መግቢያየሕይወት ታሪክመጻሕፍትየድምፅ ማኅደርቃለ ውግዘትግምጃ ቤት
 


የክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ ዕረፍት ፯ኛ ዓመት መታሰቢያ።
ነሐሴ ፲፬ ቀን ፳፻፮ ዓ. ም.

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ አሜን።

ነሐሴ ፲፬ ቀን ፲፱፻፺፱ ዓ. ም. ከዚህ ዓመት የተለዩት የታላቁ ሊቅ የአለቃ አያሌው ታምሩ (አቡነ ወልደ ጊዮርጊስ) ፯ኛ ዓመት የዕረፍታቸው መታሰቢያ ነሐሴ ፲፬ ቀን ፳፻፮ ዓ ም በጸሎት ታስቦ ውሏል። በዚሁ ዕለት በደብረ አሚን ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከቤተ ልሔሙ አጠገብ ከሚገኘው የመቃብራቸው ሥፍራ ላይና በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ዳዊት ተደግሞ የጸሎት ሥነ ሥርዓት ተደርጎአል።

በዚሁ ሥነ ሥርዓት ላይ ከሊቁ ቤተ ሰብ በተጨማሪ በቅርብ የሚያውቁኣቸው ወዳጅ ዘመድ እንዲሁም፤ የጸሎት ሥነ ሥርዓቱን የመሩ ጥቂት ካህናተ እግዚአብሔር ተገኝተዋል።

በደብረ አሚን ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከቤተ ልሔሙ አጠገብ ከሚገኘው የመቃብራቸው ሥፍራ ላይ የሊቁን ስም፥ ሥዕልና የሕይወት ዘመን የሚያሳይ ምልክት የቆመ ሲሆን በምልክቱ ላይ ከሊቁ ቃል የሚከተለው ተቀርጾኣል። «እግዚአብሔር መንፈሳውያን ሰዎቹን፤ «ክላህ በኃይልከ ወአንሥእ ቃልከ ወኢትምሀክ፤» «በኃይል ድምፅህን አሰማ፤ ይሉኛል አትበል፤» እያለ ሲቀሰቅሳቸው መኖሩ ይታወቃል። በዚህም ምክንያት ነቢያትና ሐዋርያት፥ ተከታዮቻቸውም በሰው ፊት፥ በዓለም እየተናቁና እየተጠሉ ፍቅሩን፥ አደራውን ሲመሰክሩ ኖረዋል። ዛሬም ያለነው የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ይበልጡን በከፍተኛ አመራር ላይ ያሉ አባቶች ስለ ኢትዮጵያ፥ ስለ ትውልዷ፥ ስለ ቤተ ክርስያኗ፥ ስለ ሃይማኖቷ፣ ስለ ታሪኩዋ ተጠያቂዎች ናቸው፤ ተጠያቂዎች ነን። ሌላ ማድረግ ባይቻል እንኩዋ ድምፅን ማሰማት ከቤተ ክርስቲያን በኩል የሰውም፥ የእግዚአብሔርም ግዴታ ነው። (አለቃ አያሌው ታምሩ ለቅዱስ ሲኖዶስ ከጻፉት ደብዳቤ የተወሰደ።)

የጸሎት ሥነ ሥርዓቱ ከተጠናቀቀ በኁኣላ በቦታው የተገኙ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ስለ በዓሉ እንዲሁም ስለ ሊቁ ቅን እምነት፥ ሊቅነት፥ ስለ ጠባያቸውና ለቤተ ክርስቲያን ስላደረጉት ተጋድሎ ያላቸውን ትዝታ የገለጡ ሲሆን፤ ከዚህም በተጨማሪ ሊቁ ካረፉበት ጊዜ አንሥቶ ባሉት ፯ ዓመታት ውስጥ ሊቃውንት እያነሱ፥ የቤተ ክርስቲያን ጉዳትም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ መሄዱን፤ ይህም በእጅጉ የሚያሳዝን መሆኑን አመልክተዋል። ስለ ሆነም፤ ምእመናንም ሆነ የቤተ ክርስቲያን አባቶች የታላቁን ሊቅ አርኣያ በመከተል በቀናችው እምነት ጸንተን ቤተ ክርስቲያናችንን መጠበቅ እንዳለብን አሳስበዋል።

ከዚህ በመቀጠል የክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ የበኩር ልጅ የሆኑት ወ/ሮ ሥምረት አያሌው ቤተ ሰቡን በመወከል ባደረጉት ንግግር፤ ሊቁ ካረፉበት ጊዜ አንሥቶ ከቤተ ሰባቸው ሳይለዩ ያጽናኑትንና በየዓመቱ በሚከበረው የመታሰቢያቸው ሥነ ሥርዓት ላይ ተሳትፎ ያደረጉትን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን አመስግነዋል። እሳቸውም በበኩላቸው ሊቁን በሥጋዊ አባትነታቸው ብቻ ሳይሆን በመን,ፈሳዊ አባትነታቸውም ጭምር የሚያስታውሱባቸውን መልካም ነገሮች አቅርበዋል። እንዲሁም ሊቁ ለቤተ ክርስቲያን ያደረጉት ተጋድሎ፤ ከቤተ ክርስቲያን አባቶች ጋር የግል ቅራኔ ኖሯቿው ያደረጉት ሳይሆን፤ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት፥ ሥርዓትና ታሪክ ከልጅነታቸው ጀምሮ ካላቸው ቅናት በመነሣት መሆኑን፤ ይህንንም ሁሉም ሊገነዘበው የሚገባ መሆኑን አመልክተዋል። በመሆኑም ምእመናንም ሆነ የቤተ ክርስቲያን አባቶች የታላቁን ሊቅ አርኣያ በመከተል በቀናችው እምነት ጸንተን ቤተ ክርስቲያናችንን መጠበቅ እንዳለብን አሳስበዋል።

በመጨረሻ ለበዓሉ መታሰቢያ የተዘጋጀው ጠበል ጠዲቅ በሥነ ሥርዓቱ ተሳታፊዎች ከተቀመሰና ለነዳያንም ከቀረበ በኁኣላ የመታሰቢያ ሥነ ሥርዓቱ ፍጻሜ ሆኖአል።

እግዚአብሔር አምላካችን በቸርነቱ ብዛት፤ የአገልጋዩን የአባታችንን (አቡነ ወልደ ጊዮርጊስ) ነፍስ፤ በእመቤታችን በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፤ በአብርሃም፣ በይስሐቅ፣ በያዕቆብ አጠገብ፣ በገነተ ትፍሥሕት፣ በመካነ ዕረፍት ያሳርፍልን ዘንድ፤ ከበረከታቸውም ያድለን ዘንድ፤ እንለምነዋለን፡፡

ክቡር አባታችንን ዐጭር የሕይወት ታሪክ ለማንበብ ከዚህ ይጫኑ፡፡

 

ተጨማሪ ገጾች።
 ዜናዎች
 አስተያየቶትን ይጻፉልን
 የ aleqayalewtamiru.org አባል ይሁኑ
ይህንን ገጽ ለወዳጆችዎ ያሳውቁ።
የኒውስሌተራችን ተጠቃሚ ይሁኑ
በየጊዜው የሚደረጉ ለውጦችን ለማወቅ ይመዝገቡ።
ሙሉ ሥም
የኢሜይል አድራሻ
መውረድ የሚችሉ ፋይሎች
የክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ የመንፈቅ መታሰቢያ። (.zip, 28.3 MB)
የክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ የመንፈቅ መታሰቢያ። (light weight) (.zip, 2.4 MB)
Unable to read the text?
Download Font (nyala.ttf, 427KB)
For PC users: download and save the font file in "C:\Windows\Fonts" folder and restart your browser
(Nyala.ttf, © 2006 Microsoft Corporation. All Rights Reserved. Nyala is either a registered trademark or a trademark of Microsoft Corporation in the United States and/or other countries.)
መግቢያየሕይወት ታሪክመጻሕፍትየድምፅ ማኅደርቃለ ውግዘትግምጃ ቤት
Copyright  , aleqayalewtamiru.org