የክቡር አባታችን የአለቃ አያሌው ታምሩ ዕረፍት ፪ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል ነሐሴ ፲፬ ቀን ፳፻፩ ዓ ም በደማቅ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዐት ተከብሮ ዋለ።
በዕለቱ ከጠዋቱ ፬ ሰዓት ላይ በደብረ አሚን ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን የክቡርነታቸው መቃብር በሚገኝበት ስፍራ ላይ ካህናተ እግዚአብሔር፥ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፥ ቤተሰብ፥ ወዳጅና ዘመድ እንዲሁም ተማሪዎቻቸው በተገኙበት የጸሎት ሥነ ሥርዐት ተካሂዷል።
በመቀጠልም ታላቁ አባት ለ፴፯ ዓመታት በኖሩበት፥ በጸለዩበት፥ በግዞት በኖሩበትና ጉባኤ ወንጌል ባካሄዱበት መኖሪያ ቤታቸው በመሄድ ጸሎተ ፍትሐት ተከናውኗል።በዚሁ ጊዜ የክቡር አባታችንን ሕይወት የሚያዘክሩ ቅኔዎችና ዝማሬዎች ቀርበዋል። የቅኔዎቹና የዝማሬዎቹ ምስጢርና ውበት የሥነ ሥርዐቱን ታዳሚዎች ልብ የነካ ነበር።
በሥነ ሥርዐቱ ማጠቃለያ ላይ ሊቀ ኅሩያን በላይ መኰንን ዐጭር መንፈሳዊ ትምህርት ሰጥተዋል። በትምህርታቸው ውስጥ የክቡር አለቃ አያሌው ታምሩን ሕይወትና መሥዋዕትነት ካስታወሱ በኋላ፤ «እኛ ዛሬ እዚህ ታላቁ ሊቅ ለዘመናት በጸለዩበት፥ ለ፲፩ ዓመታት በግዞት በኖሩበት፥ ጉባኤ አስፍተው ባስተማሩበት ስፍራ የተሰበሰብነው በእኛ ጸሎት አባታችንን እናስምራለን ብለን ሳይሆን እግዚአብሔር ለአባታችን ካደላቸው በረከት እኛንም እንዲያድለን ነው፤» በማለት ተናግረዋል። በመቀጠልም አባታችን አለቃ አያሌው ታምሩ ለቤተ ክርስቲያንና ለአገር፥ ለወገን ትተውት ያለፉት ታሪክ ሕያው ሆኖ እንደሚኖር እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል። በትምህርታቸው ውስጥ፤ «ብፁዕ ብእሲ ዘኢሖረ በምክረ ረሲዓን፤ ወዘኢቆመ ውስተ ፍኖተ ኃጥአን፤ ወዘኢነበረ ውስተ መንበረ መስተሣልቃን፤ ዘዳዕሙ ሕገ እግዚአብሔር ሥምረቱ፤ ወዘሕጎ ያነብብ መዓልተ ወሌሊተ።» «በክፎች ምክር ያልሄደ ሰው ምስጉን ነው፤ በኃጢአተኞችም መንገድ ያልቆመ፤ በዋዘኞችም ወንበር ያልተቀመጠ። በእግዚአብሔር ሕግ ደስ የሚለው ብቻ፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት የሚያስብ፤» በማለት ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት የተናገረውን ቃል (መዝ፤ ፩፥ ፩ እና ፪።) በሕይወታቸው ካስመሰከሩ ቅዱሳን አባቶች አንዱ በዘመናችን ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የተሰጡን አባታችን አለቃ አያሌው ታምሩ ነበሩ ብለዋል። በመቀጠልም ለዚህ ትውልድ ተሰጥተው የነበሩትን የእኒህን ታላቅ ሊቅ ፈለግ ተከትለን፤ «ተዘከሩ መኳንንቲክሙ ዘነገሩክሙ ቃለ እግዚአብሔር ወእንዘ ትሬእዩ ሠናየ ግዕዞሙ ወሞፃእቶሙ ተመሰሉ በሃይማኖቶሙ።» «የእግዚአብሔርን ቃል የነገሩአችሁን ዋኖቻችሁን (መምህሮቻችሁን) ዐስቡ፤ መልካም ጠባያቸውንና ፍጻሜአቸውን አይታችሁም በሃይማኖት ምሰሉአቸው፤» በማለት ቅዱስ ጳውሎስ የሰጠንን ትምህርት (ዕብ፤ ፲፫፥ ፯።) ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል በማለት ትምህርታቸውን አጠናቀዋል።
ከሊቀ ኅሩያን በላይ መኰንን በመቀጠል ቤተሰቡን በመወከል ዐጭር ንግግር ያደረጉት ወ/ሮ ሥምረት አያሌውም፤ «የክቡር አባታችን ከዚህ ዓለም መለየት ለአዳም ልጆች ሁሉ የማይቀር ሕግ መሆኑን ብንገነዘብም በእሳቸው ሞት ምክንያት ያጣነው ነገር እጅግ በጣም ብዙ መሆኑ ኀዘናችንን አጠንክሮታል። ይህ ሁኔታ የተፈጸመበት ዘመን ደግሞ ዘመነ ስደትና ዘመነ መከራ በመሆኑ የተነሣ የኀዘኑ ክብደት በጣም እንዲሰማን የሚያደርጉ ሁኔታዎች አጋጥመውናል። በእናንተና እናንተን መሰል ወገኖቻችን ባንታገዝ ኖሮ ሊደርስብን ይችል የነበረው የስሜት መጎዳት ከግምት በላይ ነው። በመሆኑም በእነዚህ ሁለት የኀዘን ዓመታት ከጎናችን ሳትለዩ ሸክማችንን ያገዛችሁን ወገኖቻችን በሙሉ እግዚአብሔር በቸርነቱ እንዲጎበኛችሁ፤ ከወዳጁ፥ ከአገልጋዩ ከአባታችን ከአለቃ አያሌው ታምሩ (አቡነ ወልደ ጊዮርጊስ) በረከት እንዲከፍላችሁ ፈቃዱ ይሁን። እግዚአብሔር ይስጥልን፤» በማለት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በመጨረሻም ዕለቱን በማሰብ የተዘጋጀውን ጠበል ጠዲቅ ረዳት ከሌላቸው ወገኖች ጋር በመሳተፍ የበዓሉ ፍጻሜ ሆኗል።