራሳችሁን መርምሩ። ክፉ ከመስማት ጆሮአችሁን፥ ክፉ ከማየት ዐይናችሁን ከልክሉ።

እግርን ከክፉ ስለ መጠበቅ፤ «ቀኝ እግርህ ምክንያተ ስሕተት ሆና የማይገባ ሥራ ብታሠራህ ቈርጠህ ጣላት፤ ሙሉ ሰውነት ኖሮህ በኋላ ገሃነመ እሳት ከምትገባ በዚህ ዓለም አንድ ዐይን፥ አንድ እጅ፥ አንድ እግር ሆነህ ኖረህ ኋላ መንግሥተ ሰማያት ብትገባ ይሻልሃል፤» ብሎ አስተምሮናል። (ማቴ፤ ፭፥ ፳፩ - ፴።)

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዐይንህን አውጣ፤ እጅህን እግርህን ቈርጠህ ጣል ብሎ ሲያስተምረን ሰው ሁሉ ዕውር፥ አንካሳ፥ ቈራጣ ሆኖ በችግር እንዲኖርና ሌላውንም በልመና እንዲያስቸግር አይደለምና የሚመስለው ሰው ቢኖር ይህ የመድኃኒታችን ትእዛዝ ሰውነታችንን በሕግ፥ በሥርዐት ሠርተን፥ ቀጥተን፥ ወስነን እንድንኖር የሚያመለክት ስለ ሆነ ይህንኑ ዐውቆ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ምክንያት ከመፍጠር ይጠበቅ።

በእውነተኛ ሕግ ጸንቶ የሚኖር፥ እውነት ነገርን የሚናገር፥ የኃጢአትን መንገድ የሚጠላ፥ ጉቦ ከመቀበል እጁን፥ ክፉ ከመስማት ጆሮውን፥ ግፍ ከማየት ዐይኑን የሚከለክል፤ እንዲህ ያለ ሰው ከልዑል እግዚአብሔር በሚደረግለት ጽኑዕ ረድኤት ከመከራው ሁሉ ተጠብቆ ይኖራል።

አንደኛው ጾም ይህ ነው።

ሁለተኛው ጾም ግን ከምግብ መከልከል ነው። ስለዚህ ማንኛውም ጸዋሚ ሰው እንዳገኘ ከበላ፥ እንዳገኘ ከጠጣ ሰውነቱን ወስኖ፥ ገቶ መኖር አይቻለውምና ለሰውነት ኃይል፥ ጽንዕ፥ ልምላሜ ከሚሆኑት የምግብ ዐይነቶች ተከልክሎ ሐገ ጾምን ይፈጽማል።

ጾም ሰው ከእንስሳት የሚለይባት፥ ከመላእክት ጋራ የሚመሳሰልባት ታላቅ ምስጢር ስለ ሆነች፤ እንደ እንስሳት ሰዓት፥ ጊዜ ሳይወስኑ ከጧት እስከ ማታ ከመብላትና ሥጋንም ለአፈር ከማስባት ተከልክሎ በጸሎት፥ በትዕግሥት፥ በኀዘን፥ በለቅሶ የሚፈጽማት ሕግ ናት።

ሕግነቷም በብሉይ ኪዳን፤ «ጾም ለዩ፤» ብሎ ያዘዘ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ፤ «ስለ ጽድቅ የሚራቡና የሚጠሙ ብፁዓን ናቸው፤» ሲል በመጀመሪያ ትምህርቱ በዐዋጅ ያዘዛት፥ ያጸናት የማትለወጥ፥ የማትናወጥ ሕገ እግዚአብሔር ናት እንጂ፤ እንደ እንግዳ ድንገተኛ ደራሽ፥ እንደ ጎርፍ ድንገተኛ ፈሳሽ ወይም ሰው ሠራሽ ሕግና ልብ ወለድ ተረት አይደለችም። (ማቴ፤ ፭፥ ፮።)

በጾም ሕግ የተወሰነና ያልተወሰነ የሚል አከፋፈል አለበት። የተወሰነ ጾም፤ በክርስቶስ አምኜ ጸንቼ እኖራለሁ የሚል ሰው እሱ እንደ ሄደ ሊሄድ፥ እሱ እንደ ኖረ ሊኖር ስለሚገባው መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ እንደ ጾመ እኛም እሱን መሪ አብነት አድርገን የምንጾመው ጾም ነው። (፩ ዮሐ፤ ፪፥ ፮።)

በሥርዐተ ቤተ ክርስቲያን የተወሰነ ጾም በ፯ ክፍል ይከፈላል። አንደኛው ዐቢይ ጾም ነው። ይኸውም መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጾመው ነው። ይህ ጾም ዐቢይ ጾም፥ ጾመ ኢየሱስ፥ ሑዳዴ ተብሎ ይጠራል። (ማቴ፤ ፬፥ ፩ - ፲፩።)

ዐቢይ ጾም መባሉ አንደኛ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበልነው ስለ ሆነ፤ ሁለተኛ የሰው ድኅነቱ ዓለም ከተፈጠረ ዐምስት ሺሕ ዐምስት መቶ ዘመን በኋላ ለመፈጸሙ መታሰቢያ ስለ ሆነ፤ ከሌሎቹ በበለጠ ዐምሳ ዐምስት ቀን ስለሚጾምና በመጨረሻውም በአክፍሎት መሠረትነት ሦስት መዓልት ሦስት ሌሊት ስለሚጾም ነው።

ከዐሙስ ማታ እስከ እሑድ መንፈቀ ሌሊት የሚፈጸመው የአክፍሎት ጾም መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዐሙስ ማታ ከደቀ መዛሙርቱ ጋራ በማእድ ላይ ተቀምጦ ሳለ፤ «በአባቴ መንግሥት አዲሱን እስክጠጣው ድረስ እንግዲህ ከዚህ የወይን ጭማቂ አልጠጣም፤» ሲል በንግግር የመሠረተው፤ በኋላም እሱ በመቃብር እነሱ በኀዘን ሦስቱን ቀን አሳልፈው በገሊላ በትንሣኤው በተገናኙ ጊዜ፤ «ልጆቼ! አንዳች የሚበላ ነገር አላችሁን?» ብሎ ጠይቆ የማር ወለላ፥ የተጠበሰ ዓሣ አቅርበውለት በመብላት የፈጸመው ነው። (ማቴ፤ ፳፮፥ ፳፱። ሉቃ፤ ፳፬፥ ፵ - ፵፫።)

ኢትዮጵያ፤ ነቢዩ ኢሳይያስ፤ «ለለ ዓመት ወለለ መዋዕል ደንግፃ ወተክዛ ዕለተ ሕማም እንዘ ትትሔዘባ።» «በየዓመቱ በየዘመኑ የሞቱን የሕማሙን ቀን እያሰባችሁ እዘኑ፤ አልቅሱ፤» ብሎ በቃል ያስተማራትን፥ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃል በሥራም ያስጠናትን ይህንን ጾም አክብራ ጠብቃ እስከ ዛሬ አለች፤ ትኖራለች። (ኢሳ፤ ፴፪፥ ፱።)

ጻፎችና ፈሪሳውያን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን፤ «የእኛና የዮሐንስ ደቀ መዛሙርት ይጾማሉ፤ ደቀ መዛሙርትህ ለምን አይጾሙም፤» ብለው ቢጠይቁት፤ «ሙሽራ ከእነሱ ጋራ ሳለ የሙሽራ ሚዜዎች ሊጾሙ አይችሉም፤ ነገር ግን ሙሽራው ከእነሱ የሚለይበት ጊዜ ይመጣልና ማለት አይሁድ እኔን ከደቀ መዛሙርቴ ለይተው የሚሰቅሉበት ጊዜ ይመጣልና ያን ጊዜ ይጾማሉ፤» ብሏቸዋል። (ሉቃ፤ ፭፥ ፴፫ - ፴፭።)

ስለዚህ ክርስቲያን ክርስቶስ ከሞተበት ቀን ጀምሮ ራሱ ሊቀ ካህናት ክርስቶስ፥ አገልጋዮቹ ነቢያትና ሐዋርያት የፈጸሙትን የጾም ሕግ በትሕትና በመታዘዝ ያለ ማንጐራጐር ይፈጽማሉ።

በብሉይ ኪዳን ልዩ ልዩ ዐይነት ጾም ነበር። ጸዋሚዎችም ፍርድ እያደሉ፥ መማለጃ እየበሉ፥ ወንድማቸውን እየበደሉ፥ ብድራታቸውን እየተከፈሉ ያለሚገባ ይጾሙት ነበር። ስለዚህም ጾሙ ዋጋ ሊሰጣቸው አልቻለም። (ኢሳ፤ ፶፰፥ ፫ - ፬።)

አዲስ ጨርቅ ከአሮጌ ጨርቅ እንዳይጣፍ፥ ቢጣፍም አዲሱ አሮጌውን እንዲጎትተው፥ መቀደዱም እየባሰው እንዲሄድ፤ የብሉይ ኪዳን ጾም ለክርስቲያን እንዳይገባቸው መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስረድቷል። እንዲሁም አዲስ የወይን ጠጅ በአሮጌ ዕቃ እንዳይቀመጥ፤ ቢቀመጥ ግን አዲሱ የወይን ጠጅ አሮጌውን ጋን ይሰብረዋል፤ ጠጁም ይፈሳል፤ ዕቃውም ይበላሻል። እንዲሁ የሐዲስ ኪዳን ጾም የሙሴ ደቀ መዛሙርት ነን ለሚሉ ለጻፎችና ለፈሪሳውያን እንደማይስማማ በግልጥ ተናግሯል። (ሉቃ፤ ፭፥ ፴፮ - ፴፱።)

ከዚህ በኋላ አዲሱ የወይን ጠጅ በአዲስ ዕቃ ይደረጋል፤ ሁለቱም ይጠባበቃሉ፤ ብሎ ያዲሲቱ ሕግ የወንጌል ጾም ለአዲሶቹ ምእመናን ክርስቲያን እንደ ሆነ አስተማረ። ስለዚህ ክርስቲያን ሁሉ በብሉይ ኪዳን በነበረው ጾም ፈንታ ቤተ ክርስቲያን የሰጠቻቸውን ሰባቱን አጽዋም በሕግ ይጾማሉ። እነዚህም አንደኛ ጾመ ኢየሱስ፥ ሁለተኛ ጾመ ድኅነት፥ ሦስተኛ ጾመ ነነዌ፥ አራተኛ ጾመ ሐዋርያት (ሰኔ)፥ ዐምስተኛ ጾመ ፍልሰታ (ነሐሴ)፥ ስድስተኛ ጾመ ነቢያት (ገና)፥ ሰባተኛ ገሃድ (ጋድ) ናቸው። እነዚህ አጽዋም በሕግ የታወቁ፥ በቤተ ክርስቲያን የተጠኑ ስለ ሆኑ በግልጥ ይጾማሉ።

ከእነዚህ ሌላ መብል ለሆድ ነው፤ ያጸናዋል፤ ሆድም ለመብል ነው፤ ይሸከመዋል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ሁለቱንም ያሳልፋቸዋል። መብል አይረባንም፥ አይጠቅመንም፤ ያለውን ቃል ያወቁ፥ የጠበቁ ፍጹማን ምእመናን፤ እንብላ፥ እንጠጣ ነገ እንሞታለን በማለት ፈንታ፤ ነገ እንሞታለንና እንጹም፥ እንጸልይ በማለት የሚጾሙት ጾመ ፈቃድ አለ። ይህ ጾም በስውር ይጾማል። ስለዚህም ጾመ ፈቃድ ይባላል። ጾምን የሚፈጽሙ ስለ ጽድቅ የሚራቡና የሚጠሙ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደ መሰከረላቸው ብፁዓን ናቸው። ይህ ብፅዓን እንዳይቀርብን እንጹም፥ እንጸልይ።

የጾም ተቃዋሚው ምክንያት መፍጠር ነው። አንዳንድ ሰዎች መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምትጾሙበት ጊዜ ፊታችሁን ታጠቡ፥ ራሳችሁን ተቀቡ ብሏል። ክፉ ካልሠራን ሥጋ፥ ቅቤ ብንበላ፥ ወተት ብንጠጣ ምን አለበት ይላሉ። ይህ ምክንያት ለመፍጠር ነው እንጂ በእውነቱ በልቶ፥ ጠጥቶ ፈቃደ ሥጋን ወስኖ ገቶ መኖር የሚቻል ሆኖ አይደለም። (ማቴ፤ ፮፥ ፲፮ - ፲፰።)

ከሁሉ አስቀድሞ የመድኀኒታችን ንግግር ረቂቅ ምስጢር መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል። ሰዎች ሥጋዊ ፈቃዳቸውን ሳይተዉ በኀጢአት ላይ ኀጢአት እየሠሩ ፥ በክፋት ላይ ክፋትን እየጨመሩ ሰውነታቸውን ከበደል፥ ልቡናቸውን ከቂም ከበቀል ሳይከለክሉ፤ በቁጠባና በማጣት ምክንያት የሚፈጽሙትን ጾም ቁም ነገር አድርገው እንጾማለን፥ እንጸልያለን እግዚአብሔር ግን አይሰማንም ይላሉ።

ክርስቶስ፤ በጾማችሁ ጊዜ ፊታችሁን ታጠቡ፤ ራሳችሁን ተቀቡ፤ ብሏል፤ ብንበላ፥ ብንጠጣ ምን አለበት የሚሉትና፥ ብንጾም ብንጸልይ እግዚአብሔር አይሰማንን የሚሉት ሁለቱ ምክንያቶች ከእውነት ውጭ ናቸው። እውነትስ፤ ክርስቶስ፤ በጾማችሁ ጊዜ ፊታችሁን ታጠቡ፤ ሲል እያለቀሳችሁ፤ ራሳችሁን ተቀቡ፤ ሲል ፍቅርን ይዛችሁ ጹሙ ማለቱ እንደ ሆነ ማወቅ ነው። አይሰማንም ለሚሉትም እግዚአብሔር በጾማችሁ ጊዜ ፈቃዳችሁን እየፈጸማችሁ ጾምነ አልሰማኸንም ትሉኛላችሁ፤ ሰው በኃጢአት ጾም እንደ ሸረሪት ድር ወይም እንደ ቀለበት አንገቱን ቢያቀጥን እንዲህ ያለውን ጾም አልፈቅደውም፤ ይስማን ካላችሁ፤ ሰውነታችሁን ከበደል፥ ልቡናችሁን ከቂም ከበቀል ለይታችሁ ጹሙ ብሎ እንዳዘዘ ማስተዋል ነው።

ጾም እንደ ምክንያት ፈጣሪዎች ወይም በማጣትና በቁጠባ ምክንያት አንደሚጾሙት ሰዎች ዐሳብ አይደለችምና ሥርዐቷ፥ ሰዓቷ፥ ጥቅሟ በእውነት የታወቀላት፥ በቃልም ሆነ በሥራ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሠራት፥ የፈጸማት፥ ለደቀ መዛሙርቱ ያዘዛት እውነተኛ ሕግ መሆኗን ዐውቀን ከሥጋ፥ ከቅቤ፥ ከሚያሰክር መጠጥ፥ ከክፉ ሥራ ሁሉ ተከልክለን እንፈጽማት።

አባታችን ሆይ! እውነተኛውን ጾም እንድትገልጽልን፥ ለመፈጸም እንድታበቃን፥ እንዲሁም ክፉ ዐሳብን የሚፈጥረው ይህ የሥጋ ዘመድ ያለ ጾምና ያለ ጸሎት አይወጣምና በጾምና በጸሎት ድል እንድንነሣው ታደርገን ዘንድ ፈቃድህ ይሁን። አሜን።

 

ተጨማሪ ገጾች።
 ዜናዎች
 አስተያየቶትን ይጻፉልን
 የ aleqayalewtamiru.org አባል ይሁኑ
ይህንን ገጽ ለወዳጆችዎ ያሳውቁ።
የኒውስሌተራችን ተጠቃሚ ይሁኑ
በየጊዜው የሚደረጉ ለውጦችን ለማወቅ ይመዝገቡ።
ሙሉ ሥም
የኢሜይል አድራሻ
መውረድ የሚችሉ ፋይሎች
የክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ የመንፈቅ መታሰቢያ። (.zip, 28.3 MB)
የክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ የመንፈቅ መታሰቢያ። (light weight) (.zip, 2.4 MB)
Unable to read the text?
Download Font (nyala.ttf, 427KB)
For PC users: download and save the font file in "C:\Windows\Fonts" folder and restart your browser
(Nyala.ttf, © 2006 Microsoft Corporation. All Rights Reserved. Nyala is either a registered trademark or a trademark of Microsoft Corporation in the United States and/or other countries.)
መግቢያየሕይወት ታሪክመጻሕፍትየድምፅ ማኅደርቃለ ውግዘትግምጃ ቤት
Copyright  , aleqayalewtamiru.org