«እውነትን ዐውቀው በክፋታቸው በሚለውጡአት በዐመፀኛውና በኃጢአተኛው ሰው ሁሉ ላይ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መቅሠፍት ከሰማይ ይመጣል። እግዚአብሔርን ማወቅ በእነሱ ዘንድ የተገለጠ ነውና፤ እግዚአብሔርም ገለጠባቸው። ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ታይቶ የማይታወቅ እግዚአብሔር የፈጠረውን ፍጥረት በማሰብ በመመርመር ይታወቃል፤ ከሃሊነቱ፥ የዘለዓለም ጌትነቱም እንዲህ ይታወቃል፤ መልስ የሚሰጡበት ምክንያት እንዳያገኙ። እግዚአብሔርን ሲያውቁት እንደ እግዚአብሔርነቱ አላመኑትም፤ አላመሰገኑትምና፤ ካዱት እንጂ፤ በገዛ ዐሳባቸው ረከሱ፤ ልቡናቸውም ባለማወቅ ተሸፈነ። እንራቀቃለን ሲሉ ደነቆሩ። የማይሞተውን የእግዚአብሔርን ክብር ለውጠዋልና፤ የሚሞት የሰውን መልክ አምሳያ አድርገዋልና፤ በእንስሳ አምሳያ፥ በአራዊት አምሳያ፥ በአዕዋፍ አምሳያ አድርገዋልና። ስለዚህም መልሶ ተዋቸው፤ በገዛ እጃቸው ራሳቸውን እንዲያረክሱ፤ ሰውነታቸውንም እንዲያጎሰቁሉ። የእግዚአብሔርንም አምላክነት ሐሰት አድርገዋታልና፤ ተዋርደውም ፍጥረቱን አምልከዋልና፤ ሁሉን የፈጠረውን ግን ተዉት፤ ይኸውም ለዘለዓለም የሚኖር የባሕርይ አምላክ ነው።» (ሮሜ፤ ፩፥ ፲፰ - ፳፭።)
የተወደዳችሁ ምእመናን!
በቅርቡ በመገናኛ ብዙኃን (አዲስ አድማስ ጋዜጣ፥ ሰኔ ፳፮ ቀን ፳፻፪ ዓ. ም.) የቀረበውን ለፓትርያርክ አባ ጳውሎስ በአዲስ አበባ ቦሌ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ሐውልት ሊቆም መታሰቡን በመግለጽ የቀረበውን ዜና በኀዘን አንብበናል። ይህ ሐሳብ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እምነት፥ ሥርዓትና ባህል ውጪ በመሆኑ፤ በኢትዮጵያ አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም የምንቃመው መሆኑን እየገለጽን ክቡር አባታችን አለቃ አያሌው ታምሩ የዛሬ ፲፬ ዓመት በገናናው ጋዜጣ አማካይነት ያስተላለፉትን ሁለተኛ ቃለ ግዝት እንድታነቡ እንጋብዛለን።
ገናናው ጋዜጣ፤ ሐምሌ ፭ ቀን ፲፱፻፹፰ ዓ. ም.
አለቃ አያሌው ታምሩ ሁለተኛውን ቃለ ግዝታቸውን ሰጡ።
«አንበሳ አገሣ፤ የማይፈራ ማነው? ጌታ እግዚአብሔር ተናገረ፤ የማይደነግጥ፥ የማይታዘዝ፥ የማይፈራ፥ የማይናገር ማነው?»
ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ካህናትና ምእመናን በሙሉ! በአሁኑ ጊዜ በኦርቶዶክሳዊው የሊቃውንት ጉባኤና በእምቢተኞች የቤተ ክርስቲያን መሪዎች መካከል በዚህ ዓመት በተለይም ከመጋቢት እስከ ዛሬ የሚደረገውን፥ በመደረግ ላይ ያለውን ሃይማኖታዊ ትግል በልዩ ልዩ መንገድ እንደ ተከታተላችሁ አምናለሁ።
አባቶቼ ካህናት፥ ወንድሞቼ፥ እኅቶቼ ምእመናንና ምእመናት! የሌኒን ጣዖት በአፍሪካ አንድነት ድርጅት አጠገብ፤ የሌኒን፥ የማርክስ፥ የኤንግልስ ጣዖታት ምስሎች በአብዮት ዐደባባይ፤ የልዩ ልዩ ወታደሮች ምስል በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አጠገብ በተሠራው ሐውልት ላይ፤ እንዲሁም በልዩ ልዩ ስፍራ ልዩ ልዩ ምስሎች ተሠይመው ማንም የአበባ ገጸ በረከት መሥዋዕት ሳይቀር ያቀርብላቸው በነበረበት፥ በየዐደባባዩ የደም መፍሰስ፥ የለቅሶ፥ የዋይታ ድምፅ ሲያስተጋባ በነበረበት በዚያ የ፲፯ ዓመት ትዝታ ማንም አባት ዐብሮአችሁ ያልነበረ ሲሆን በትግላችሁ ያልተለየሁ እግዚአብሔር የሾመላችሁ የወንጌል ሰባኪ ሐዋርያ እንደ ሆንኩ አምላኬም፥ እናንተም ምስክሮች ናችሁ።
ይሻላል ያሉት ኩል ዐይን አጠፋ ሆነና ይሆናሉ የተባሉ አባቶች በማንኛውም ጊዜ በዐደራ የተቀበሏትን ቤተ ክርስቲያንና ምእመናኖቿን በአምላካቸው ስም መጠበቅ ሲገባቸው ትናንትም ዛሬም የመንግሥት ደጋፊ ሆነው እያስቸገሩን ነው። ብዙ መናገር ይቻላል፤ ግን እታገሣለሁ። ሆኖም ቁም ነገሩን ማለፍ አልችልም። የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአበው ውግዘት ተጣሰ፤ የቤተ ክርስቲያን ክብር ተገሠሠ እያልን አቤቱታችንን እያሰማን መንግሥት በሃይማኖት አያገባኝም ብሎ እጁን አውጥቷል። አይጠይቀንም በማለት ይመስላል። የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች በዕብሪት፥ በትዕቢት በበደል ላይ በደል ሲጨምሩ፥ ኦርቶዶክሳዊውን የሊቃውንት ጉባኤ ሊያፈርሱ ሲፈልጉ በጉልበታቸው በሥልጣናቸው ተጠቅመው የቤተ ክርስቲያኒቱን አባሎች ከሥራና ከደመወዝ ሲያባርሩ፥ ይህም አልበቃ ብሎአቸው በክስ ሲያጉላሉ፤ ይህን ሁሉ እየሰማ፥ እያወቀ ፍርድ ሊሰጥ፥ ዐመፀኞችን ሊቀጣ፥ ቤተ ክርስቲያንን ከደረሰባት በደል ነጻ ሊያወጣ የሚገባው ሲኖዶስ የግፍ ግፍ ሚያዝያ ፴ ቀን ፲፱፻፹፰ ዓመተ ምሕረት አጽድቆ ባወጀው፥ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ሲል በጠራው የአምልኮ ጣዖት ሕግ ፓትርያርኩን በመንፈስ ቅዱስ ፈንታ በሲኖዶስ ሥልጣንና ተግባር አመራር ሰጪ፥ የሲኖዶሱን አባሎችም ለቤተ ክርስቲያን ተጠሪ መሆናቸው ቀርቶ ለፓትርያርኩ ተጠሪዎች በማድረግ በቤተ ክርስቲያን ላይ የአመልኮ ጣዖት ዐዋጅ ዐውጆአል።
ለዚህም ሐምሌ ፮ ቀን ፲፱፻፹፰ ዓመተ ምሕረት በዓሉን ለማክበር በመዘጋጀት ላይ ስለ ሆነ ይህ ስሕተት እንዲታረም በዓሉ ከመድረሱ በፊት ሕጉን ጳጳሳት ተሰብስበው ሚያዝያ ፴ ቀን ፲፱፻፹፰ ዓመተ ምሕረት አምልኮ ጣዖት ያወጁበትን፥ መንበረ ማርቆስን ነቅለው መንበረ ጣዖት የተከሉበትን ሕግ እንዲሽሩ፥ ወደ ጣዖትነት ያደጉትን ፓትርያርክም ከሥልጣን እንዲያነሡ በቃለ ግዝት ሰኔ ፳፯ ቀን ፲፱፻፹፰ ዓመተ ምሕረት በነጻው ፕሬስ በኩል በመብሩክ ጋዜጣ በፈጣሪዬ ስም መልእክት ማስተላለፌ ይታወሳል። እነሱ ግን ምንም እርምጃ አልወሰዱም፤ ጥያቄዬንም አልተቀበሉም። እግዚአብሔር አምላክ ግን ቦታውን ለጣዖት አልሰጠም፤ መንበሩንም አልለቀቀም። የሚሰማው ቢያገኝ እየተናገረ፥ ምክርና ተግሣፅ እየሰጠ ነው።
በሥልጣናቸው ተደግፈው እግዚአብሔርንና ቤተ ክርስቲያንን የሚዋጉትና በመንፈስ ቅዱስ አንዳኝም በማለት ትግላቸውን የቀጠሉት አቡነ ገሪማ፥ እንዲሁም የፓትርያርኩ አጋፋሪ ብርሃኑ መኮንን ግን የአድባራትን፥ የገዳማትን አስተዳዳሪዎችንና ካህናትን በማስተባበር በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን የቅድስት ሥላሴን መንግሥት ሽረው ጣዖት ሊያገለግሉ፥ በዓል ሊያከብሩ ፕሮግራም አውጥተዋል። ከልዩ ልዩ ጌጣጌጥ ጀምሮ እስከ ዊስኪ መጠጥ፥ ጮማ ቁርጥ ድረስ በብዙ ሺሕ የሚቆጠር የቤተ ክርስቲያን ገንዘብ እየወጣ ድግስ እየተዘጋጀ ነው። ስለዚህ እነሱ ቢንቁኝ አልደነቅም። ቃሉ ደግሞ አይናቅም። በጠቅላላ ቤተ ክህነትና መሪዎቹ ለእግዚአብሔር አንታዘዝም ያሉ ስለ ሆነ ካህናትና ምእመናን ለዐመፅ እንዳትተባበሯቸው፥ በዓሉን እንዳታከብሩ፥ ድግሱንም እንዳትበሉ በቤተ ክርስቲያን አምላክ ስም፥ በኢትዮጵያ አምላክ ስም እጠይቃችኋለሁ። ሊቃነ ጳጳሳት፥ ኤጲስ ቆጶሳት በአምልኮ ጣዖት ስም ሚያዝያ ፴ ቀን ያወጃችሁትን ሕግ እንድሽሩ፥ የሠየማችኋቸውንም እንድታነሡ፥ በቤተ ክርስቲያንና በምእመናኖቿ ላይ የጫናችሁትን ቀንበር እንድታስወግዱ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እጠይቃችኋለሁ። እምቢ ብትሉ ግን በቃለ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ፥ በቃለ ሐዋርያቱ አሁንም ገዝቼአለሁ።
የኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያ አለቃ አያሌው ታምሩ ዘዲማ ጊዮርጊስ።